RSS

ሸበላው በሼፊልድ (2) . . .

19 Dec

በንግሪቭ አደባባይ . . . sheffield

በእንግሊዟ ደብረሲና (ሼፊልድ) ከሸበላው ጋር መጀመሪያ የሄድነው ወደ በንግሪቭ አደባባይ ነበር፣ ይህን አደባባይ በርን ግሬቭም ይሉታል አሉ፡፡ እናም እንደደረስን ግራ ይገባኝ ጀመረ… ግራ መጋባቴን የተገነዘበው ሸበላው “እሺ ሸበላው መርካቶ አብዱ በረንዳ የመጣህ መሰለህ አይደል?” ቢለኝ… “አይ የለም ሲኒማ ራስ ነው የመሰለኝ” ሳቅ እያልኩ…

ያለምንም ማጋነን በርግጥ ሸገር የገባሁ ነው የመሰለኝ፡፡ ከሸገርም ቅልጥ ያሉ ጫትና ጥቃቅን ነገሮች መቸርቸሪያ ሰፈሮቿ የደረስኩ ያህል ነው የተሰማኝ… ታላቋ ብሪታኒያ ስለሚገኙ መቃሚያ ቤቶችና በእንግሊዝ ምድር ጫት መነገድም ሆነ መቃም ያልተከለከለ ስለመሆኑ የሰማሁ ቢሆንም በለምለም ኮባ ቅጠል የተጠቀለለ… የሸገርን ጫት ነጋዴዎች ሊቀታተር የሚችል ትኩስ ጫት በክብር እና በግርግር ሲሸጥ ያጋጥመኛል ብዬ ፈፅሞ አልገመትኩም!… በወግ የተስተካከለ መጅሊስ ያለበት መቃሚያ ቤት አገኛለሁ ብዬማ ፈጽሞ አልጠረጠርኩም!… ማንበብ ሌላ ማየት ሌላ ማለትስ ይሄኔ ነው…

የአካባቢው ድባብ፣ የቸርቻሪ ሱቆቹ ሁኔታ፣ የነጋዴዎቹ ባህሪ፣ ጫት ፍለጋ ገባ ወጣ የሚሉት ዲያስፖራዎች፣ የየመኒዎቹ ዎልፍና ትርምስ፣ የመስጂዱ የርቀት የአዛን ድምጽ፣ የዙሪያ ገባው ቆሻሻ፣ እዚም እዛም የወዳደቁት ፌስታሎችና ቆርቆሮዎች… ኧረ ምኑ ቅጡ ብቻ ምኑም አውሮፓ አውሮፓ አይሸትም! ሸገር ሸገር እንጂ፡፡ ከመጣሁባት ከወግ አጥባቂዋ ስውዲን ጋር እያነጻጸርኩ… ከእትብቴ ምድር ከኢትዮጵያዬ ጋር እያዋደድኩ መጠየቅ ጀመርኩ…

እኔ፦ ቆይ ግን ጫት እንዴት አልከለከሉም?!

ሸበላው፦ አይ ሸበላው! ለምን ብለው ይከለክላሉ?!… ዝም ድንዝዝ የሚያደርግን ነገር ለምን ይከለክላሉ?… ቃሚው ይቅማል ከዚያም ዝምም ብሎ ያኗኗር ዘይቤያቸውን በልምምድ ያውጠነጥናል… ታርጋውንና የተመዘገበበትን ታሪክ ያብሰለስላል…. ምን አደረገኝ ብለው ነው የሚከለክሉት?… አንድ ሰሞን ጫት ይከልከል ተብሎ ቆሞ ነበር አሉ ታዲያ አንዱ ሃራራ አናቱ ላይ የወጣበት ሱማሌ እዚሁ መሃል አደባባይ ላይ ቆሞ “አላህ ሃራም ያደረገውን ወንድና ወንድ መጋባት እየፈቀዱ ለምለም ቅጠል እንዴት ይከልክሉናል? ፋክ ኢንግሊዚ… ፋክ ኢንግሊዚ!” እያለ በጩኸት አቀለጠዋ…

እኔ፦ አሃሃሃሃሃ… ወይ ሱማሌ!… ቆይ ታርጋ ምንድነው? የምን ታርጋ?

ሸበላው፦ አገር ቤት መኪና ነው ታርጋ ያለው አይደል… እዚህ ደግሞ ላንተም መለያ ቁጥር ይሰጥሃል… ያው ታርጋህ እንደማለት ነው… ኮሽታህ ሁሉ ይመዘገብበታል… አለቀ:: ስለዚህ ወደድክም ጠላህም ነጋ ጠባ እርምጃህን ከታርጋህ ጋር ታዛምዳታለህ… የኛ የትራፊክ ፖሊሶች ታርጋ እየፈቱ ሾፌሮችን እንደሚያበሳጩት ሁሉ እዚህም ታርጋህ ላይ ጥቁር ነጥብህን እየለጥፉ ናላህን ያዞሩታል … ሲስተም ነው የሚሰራው የሚሉት ፈሊጥ እዚህ ነው የሚገባህ… አጀብ ነው አቦ!

