
ከየት እንዳመጣችው ባላውቅም እናቴ ደስታዋ አልያም ትዝብትዋ ከመገረም በላይ ሲሆንባት ሁሌም የምትላት ነገር አለቻት… “ገርሞ…ገርሞ…ደግሞገረመኝ!”… ʻየምር ለአፍሪካ ዋንጫ አልፈናል አይደል?ʼ… እውን ከነ ናይጄሪያ፣ ከነዛምቢያና ቡርኪናፋሶ ጋር ተደልድለን ልንፋለም ነው አይደል?… እውን እምዬ ጦቢያም ወግ ደርሷት ከእግር ኳስ ተፋላሚ አገሮች ተርታ ተሰልፋ ላያት ነው አይደል?… እያልኩ ደግሜ ደጋግሜ ሳሰላስል፣ የኳስ ደስታንና ያገር ደስታን ሳብሰለስል፣… ምክንያቱን የማላውቀው እምባ አይኔን ሲሞላው ዝም ብሎ ይገርመኛል (ጅል ነኝ አይደል?…) ይገርም ይገርምና ይወስደኛል… ጭልጥ አድርጎ ይወስደኛል ወደ ዘመነ ቼልፊኮ… ወደ ዘመነ መንግስቱ… ወደ ዘመነ አዋድ… ወደ ዘመነ ሉችያኖ… ወደ ዘመነ ተስፋዬ… ወደ ዘመነ ስኬት… ወደ ዘመነ ዝና… ወደ ዘመነ ክብር… ከዚያም ቼልፊኮና እግር… እግርና አገር… አገርና ፍቅር… ፍቅርና ክብር…. ይደበላለቁብኛልና እንዲህ እላለሁ . . .
በቼልፊኮ ጫማ እግር እየደማ
በ’ናት አገር ፍቅር ልብ እየተጠማ
ስንት ታሪክ ታየ ስንት ጉድ ተሰማ . . .!
ቼልፊኮ የድሮ የኢትዮጵያ ተጫዋቾች የእግር ኳስ መጫወቻ ጫማ ነው… ይህ ጫማ የሚሰራው እያንዳንዱ ተጫዋች ባዶ እግሩን ወረቀት ላይ ከተለካ በኋላ ሲሆን፣ ሁሉም በየልኩ ሶሉ በሚስማር እየተመታ ይዘጋጅለታል… በጨዋታ መሃል ሶሉ ሊገነጠል ስለሚችልም የዛን ጊዜ ወጌሻዎች መዶሻ ይዘው ወደ ሜዳ ይገቡ ነበር ይባላል… ʻአጃኢበ ረቢ!ʼ አትሉም!?… aha… እንደውም ባንድ ወቅት መንግስቱ ወርቁ ገጠመኞቹን ሲያወራ “ያፍሪካ ዋንጫን በወሰድንበት ጨዋታ ጎል ካገባሁ በኋላ የቸኮልኩት ዋንጫውን ለመውሰድ ሳይሆን ጫማው እግሬን የወጋኝን ቶሎ ፈትቼ ለመገላገል ነው” ሲል በማስፈገግ የጫማውን አስቸጋሪነት ጠቁሞ ነበር…
የጎንደር ልጅ ነው ያውም የቋራ
መንግስቱ ወርቁ ልበ ተራራ …!
(ያዝማሪ ዘፈን)
ግን መንግስቱ ወርቁን የሚገባውን ክብር ለግሰነው ይሆን?!… አይመስለኒ!… ብለን ትንሽ ብናስታውሰውስ?!… መቼም የሚዘከሩት ሌሎች ሲሆኑ ገረመንና “የነሱ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን!”… aha… መንጌ ፊት አውራሪው… መንጌ ጎንደሬው… መንጌ አድባሩ… መንጌ 8 ቁጥሩ… መንጌ የእምዬ ባለውለታ… ደግሞ እኔ ያወጣኋቸው ስሞች እንዳይመስሏችሁ… ሲሞገስበት የነበረ እንጂ!እኛ እንኳን ባቅማችን ድሮ ቢንጎ ስንጫወት B8 ሲወጣ “B መንግስቱ ወርቁ!” ብለን በመጥራት የማስታወስ ሙከራ አድርገንለት ነበር… ብሔራዊ ሎተሪ ሰምቶ ቢንጎ ሎተሪን ሲያዘጋጅ በማጽደቅ አልተባበረንም እንጂ! … aha
በሰባት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች አገርን ወክሎ መሰለፍ፣ ባፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ከሰባት ምርጥ ጎል አግቢዎች አንዱ መሆን (10 ጎል በማግባት)፣ ብሔራዊ ቡድንን በማሰልጠን ላፍሪካ ዋንጫ ውድድር ይዞ መቅረብ፣ ከ115 በላይ አለም አቀፍ ጨዋታዎች በላይ መሳተፍ፣ ከ 65 በላይ ጎሎችን ማስቆጠር፣ በዘመኑ ምርጥ በመሆኑ በጣልያን፣ በግሪክ፣ በስፔይን፣ በፈረንሳይ እና መሰል ሃገሮች እንዲጫወት ተጠይቆ የነበረ መሆኑ እና ሌሎች ብቃቶቹ… ክብር የማይገባው ተራ ነገር ይሆን?!.. ያው የኳስ እውቀቱ ስለሌለኝ የሚመለከታቸው እነ ጋዜጠኛ አበበ ግደይ ወይም ሌሎች እንዲተነትኑት ትቼ ዝም ብዬ መገረሜን ልቀጥል… (የምር ግን ሁሉም ነገር በባለሞያ ሲተነተን አሊያም ሲሰራ ደስ ይላል… ሙዚቃውንም ፖለቲካውንም… ምኑንም ምኑንም ደግሞ ከኔ ወዲያ ብሎ መፈትፈት ሼ ነው እኮ!…. ኧረ ሼሼሼሼሼ…. aha…)
አዋድ ሞሃመድስ ቢሆን በአምስት የአፍሪካ ዋንጫዎች ከመሳተፉም በላይ ኢትዮጵያችን እስካሁን ጉራዋን የምትቸረችርበትን ብቸኛ ዋንጫ ስታነሳ ከነሉችያኖ፣ ከነኢታሎ፣ ከነጌታቸው፣ ከነአስመላሽ፣ ከነክፍሎም፣ ከነበርሔ፣ ከነመንግስቱ፣ ከነተስፋዬ፣ ከነግርማ እንዲሁም ከግብ ጠባቂው ጊላሚካኤል ጋር አብሮ የጨፈረ ተጫዋች አይደለምን?… ግና ምን ተሸለመ? አሊያም ምን ተደረገለት? ብለን ስንጠይቅ…“ምንም የተደረገልኝ ነገር የለም… በርግጥ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሲያገኙኝ በክብር ያናግሩኛል… ሌላው ቀርቶ ባበረከትነው አስተዋፅኦ አማካኝነት የተሰጠንን የእድሜ ልክ የነፃ መግቢያ ትኬት ሰረዙት::”… ሲል ባንድ ወቅት የተናገረው መልስ ይሆነንና እንገረማለን… ግን የነሱ የነፃ መግቢያ ትኬት ቢሰረዝና ከፍለው እንዲገቡ ቢደረግ ለአገሪቷ የኢኮኖሚ እድገት አስተዋፅኦ ያደርጋል ተብሎ ታስቦ ይሁን?… aha… ብሽቅ አለ ጋስ ስብሃት!…
አዋድ ግን ይቀጥላል “እኔ ባበረከትኩት ውለታ ደስ እንዲለኝ… ወጣቶቹ እኛን እያዩ መበረታቻ እንዲሆናቸው እንጂ እኔ የምከፍለው እስካለኝ ድረስ ከፍዬ ‘ገባለሁ… ደግሞም ይመስገን በኑሮዬ ደስተኛ ነኝ” ይሄን ሲናገር ያየሁበት የፊት ገፅታ ውል ሲለኝና የነሰለሃዲን የአሸናፊነት ድል መታሰቢያነቱ ለድሮው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሆነ መባሉን ስሰማ… የምር ገረመኝ!… ገርሞ… ገርሞ… ደግሞ ገረመኝ!
በበኩሌ ያለፉት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ቢዘከሩ ቅንጣት አይከፋኝም!… ግን ደግሞ እንደ መንግስቱ ወርቁ ያሉ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች አሊያም የዛኔው ቡድን ቢዘከርበት (መዘከሩ ካስፈለገ) የበለጠ ትርጉም አይኖረው ይሆን?!… እነ አዳነ፣ እነ ሳላሃዲን፣ እነ ደጉ እና መላው የቡድኑ አባላትስ ቢሆኑ ታሪክ ቀያሪ ከመሆናቸውም በላይ የበለጠ ታሪክ እንዲሰሩ፣ ነገ እነሱም የሚዘከሩበት ስም እንዲተክሉ የተሻለ የሞራል ብርታት አይሆናቸው ይሆን?… በደስታ ጊዜ የሚደረጉ ማናቸውም ነገሮች ነገ የበለጠ ደስታ የሚያስገኙ፣ ለተሻለ ፍሬ የሚያበቁ ቢሆኑ ደስ ይላል… በርግጥም የተሻለ ነገር ያመጣሉና!… ቱ!… ድንቄም ምክር እቴ!…
ደግሞ ይሄን ስላልን አንዳንድ የዋህ ደጋፊዎች ተነስታችሁ “ፀረ ልማት፣ ፀረ እድገት” ምናምን የሚል የሽብር ታርጋችሁን ለመለጠፍ ብትሯሯጡ… እንዲሁም አንዳንድ ከንቱ ተቃዋሚዎች መንገድ አገኘን በሚል የዘለፋ ውርጅብኛችሁን ለማውረድ ብትውተረተሩ አሁንም ገርሞ… ገርሞ… ደግሞ ገረመኝ!… ከማለት ሌላ የምንለው አይኖረንም!… aha… እስቲ ኳስን በኳስነቱ ብቻ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲያደርጉት እነዚህን ምርጥ ልጆች እናበረታታቻው… ያ ሲሆን ብዙ ምርጥ ምርጥ ተተኪ ታዳጊዎችን ማፍራት ይቻላልና. . .
እዚህ ጋር
Tessema Simachew የተባለ የፌስ ቡክ ወዳጃችን ከድል በኋላ የለጠፈውን ብዋሰው ውስጤ ያለውን የበለጠ ይገልፅልኝ ይመስለኛል… “እንዲህ አይነት ቀኖች ያለፈው ጊዜ ማብቅያ ብቻ አይደሉም፣ የመጭው ጊዜም መጀመሪያ ናቸው። ነገ ኳስ ይዘው ወደ ሜዳ የሚሄዱ ህጻናት ሳልሃዲን ሰይድን ወይም አዳነ ግርማን መሆን ስለሚፈልጉ በደስታ ይጫወታሉ። ከዚህ በኋላ ለሌላ አስርት አመታት የበይ ተመልካች በእርግጠኝነት አንሆንም። የሽንፈት ታሪካችንን ስለሰበራችሁልን፣ ጀግኖቻችን ናችሁ።” ክበርልኝ ተሰማ! . . .
ከጨዋታው በፊት ቡድናችንን ይቅናችሁ ስል እንዲህ የሚል ዱዓ የፌስ ቡክ ግድግዳዬ ላይ ለጥፌ ነበር
አዳነ ሳላሃዲን፣ ሳላሃዲን አዳነ
የእምዬ ክብር በናንተ ተጫነ
እንግዲህ አደራችሁን ብርታት አይራቃችሁ
እምዬ እናት ዓለም ዛሬ ትኩራባችሁ . . .ዱዓና ጸሎታችን ተሰማና በስም የተጠሩት ተጫዋቾች እምዬን ታደጓት (እንደ አባባ ታምራት መጠንቆል አማረኝ እንዴ ?!… aha)… ብቻ የሆነ ሆኖ በጭፈራ ውስጥ ሆነን ደግሞ እንዲህ አልን…
አዳነ፣ ሳላሃዲን፣ ሰላሃዲን፣ አዳነ
አገር ከህመሙ በናንተ እግር ዳነ
ስኬት ብልፅግና ይብዛላችሁ
ደስታ ዛሬ ለሰራችሁት ለህያው ውለታ . . . !
እልል በይ ሃገሬ በይ ኩሪ ጨፍሪ
ነገ ደግሞ ሌላ ፈርጦች ልታፈሪ . . . !ክብርና ምስጋና ለመላው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት…
ሁሌም ሰላም እና ዘላለማዊ ፍቅር ለኢትዮጵያችን…
ነገ ደሞ የተሻለ ይሆናል . . . ኢንሻአላህ!
Like this:
Like Loading...
Related