የልጅነት ህልሜ
ነጺዬ እመቤቴ ፍቅሬ አበባዬ
ምነው ድምፅሽ ጠፋ ብቅ በይ ሽታዬ …
*
እኔ ባንቺ ፍቅር . . .
ምስልሽን ስስል፣ ሳሳምር ስቀባ
እልፍ ዘመን ነጉዶ፣ እልፍ ዘመን ጠባ …
አብረን አላሳለፍን፣ ወይ ትዝታሽ የለኝ
በሩቁ እያየሁሽ፣ ናፍቆትሽ ገደለኝ …
ነፂዬ ምኞቴ፣ ነፂዬ ስጋቴ
ነፂዬ ስስቴ፣ ነፂዬ ብሶቴ
አንቺው ነሽ ውበቴ፣ ባንቺው ነው ማማሬ
ከሰው ሰልፍ የምገኝ በወግ ተቆጥሬ …
አንቺ የሌለሽበት . . .
እንጀራው አይወርደኝ ይተናነቀኛል
ውሃ እንኳን ወግ ደርሶት ጀግኖ ያንቀኛል
አንሶላ ትራሱ ይኮሰኩሰኛል
ጨዋታው አይጥመኝ ይጎረብጠኛል …
*
እኔ አንቺን ፍለጋ . . .
ውሃ እንደ አቧራ ባይኔ እየቦነነ
እልፍ እፍኝ በረዶ ጉንጬ እየዘገነ
እጅ እግሬ ደንዝዞ በቆፈን ተይዞ
በቀጩ፣ በውርጩ ወዜ ተመዝምዞ
በድን አካል ይዤ አገር አስሳለሁ
ባገኝሽ እያልኩኝ እንከላወሳለሁ …
ወዴት ነው ያለሽው አለሁ በይኝ ውዴ
የት ነው የማገኝሽ እስቲ ጥሪኝ ግዴ
አንችን በመፈለግ በዛ መማገዴ …
*
እኔ አንቺን ፍለጋ . . .
ሃሩሩ በአናቴ ነግሶ እየነደደ
ህይወት በበረሃው እየተማገደ
በአሸዋው ቃጠሎ
ጅስሜ ተብሰልስሎ
የኮዳዬን ውሃ ጨልጬ አንጠፍጥፌ
በፍቅርሽ ለመለም ተስፋዬን ሸክፌ
ይኸው ካገር አገር እንከራተታለሁ
አለሁ በይኝ ውዴ እጎዳብሻለሁ …
ኧረ ተይ ዝም አትበይ አንቺ ነፃነቴ
ሲገባሽ ስታውቂው ባንቺ መጎዳቴ
እስቲ ተለመኚኝ ብቅ በይ በሞቴ …
ነጺዬ ነጺዬ
ነጺዬ ነጺዬ
ባንቺው ተቃጥዬ
ላንቺው ተብሰልስዬ
አለሁ ሁሉን ችዬ … …!
(አብዲ ሰዒድ)