እኔ፦ ያው በሁሉም የሰለጠኑ ሃገሮች እንደሱ መሰለኝ…. ብቻ ይገርማል…. ይህ ሰፈር ግን ነገሩ ሁሉ አገር ቤት አገር ቤት ይመስላል…

ሸበላው፦ ነው እኮ ነው ታዲያ!… ይህ ሁላ ሸበላ አንገቱ ላይ ስካርፕ ጠምጥሞና አለባበሱን ለውጦ ስታየው እውነት እንዳይመስልህ… ለመመሳሰል እኮ ነው… ልቡም፣ ግብሩም፣ ህልሙም እዛው ነው − እናቱ ቤት፡፡ የኛ ሰው አገር እንጂ አመል አይለውጥም!… ህዝባችን አህጉሩ እንጂ ግብሩ አይቀየርም!… በየሄደበት የራሱን አገር ይገነባል… ታዲያ ሌላውም ሰፈር እንዲህ እንዳይመስልህ… የቀለጡ የፈረንጅ ሰፈሮች አሉልህ…

እኔ፦ እሱስ ልክ ነህ…

ሸበላው፦ እንግዲህ ክተበው!… ለምን እዚህ ያመጣውህ ይመስልሃል?!… ሸበላው ወዳጃችን ትጽፋለህ ስላለኝ እኮ ነው!… አየህ ሰው ነው የሚጻፍ…. ስለ ሰው ነው የሚከተብ… እንጂማ ምድር ያው ምድር ነው… ግንብም ያው ግንብ ነው… ወላሂ የሚከትበን አጥተን እንጂ ስንት ጥራዝ ይወጣን መሰለህ… እስቲ ደሞ ወደ ሻምበል እንሂድ (መኪናውን እያሽከረከረ)…

ቀልደኛው ሻምበል . . .

በ1981 (እ. ኢ. አ) ስለተደረገው የከሸፈ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ… በጓድ መንግስቱ ሐይለማሪያም እና በጀነራሎቹ መካከል ስለነበረው ሽኩቻ… አያ መንጌ ከጀርመን ሲመለስ አየር ላይ እንዳለ እሱን አመድ አድርጎ አብዮቱን ለመቀልበስ ስለተዶለተው ያልሰመረ ዱለታ… ስለጀነራሎቹ ፍጻሜ እና ስለ ጦር ሰራዊቱ የተለያየ ውጥንቅጦች ከየመጽሃፍቱ ከመቃረም በቀር ክዋኔውን በቦታው ሆኖ የታዘበ አሊያም በከፊልም ቢሆን የታሪኩ አካል የሆነ ሰው ገጥሞኝ አያውቅም… ኧረ ያጋጥመኛል ብዬ አስቤም አላውቅ… በእንግሊዟ ደብረሲና ግን ቀልደኛው ሻምበል ጥርስ በማያስከድን ጨዋታው እያዋዛ ልክ ትላንት የተፈጸመ ያህል ሲተርከው ሳይ ወይ ስደት ስንቱን ይዞታል ብዬ ከመቆዘም ሌላ ምን ልል ይቻለኛል…

“አባቴ ያቺን ሰዓት” በሚል ርዕስ በደረጀ ደምሴ ስለ ሜጀር ጀነራል ደምሴ ቡልቶ (የጸሃፊው አባት ናቸው) የተጻፈውን መጽሃፍ የወጣ ሰሞን ማንበቤን አስታውሳለሁ… በጀነራሉ ቆራጥነት፣ ለአላማቸው ባላቸው ጽናት፣ ስለ ጦር ሳይንስ ባላቸው እውቀት መደመሜም ትዝ ይለኛል… አስመራ ከተማ ላይ ስለነበራቸው የመጨረሻ ሰአት ቆይታና ስለህወታቸው ፍጻሜም ያነበብኩት ባይኔ ላይ አለ… እሳቸው በተገደሉበት በዚያች ቅጽበት በቦታው ኖሮ በጆሮው ግራና ቀኝ ጥይት እያፏጨ… ፍጻሜያቸውን የተመለከት፣ የወጡበትን መኪና እስከነታርጋ ቁጥሩ፣ እስከነ ሞዴሉ፣ እስከነአለባበሳቸው፣ እስከነአወዳደቃቸው ፊልም በሚመስል መልኩ የሚተርክ ሰው ማግኘት ግን ከማንበብም በላይ ደስ የሚል ነገር ነው…

ስለ ሜጀር ጀነራል ቁምላቸው ደጀኔም ቢሆን ያው ስለ አብዮቱ ከተጻፉ መጻህፍት እንዳቅሚቲ ቃርሜያለሁ… እንዴት ከሞት እንዳመለጡ፣ እንዴት ጉራጌ አካባቢ እንደተሸሸጉ፣ እንዴት ከሃገር እንደወጡ በመጠኑ ለቃቅሜያለሁ፡፡ የሚኪሊላንድ ታሪክና የሳቸው ካገር አወጣጥ በርግጥ እንደፊልም መስጦኝም ነበር… የደብረሲናው ሻምበል ይህንንና መሰል ታሪኮችንም በሳቅ ፍርስ በሚያደርጉ የጦር ቤት እና የራሽያ ትምህርት ቤት ገጠመኞች እያዋዛ ተረከልኝ… በዚህ አጋጣሚ ምነው ግን ፊልም ሰሪዎቻችን እኒህን ታሪኮች ቢሰሯቸው!… ቀን ከሌት የምናየውንና የምንኖረውን ኑሮ እየደጋገሙ ከሚያሰለቹን እኒህን እና መሰል ታሪኮች ጣል ቢያደርጉልን ይጣፍጥላቸው ነበር… እግረ መንገዳቸውንም ለትውልድ ታሪክ ያስተምራሉ እኮ… (ጥቆማ መሆኑ ነው እንግዲህ… በኛ ቤት ጠቁመን ሞተናል…)

ስለ ኢትዮ ኤርትራ ጦርነትስ ቢሆን በወቅቱ አገር ቤት በግል ስራ ተሰማርቶ ይኖር የነበረው ሻምበል ካለበት ተፈልጎ ተጠርቶ ጦሩን እንዳገለገለ ሲነግረኝ ተገርሜም አላባራሁ… “ከውትድርና ህይወት የራቀ ሰላማዊ ኑሮ ውስጥ ለአመታት ቆይቶ ወደ ጦርነት መመለስ አይከብድም?” ስል እንደዋዛ ለጠየቅኩት ጥያቄ የመለሰልኝ ግን በአእምሮዬ ይመላለሳል…. “እንዴ!… የጦር ባለሙያ እኮ ዋና ተግባሩ አገር መጠበቅ ነው… እኔ አሁንም ቢሆን አገርን የሚነካ ነገር ከመጣ ዛሬም እሄዳለሁ… ያቅሜን ላገሬ ለማበርከት አላንገራግርም…. ጉዳዬ ከአገር እንጂ ከማንም አይደለም… ይሄ ደሞ እኔ ብቻ ሳልሆን ማንኛውም የጦር ባለሙያ የሚጋራው ነው:: የሚያሳዝነው ግን ከዚያ ሁሉ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከንቱ እልቂት በኋላ ባለስልጣን ተብዬው የድሮ የጦር ባለሙያዎች ስላደረጉት እገዛ ሲጠየቅ ሽምጥጥ አድርጎ የ’ኔንና የመሰሎቼን ውለታ ከመካዱም በላይ ʻምን አብዛኛዎቹ እንኳን ለዚህ አላማ ቀርቶ ራሳቸውንም ማገዝ አይችሉም!ʼ እያለ ከንቱ መሳለቅ ሲሳለቅ ስትሰማ ያምሃል”…. ወይ ሻምበል!

ብቻ በዚህም ተባለ በዚያ የዚህ አይነት ሰዎች የታሪክ ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ ለታሪክ ጸሃፊዎችም የሚያበረክቱት ሚና ቀላል አይደለም… በየሃገሩ በርካታ ተመሳሳይ ሰዎች እንደሚኖሩም እሙን ነው፡፡ ምነው በሰላም ተሰባስበው… በዳይና ተበዳይም ይቅር ተባብሎ ለቀጣይ ትውልድ ታሪካቸውን በቀናነት ቢያካፍሉን ስልም የየዋህ ምኞቴን እየተመኘሁ ሸበላውን አየሁት… መደዱን ይቀጥልልኝ ያዘ . . .

እህሳ ሸበላው
አያዋ ጎምላላው
እንግዲህ ክተበው በል ጣፈው አደራ
አንዳች ቢያስተላልፍ ለወዲያኛው ጭፍራ. . .

ኡመቱ በሞላ
እንዲሁ ሲጉላላ
ደጅ ደጅ እንዳየ ውጪ ውጪ እንዳለ
ህልሙን ህልም በላው ቀኑን የትም ጣለ
እስቲ አላህ ያግራው ቀኝ በቀኝ ያ’ርግልን
ምቀኛ ሸረኛን ምንገድ ያስቀርልን. . .

ሸበላው ሸበላው ሸበላው ወዳጄ
መቼም ወገኔ ነህ መከታ ቀኝ እጄ
አንተ ትብስ አንቺ ብሎ እየተነሳ
በደቦ እንዲደቃው የቂምን ነቀርሳ
አሚን በል ዘመዴ ብርቱ ዱዓ አለብን
እምዬና ህልሟ ከንቱ ዳይቀርብን. . .

 

አብዲ ሰዒድ
2005 E.C

 
2 Comments

Posted by on December 19, 2012 in ስብጥርጥር

 

2 responses to “ሸበላው በሼፊልድ (2) . . .

 1. henok

  December 19, 2012 at 12:59 pm

  ወንድሜ አብዲ፣ መራርን ነገርን አጣፍጦ ማቅረብ ተክነህበታል፡፡ ምልከታህ አይደብዝዝ፡፡ ድንቅ ነው/ህ!!

   
  • shegereewa

   December 19, 2012 at 3:20 pm

   ወንድሜ ሄኖክ እጅግ አብዝቶ ያክብርልኝ

    

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: