RSS

ሸ- ገ – ሬ – ዋ . . . (1)

03 Nov

አንቺ የሸገር ልጅ እቴ ሸገሬዋ
ፍቅርሽ አሸፈተኝ ተረታሁ ማሬዋ . . .
*
እንደ ወንዜ ጉብል …
ዘርፋፋ ባትለብሺ፣ ሽንሽን ባታሰፊ፤
ሳዱላ ተላጭተሽ፣
ጠጉርሽን ጎንጉነሽ፣ በመስኩ ባታልፊ፤ …

እንሶስላ ሙቀሽ፣
በአልቦ፣ በድሪ፣ በክታብሽ ደምቀሽ፣
ዘንቢልሽን አንቀሽ፣
__ ገበያ ባትሄጂ፤
በአደስ፣ በከርቤ፣
በብርጉዱ ታጥነሽ፣
በጥላሽ ስር ሁነሽ
ጀግናም ባታፋጂ . . . !
*
እኔስ አንቺን አልኩኝ አንቺን ሸገሬዋ
የጣይቱን ሚሞሳ እንቡጧን ማሬዋ . . .*
ሸ- ገ – ሬ – ዋ!
እኔ እንደማውቃት እንደዚያች ኮረዳ…
ውሃ እቀዳ ብለሽ፣
እንስራሽን አዝለሽ፣ ማልደሽ ባትነሺ፤
ባንገትሽ ዝንጉርጉር፣
ጉራማይሌ ጥርስሽ፣ ቀልቤን ባትነሺ፤
ናፍቆቴን ላጋራሽ፣
በምስጢር ባልጠራሽ፣ ፉጨቴን ባትሰሚ፤
ፍቅርሽን ለማግኘት፥
ልብሽን ለማግኘት፣ ባልወረውር ሎሚ . . . !*
በ’ርግጥ አንቺን አልኩኝ አንቺን ሸገሬዋ
የከተማዋን ፈርጥ እንቡጧን ማሬዋ . . .
*
ሸ- ገ – ሬ – ዋ
እንደዚያች ባተሌ …
አቀበቱን ወጥተሽ፣
ቁልቁለቱን ወርደሽ፣
ማገዶ ባትለቅሚ፣ ከጉድባው ባትፈልጪ፤
ኬሻሽን ዘርግተሽ፣ እህል ባታሰጪ፤
እንክርዳድ ባትለቅሚ፣
ባትከኪ፣ ባትወቅጪ፤
ወገብሽን ጠፍረሽ፣
ወፍጮ ላይ አቀርቅረሽ፣ መጅሽን ባትገፊ፤
ራስሽን ሸብ አ’ርገሽ፣
ጥሬ ባታነፍሺ፣ በወንፊት ባትነፊ፤
ላባወራሽ ክብር
በጭስ ተጨናብሰሽ ቤት ለቤት ባትለፊ::*
መቼም አንቺን አልኩኝ ሁኚኝ እማወራ
አቤት አቤት ልበል ያዘዝሽን ልስራ . . .(አብዲ ሰዒድ
ካዛንቺስ – አዲስ አበባ
ታህሳስ – 2001 E.C)
 
Leave a comment

Posted by on November 3, 2012 in ግጥም

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: