ውሃ እንደ አቧራ ባይኔ እየቦነነ
እልፍ እፍኝ በረዶ ጉንጬ እየዘገነ
እጅ እግሬ ደንዝዞ
በቆፈን ተይዞ
ደጁ እንደ መርግ ከብዶኝ ከቤት ብውል ባድርም
ኧረ እንዴት፣ ኧረ እንዴት፣ እኮ እንዴት ‘ቀራለሁ?!
በረዶ ለብሼ፣ በረዶ ጎርሼ እመጣልሻለሁ!
ሰሚኝማ ውዴ …
ቅድም ና ብለሽኝ በሳይክል ስጣደፍ
አቅሌን ነፍሴን ስቼ በረዶው ላይ ስከንፍ
የነጠረው ውሃ ጎማዬን አዳልጦ
ፍቅርሽን ያዘለው ነፍሴ ተፈጥፍጦ
እኔና ሳይክሌ እዚህና እዚያ ወድቀን
በሽራፊ ሰከንድ ላመት ተራርቀን
ጉልበት ወኔ ከድቶን ተሰብረን ተጨንቀን
በጭንቁ በርትቼ
የተረፈ አካሌን ለቅሜ ጎትቼ
ስወድቅ ስነሳ እመጣልሻለሁ
አንቺ ና ብለሽኝ እንዴት ‘ቀራለሁ?!
ኧረ እንዴት፣ ኧረ እንዴት፣ እንዴት ይቻለኛል?!
በረዶ ጎርሼ፣ በረዶ ለብሼ መምጣት ይቀለኛል . . .
ስሚኝማ ፍቅሬ …
መኪናዋም በርዷት ባሱም ተጎትቶ
ወዳንቺ መምጫዬን ጊዜዬን ሰውቶ
ሰማይና ምድሩ፣
ዛፍና ቅጠሉ፣ በነጭ ተሞሽሮ
ነፍስ እያስቆዘመ ቅልጥፍናን ሽሮ
እያስተካከዘ ቢያነጫንጨኝምወዳንቺ ከመክነፍ ከቶ አያስቀረኝም . . .
ኧረ እንዴት፣ ኧረ እንዴት፣ እኮ እንዴት ‘ቀራለሁ?!
በረዶ ጎርሼ፣ በረዶ ለብሼ እመጣልሻለሁ! . . .
ስሚኝማ ፍቅሬ …
እኔነቴ ማሬ …
በጓንት በካፖርቱ በኮፍያው ታጅሎ
ዘንካታው ቁመናሽ ኩርምት ክትት ብሎ
የፊትሽ ወዘና በበረዶው ረግፎየውበትሽ ፀዳል ከራማው ተገፎ
የጎዳና ገጽሽ ጀንበሩ ቢጠልቅም
ʻከቡትስሽʼ ላይ ጣለኝ ፍቅር ጉዱ አያልቅም…
አወይ መውደድ አወይ
አወይ ፍቅር አወይ
እስቲ አሁን በሞቴ ጫማ ይወደዳል ወይ?!…
ቢወደድ ቢጠላ እኔ ምን ተዳዬ
እንኳን መልክሽ ቀርቶ ʻቡትስሽʼ ነው ገዳዬ…
“ገዳዬ ገዳዬ… አንቺ ልጅ ገዳዬ”
ጎጆሽ የተሰራ በሁለመናዬ
ህይወት ማስቀመጫ የክብር ሙዳዬ . . .
“ገዳዬ ገዳዬ… አንቺ ልጅ ገዳዬ”
መጣሁ ተቀበይኝ ማሬ ወለላዬ . . .
(© አብዲ ሰዒድ፤ 2003 E.C)