“ዶሮ ብታልም ያው ጥሬዋን”
በል እንካ ጥሬ ቃል
_ ከጥሬ ልቦና፣ ለጥሬው ዘመዴ . . .
*
ዶሮስ ጥሬ አለመች፣ ጥሬ ነው አለሟ ፣
ጥሬ ነው ህይወቷ፣ ጥሬ ነው ሰላሟ . . .
‘ምትከርመው በጥሬ
‘ምትኖረው ለጥሬ
አኗኗሯ ጥሬ
አሟሟቷም ጥሬ
ጥሬ… ጥሬ… ጥሬ…
እሷን መች ጠርጥሬ?! …
*
ይብላኝ እንጂ ለኔ፣ ይብላኝ እንጂ ላንተ !
በጥሬ ህልም ዓለም፣ ቀንህና ቀኔ ለተንከራተተ . . .
ተቃውሟችን ጥሬ
ድጋፋችን ጥሬ
ሽብራችን ጥሬ
ህዳሴያችን ጥሬ
ሃዘናችን ጥሬ
ደስታችንም ጥሬ
ጥሬ… ጥሬ… ጥሬ…
ብዙ ቀባጥሬ
“ልማት አሸብሬ” . . .
ሐይሌን አስደንብሬ . . .
እኔና አገሬን አጉል ከማጠፋ
ጥሬ እየጠረጠርኩ እስቲ ላንቀላፋ
አንተም ከጥሬህ ጋር ጥሬ ቀንህን ግፋ . . .
(© አብዲ ሰዒድ፣ ነሐሴ 2004)