RSS

ማርዬ . . .

11 Jan

ማርዬ አብሮ አደጌ የልጅነት ፍቅሬ፣maryee22
ማተብ ማንነቴ ነፃነቴ ክብሬ፣
እንዴት ነሽ ባያሌው እንዴት ነሽ አለሜ?!
አንቺ ቅን እመቤት የሌት ተቀን ህልሜ::

እኔ እንደሁ ከድቼሽ እምነትሽን ፍቄ፣
“በማሪያ” ፍቅር ላይ ላዩን ደምቄ፣
አለሁ በነጭ አለም ሰርክ አንቺን ናፍቄ::

ማርዬ … ?!

ድሮ ገና ያኔ ስትወጅኝ ስወድሽ ልባችን ሲጠፋ፣
በፍቅራችን ሰበዝ በዕምነት ስንደዶ ህይወትን ስንሰፋ፣
ጋራ ሸንተረሩ፣ ሜዳና ገደሉ፣ የአበቦቹ ሽታ፥
የመስኩ ላይ ውበት፣
የቀጠፍነው እሸት፣ ያ ውብ ሳቅ ጨዋታ፣
ሁሉም ትዝ እያለኝ እየዞረ ባይኔ
ይደጋግመኛል ባንቺ መብከንከኔ::

ግን እንዴት ነሽ ውዴ? እንዴት ነሽ አለሜ?!
ሰርክ የምትናፍቂኝ የውስጠት ህመሜ::
እኔ እንደሁ ከድቼሽ እምነትሽን ፍቄ
“በማሪያ” ፍቅር ላይ ላዩን ደምቄ
አለሁ በነጭ አለም ሰርክ ተጨንቄ::

ማርዬ … ?!

እኔ ወዲህ ልሸኝ ስትሰናበቺኝ፣
ቅዱስ ቃሉን ይዘሽ መፅሃፍ ስታስመቺኝ፣
ያንገትሽን ማተብ ባንገቴ ስታስሪ፣
የኔን ያንገት ማተብ
ከግማድሽ ጋራ በወግ ስትቋጥሪ፣
በበተስኪያን አፀድ ደውሉ እያስተጋባ፣
ላትከጂኝ ላልከዳሽ ቃል ስንገባባ፣
በአማልክት አጀብ ምዬልሽ ነበረ፣
እርሜን በላሁ እንጂ ቃሌ ተሰበረ::

ማርዬ እመቤቴ የልጅነት ፍቅሬ፣
እንዴት ነሽ ባያሌው ነፃነቴ ክብሬ፣
እኔ እንደሁ ከድቼሽ እምነትሽን ፍቄ፣
“በማሪያ” ፍቅር ላይ ላዩን ደምቄ፣
አለሁ በነጭ አለም ሰርክ ተሳቅቄ::

ማርዬ …?!

የነጃሺ አድባር፣
የሶሃቦቹ አጥንት፣
ጀማ ንጉስ መውሊድ ፣ የሸሆቹ ዱዓ፤
ቡራኬያቸው ደርሶ፣
እምነት ፅናት ለብሶ፣
ለፍቅራችን ፀዳል የሆነን “ሸፈዓ!”፤

የስጋ ወደሙን ምስጢረ አንድምታ፣
አብረን የጎረስነው በፆመ ፍልሰታ፣
ያጠጣሽኝ ፀበል ቀድተሽ በማለዳ፣
ሰርክ እየፈወሰኝ ከሚገጥመኝ ፍዳ፣
ሁሉም በልቤ አለ በደማቅ ተፅፎ፣
ዝንታለም ማይጠፋ አንቺነትሽ ገዝፎ::
ብቻ እንዴት ነሽ ውዴ እንዴት ነሽ አለሜ?!
ሰርክ ያማስታውስሽ የነፍስያ ህመሜ::
እኔ እንደሁ ከድቼሽ እምነትሽን ፍቄ
“በማሪያ” ፍቅር ላይ ላዩን ደምቄ
አለሁ በነጭ አለም ሰርክ ህልሜን ናፍቄ::

ማርዬ …?!

ግን እውነት ከድቼሽ?!
እኔ አንቺን ረስቼ፣ ትቼሽ ይመስልሻል?!
ዳሩ …!? መጥተሽ ካላየሽው …!
እንዴትስ ብነግርሽ እንዴት ይገባሻል!?
ብቻ ትዝ እንዳልሽኝ
ብቻ ት…ዝ…! እንዳልሽኝ 
… ዘመን ነግቶ ይመሻል::

እንኳን አንቺን ቀርቶ …
እንኳን አንቺን ቀርቶ …
የኩበት ጭስ ሽታ፣
የከብቶች ኳኳታ፣
የአህዮች ማናፋት ሁሉ ይናፍቀኛል፤
የእረኞች ፉጨት፣
የወፎች ዝማሬ፣
ቅዳሴና አዛኑ ሁሌም ውል ይለኛል::

ያ …! ደርባባ ፊትሽ፣
ትሁት አንደበትሽ ፣
ሽንሽን፣ መቀነትሽ፣
ነጠላ፣ ዘንቢልሽ፣ ጥላሽ በልቤ አለ፤
ህያው ማንነቴን፣
የፍቅር እመቤቴን፣
ማርዬን፣ ማርዬን፣ ማርዬን እንዳለ::

አንቺ ማለት እኮ!
ባህልና ቅርሴ፣
የዘር ማንዘር ውርሴ፣
ኩራትና ክብሬ፣
እትብት የደም ስሬ፣ እናት አገሬ ነሽ፤
ከውስጤ ነጥዬ፣ ቆርጬ ‘ማልጥልሽ::

ብቻ ግን እንዴት ነሽ እንዴት ነሽ አለሜ
ሰርክ የማስታውስሽ የዘውትር ህመሜ
እኔ እንደሁ ከድቼሽ እምነትሽን ፍቄ
“በማሪያ” ፍቅር ላይ ላዩን ደምቄ
አለሁ በነጭ አለም ሰርክ ተሳቅቄ::

____ / © አብዲ ሰዒድ 2004 E.C / ____
_______ / ኡፕሳላ፤ ስውዲን / _______

 
Leave a comment

Posted by on January 11, 2013 in ግጥም

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: