አንቺ የሸገር ልጅ እቴ ሸገሬዋ
*
መቼም ባንቺ መንደር . . .
ሳዱላ፣ ኮኮባው
ውሃ ከርል፣ እሳት ከርል፣
ፓይስትራ፣ ስትሮው ተብሎ ቢሞሸር፤
ዘርፋፋ ሽንሽኑ፣
ትፍትፍ መቀነቱ፣
በዘመን ጅንሶችሽ ቢልቅ ቢሽቀረቀር፤
አደስ ከርቤሽ ላንቺ ቢሆን ዲዮዶራንቱ፤
ንቅሳት፣ ውቅራት ቢተኩም በታቱ፤
ውበትሽ ሙሉ ነው ቅንጣት ያልጎደለ፤
የአፍዝ አደንግዝ ሃይልን የታደለ . . .
*
እናም አንቺን አልኩኝ አንቺን ሸገሬዋ
እንዳሻሽ አድርጊኝ ተረታሁ ማሬዋ . . .
*
ሸ ገ ሬ ዋ . . .
መቼም ባንቺ ዓለም. . .
ፉጨቴን በሚስ ኮል፣ ሎሚዬን በቴክስት፤
በኢሜል፣ በፌስ ቡክ፣
በSkype በምናምን
ቢሆንም ‘ማወጋሽ የናፍቆቴን ስስት፤
ለክብርሽ መታያ
ባይቆምም ገበያ
ቲያትር ሲኒማው
ካፌው መስክሽ ቢሆን ለዉበት ማዋያ
*
ይሁን አንቺን አልኩኝ አንቺን ሸገሬዋ
በያ ተቀበይኝ አንድ በይ ማሬዋ . . .
*
ሸ ገ ሬ ዋ!…
እንደው ቅር እያለኝ…
ጅም እገባ ብለሽ፣
ትጥቆችሽን አዝለሽ፣ ማልደሽ ብትነሽም፤
ሳውና፣ ውሃ ዋና፣
ስቲም፣ ጠጉር ስራ፣
ጥፍር ከተረገዝ ውበትን ድርደራ፣
ሄደሽ ብታመሽም፤
በፋሽን ላይ ፋሽን መግዛት ብትወጅም፤
ለፍቅርሽ መድመቂያ፣
መንፈስ ማነቃቂያ፣ ሰርፕራይዝ ብትለምጅም. . .
*
ይሁን ችለዋለሁ አንቺን ሸገሬዋ
የከተማዋን ፈርጥ ውዲቷን ማሬዋ
አንቺን ሸገሬዋ፣ አንቺን ሸገሬዋ
አቤት አቤት ልበል ለፍቅርሽ ማሬዋ᎓᎓
(አብዲ ሰዒድ
ካዛንቺስ – አዲስ አበባ
ታህሳስ – 2001 E.C)