እ – ህ – ህ… ወ – ፍ – ዬ . . . ኡ – ሁ – ሁ… ወ – ፊ – ቱ . . .
ከሚለው የአበበ ተካ ዘፈን ጋር ለአመታት የከረመው ፍቅሬ ሰሞኑን አገርሽቶ (ምን እንደቀሰቀሰው ባይታወቅም) እንደገና እንደ አዲስ ከወፍዬ ጋር እየዘመርኩ፣ እያፏጨሁ… አብሬያት አለሜን እየቀጨሁ… የግጥሙን ርቀት… የጥበቡን ጥልቀት ሳብሰለስል… ፍቅርና ወፍ፣ ወፍና ጎጆ፣ ጎጆና ሰው፣ ሰውና እምነት፣ እምነትና ተፈጥሮ፣ ተፈጥሮና ህይወት ምናምን እያልኩ ማደበላለቅ ሲያምረኝ… ሲያመራምረኝና ሲመረምረኝ… ገጣሚው ባይኔ ላይ ይዋልል ገባ… ስምም፣ ክብርም፣ ብርም ተነፍጎት ያለፈው ሙሉጌታ ተስፋዬ… ሰላማዊ እረፍት ሙሌዋዋዋ… በዚሁ ዋዋዋ ልበል እንጂ !
ድምጻዊ አበበ ተካ በአንድ ወቅት የሙዚቃውን ገበያ የተቆጣጠረ… በቅንጣት ዝና የከበረ… ዘፈኖቹ እንደጣፋጭ ቡና እየተደጋገሙ የተጣጣሙለት ምርጥ ዘፋኝ እንደነበር የ1988ቱን የኪነ ጥበብ ፌስቲቫል እና የአቤን ሽልማት (እንዲሁም ለቅሶውን…) ማስታወስ ብቻውን በቂ ነው፡፡ ቆይ ግን አቤ የት ገባ? በቃ እልምምም?!… “ያ ሱዳን ፈናኒ” እያለ ቼቺኒያን እንዳላቀናት እንዲህ ድምጹ ጥፍት?…. ኧረ አቤ አንተ ያቀናሃት ቼቺኒያ ዛሬ ራሷን የቻለች አገር ሆና ምግብም፣ ጥበብም፣ ህይወትም፣ ሞትም እየተቸበቸበባት ነውና እንዳቀናሃት ካለህበት መጥተህ አቃናት ብያለሁ እግረመንገዴን . . .
እና እንደዚያ አቧራ ያጨሰ የነ ወፍዬ ዘፈን አልበም መላው ግጥሞቹ (ከአንድ ዘፈን በስተቀር) የሙሌ እንደሆኑ ሳስብ ያለዋዛ እንዳልተወደዱ ገባኝ… አበበ ተካ ከዚህ አልበሙ በፊት የቀደመ አልበም ነበረው እምብዛም አይታወቅም… እናም ለአበበ ዝና ሌሎች በርካታ ተጨማሪ ተዛማጅ ጥበቦች ቢኖሩም ቅሉ የሙሌ ጣፋጭ ግጥም የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ማንም አይክድም!
*
ማነው ደግሞ ያ ድሮ ጥርሰ ወርቅ የነበረው አሁን ግን ጥርሱ ሃጫ በረዶ የሚመስለው ዘፋኝ?… ያ ነዋ የጥቁር ውሃው ልጅ?… ታምራት ደስታ አትሉኝም!… ታምራት ደስታ የቱ?… ብንባል ብዙዎቻችን ታምራት “ሃኪሜ ነሽ” ነዋ ብለን እንደምንመልስ ጥርጥር የለኝም… ለምን ቢባል ታምራትን ካለመታወቅ ወደ መታወቅ ከከተፋ ቤት ወደ አደባባይ ይዛ የወጣች ዘፈን ሃኪሜ ነሽ ናትና !
♫ . . . ሐኪሜ ነሽ መድሃኒቴ
ፈዋሼ ነሽ እመ እምነቴ
ሐኪሜ ነሽ መዳኒቴ
እኔ አዳም
ብሞት አንቺንስ አልከዳም . . . ♫
♫ . . . አንቺን የመሰለ ሌላ ሰው ቢኖርም
ላይን ይሞላል እንጂ ለነፍስ አይዘምርም
ጠረንሽን ለምጄ እንደ ናርዶስ ሽቶ
ሌሊቱ እንዴት ይንጋ ቀኑስ እንዴት መሽቶ . . . ♫
የዚህም ግጥም ጌታ የታሜ ባለውለታ አሁንም ሙሌ ነውና ክብር ለሙሌ . . .
*
♫ . . . አደራ ልጄን አደራ
ሆዴን ልጄን አደራ . . . ♫
የሚለውን የብጽአት ስዩም ዘፈን ያደመጠ፣ የወለደና እና የከበደ ዘፈኑን ሲሰማ ወይም የብጽአትን በእንባ የተሞላ አዘፋፈን ሲያይ ልጁን ብሎም እናቱን እያሰበ በፍቅር እንደሚቃጠል ዘፈኑን ያደመጠ ቢፈርድ ይሻለኛል. . .
♫ . . . ወልደህ እየው ብሎ ወላጅ የመረቀው
ለልጅ ሲንሰፈሰፍ ያኔ ነው የሚያውቀው
እርብትብት ከንፈሩ ያንገቱ ስር ሽታ
ከሞትም ያድናል እንኳን ከበሽታ . . . ♫
♫ . . . ባልማዝና በእንቁ በከበረ ድንጋይ
አሽቆጥቁጬ አኑሬሽ በሆንኩሽ አገልጋይ
ምናለ ለእምዬ ውሃ ሸጬስ ባድር
ማን ውጪ እንዳይለኝ ካገርና ከእድር . . . ♫
ይህን የመሰለ መቼም ሊደመጥ የሚችል ዘፈን እንዲሁም ሌሎች የአንድ ሙሉ አልበም የብጽአት ዘፈኖች የሙሌ ናቸውና አሁንም ክብር ለሙሌ!… የፀደኒያ ገብረማርቆስ፣ የሃና ሸንቁጤ፣ የመሰረት ሌላም ሌላም… እያሉ መዘርዘር ይቻላል…
እንደው ወፍዬ ኮርኩሮኝ አነሳሁት እንጂ እጅግ የበዙትን የባለቅኔውን የዘፈን ግጥሞች እዚህ ዘርዝሬ አልዘልቀውም… ምናልባት እየቆራረጥን በተለያየ ግዜ መነካካት የቻልን እንደሆን እንጂ!… ግና የዚህ ሁሉ ጥበብ ባለቤት የሆነ ታላቅ ሰው እንደምንምና እንደማንም ተዘንግቶ ሲቀር ማየት በ’ርግጥ ያማል፡፡ ስንዱ አበበ እጅግ የበዛ ክብርና ምስጋና ይግባትና የተወሰኑትን ስራዎቹን ሰብስባ “የባለቅኔ ምህላ”ን አሳትማልናለች… “ጉኖዬ” አክብሮታዊ ምስጋናዬ ባለሽበት ይድረስሽ… ላሁኑ የዘፈን ስራዎቹ ላይ ብቻ ነኝና ስንዱ በመጽሐፉ − ደብዳቤ ለ“ሲኦል”− ስትል ስለ ሙሌ ከጻፈችው ትንሽ ልቆንጥር…
“. . . ይህንን ይሁን ብዬ ጓዶቼን ፈትቼ፣ ህዝቤን አምኜ፣ ችሎታዬን ለዘፋኞች ልስጥ አልኩና ተነሳሁ፡፡ ገበያው እጅግ የደራ ከመሆኑ የተነሳ እንኳን ሌላ ነገርሽን ከዓይንሽ ላይ ኩልሽን ሊሰርቁሽ የሚችሉ ሰዎች የበዙበት ሆነ፡፡ ይህን ትልቅ የገበያ ስፍራ ለመቀላቀል ስንት አሳር እንደቆጠርኩ ዛሬም ሳስበው ይዘገንነኛል፡፡ በቃ የስልጣናቸው የመጨረሻ ዳር ድንበር አሁን ትዝ አለኝ! “የኢኮኖሚው ባለቤት የፖለቲካውም ዋና ባለቤት” እንደሆነ ሁሉ የስራው ባለቤቶች ነጋዴዎች ብቻ ሆኑ፡፡
. . . “እኔ እበላ − እኔ እበላ” እያሉ ከሚሻሙት ጋር ለጨው ለበርበሬ፣ ለውሎ ላዳሩ እንኳ ብዬ አብሬያቸው ለመቆየት አቃተኝ፡፡ ይልቅ ጠጋ ያሉኝ ጋር በማርያም መንገድ፣ በማተብ በክርስትና ለየግል ተነጋግረን፣ ቀኑን አሳምረን፣ ዱአ አድርገን፣ ተፈጥሮንና ፈጣሪን ሳይቀር እያፋጠጥን አብረን ጎጆ ልንወጣ ሰርተን ፈረንካው ሲገኝ አይኔን ለማየት እንኳ ይፀየፋሉ፡፡ አልፈው ተርፈው ብኩርናዬን ሳይቀር እንድሸጥላቸው ሁሉ ጠየቁኝ፡፡
. . . ስሚ ʻንጂ አንድ ቀን “ያንተን የተለያዩ ዘፈኖች መደዳውን ዛሬ አራት በኤፍ ኤም ሰማሁ ብለሽ” በልብሽ ያጨበጨብሽልኝን ዕለት አስታውሼ ምን ትዝ አለኝ መሰለሽ! ያወጣሁላቸው ስሞች! ታምራት ሃኪሜ ነሽ፣ መሰረት ጉምጉም፣ ፀደኒያ ገዴ፣ ብፅአት ገዳዬ፣ ሸህ አብዱ ሃዋብስል ኧረ ስንቱን አድምቄዋለሁ አያ! ምንስ ቢሆን ሙሉጌታ ተስፋዬ ወዲ ሀለቃይ! ተጋዳላይ ነኝ’ኮ! … ” (የባለቅኔ ምህላ፣ ገፅ 133)
እስቲ ደጋግመን እናንብበውና ከባለቅኔ ምህላ ጋር ደግሞ እንመለሳለን… የቻላችሁ አንብቡትማ!… ዛሬም በርካታ ሙሌዎች በዙሪያችን ይኖራሉና ክብር ለጥበበኞች. . . ነጃ ይበለን እያልን በሃና ሸንቁጤ ዘፈን (በሙሌ ግጥም) እንሰነባበት . . .
“ነጃ በለኝ ወሎ ነጃ በለኝ ነጃ
ነጃ በለኝ የጁ ነጃ በለኝ ነጃ
ታውቀዋለህና የፍቅርን ደረጃ . . .
አንዴ በንጉርጉሮ አንዴ በመንዙማ
ሲያወድስ ይውላል የፍቅርን ከራማ !
አጠገቡ ሆኘ እሱን እየካደምኩ
ከራማው ገብቼ ሳጫጭሰው ባደርኩ !
እናቱ ዱበርቲ አባቱ ሼህ ናቸው
አድርገው ያሉትን የሚያደርግላቸው . . . ”
ሰላም!
አብዲ ሰዒድ
ፎቶ: ከስንዱ አበበ ፌስ ቡክ ገጽ የተገኘ!