RSS

ሰውና መኪና . . .

14 Jan

♫… ይላል ዶጁdodg
ይላል ዶጁ
ፏ!… ፏ!… ይላል ዶጁ
ደስ የሚለኝ ሾፌር መልከመልካም ልጁ
እኔስ እህቱ ነኝ ይብላኝ ለወዳጁ
ፏ!… ፏ!… ይላል ዶጁ
ፏ!… ፏ!… ይላል ዶጁ …

ይላል ዶጁ …
ፈገግታውን ጋብዞ … አንዴ ቢያናግረኝ
ይህም አለ ለካ … መውደዱ ጀመረኝ
ልክ እንደመኪናው … እያሽከረከረ
ሹፌር ነው የኔ ፍቅር … ልቤን ያበረረ … ♫

መቼም ይህ የነጻነት መለሰ ዘፈን ቆየት ባለው ጊዜ ሹፌር እና ለፍቅር ተመራጭነት ያላቸውን ዝምድና እንድታብሰለስል ያደርግሃል… አንድ ትንሽ እድሜው ገፋ ያለ ጎልማሳ አግኝተህ “እንደው ግን ሾፌር እንዲህ ተወዳጅ ነበር እንዴ? ነው ወይስ ዶጅ የሚባለው አሜሪካን ሰራሽ መኪና ለኢትዮጵያ አዲስ ስለነበረ ነው?” ብለህ ብትጠይቀው… “እንዴ ምን ነካህ?!… ያኔ’ኮ ሹፍርና ማንም ዘሎ ያልጠገበ ወጠጤ ዘው ብሎ የሚገባበት ሙያ አይደለም!… ረጋ፣ ሰከን!… ኮራ፣ ቀብረር ያለ!… ኮረዶቹ ሁሉ የሚዋልሉለት ቄንጠኛ ጠምበለል የሚመርጠው ሙያ እንጂ!… እንዲህ እንደዛሬው በስድብና በዘለፋ ተክነህ የምትሞላፈጥበት እንዳይመስልህ… ዶጅህን ፏ!… ፏ!… እያደረግክ በሸገር ጎዳና ስትፈስ የስንቷ የሰከነች ቆንጆ ልብ አብሮ ሲፈስልህ እንደሚውል ባየህ… እስቲ ስማው ዘፈኑን…. ስማው ዘፈኑን…” እያለ ወዳሽከረከራት ዶጅና ወዳበረራት ኮረዳ በትዝታ ሲከንፍ… ዘመንህን አፈር ድሜ ማስጋጡ እያብሰለሰለህ ከነጻነት መለሰ ጋር ትቀጥላለህ . . .

♫… ቤትሽ የት ነው አለኝ አልኩት አራት ኪሎ
በየት በኩል ቢለኝ ትንሽ ወረድ ብሎ
መቼ ልምጣ አለኝ ጧትም ማታ
ምን ለብሼ ቢል ሱፍ ካቦርታ
ምን ይዤልሽ ቢል ቸኮላታ
የምጠጪው ቢል አረንቻታ

አረንቻታ… አረንቻታ
ሿ!.. ሿ!… አረንቻታ
በምሽት ጨረቃ ለብሰህ ውብ ካቦርታ
ከቸርችል ጎዳና ገዝተህ ቸኮላታ
ናልኝ ማታ ማታ …

አረንቻታ…
ትንፋሹ ቸኮላት … ጽጌሬዳ ቃና
ልቤን ይዞት ሄዶ … መች ተመለሰና
ጠይም አሳ መሳይ … ውብ አነጋገሩ
ሙያውና ፀባይ … ዉበቱ ማማሩ …♫

እያለች አራዳዋ ነፂም ይዛህ ጭልጥ ትላለች… ወዳማታውቀው፣ ወዳልኖርከው ዘመን ታከንፍሃለች… ምን ምን እንደሚል ጣዕሙን ሳታውቀው አረንቻታ መጠጣት ያምርሃል… “አረንቻታ!… አረንቻት… ሿ!… ሿ!… አረንቻታ…” እያልክ አብረሃት ትዘፍናለህ… ያልኖርክበት ዘመን ይናፍቅሃል… ዶጅ መንዳት ያምርሃል… ሱፍ ካቦርታ ስትደርብ ይታይሃል… ፏ!… ፏ!… ማለት ይቃጣሃል… ቸኮላት ግዛ ግዛ ይልሃል (የምትሰጣት ኮረዳ ባትኖርም)… ቸኮላት ቸኮላት ያሰኝሃል… ቸርችል ጎዳና ይመጣብሃል… ቸኮላት ለመግዛት ጎዳናውን ትያያዘዋለህ…. ትወጣዋለህ ወደ እምዬ ፒያሳ… ወደ አራዶቹ መንደር…

በጉዞህ ውስጥ ከቸኮላት ይልቅ በመደዳ የተደረደሩትና ለገበያቸው መድራት ሟችን የሚናፍቁት የሬሳ ሳጥን መሸጫ ሱቆች ያዛጉብሃል… ያላዝኑብሃል… ያፋሽኩብሃል… በአበባ እና በቀለማት አሸብረቀው ሟችነትህን ያሳስቡሃል… ሳታስበው ሿ!… ሿ!… ማለትህን ይነጥቁሃል… ሞት ሞት ይሸትሃል… የማሽከርከር ምኞትህ ብን ብሎ ይጠፋብሃል… አሁን ባንተ ዘመን ደግሞ ማሽከርከርና ሞት ያላቸውን ዝምድና ያስታውሱሃል… “እንትን መኪና ተገለበጠ… ይሄን ያህል ሰው ተጎዳ… ይሄን ያህል ሰው ሞተ…. መኪኖች ተጋጩ፣ ገደል ውስጥ ገባ!”… ምናምን የሚል ዜና ያስበረግግሃል…

መቼም አሁን ባለንበት ዘመን የመኪና አደጋን ወሬ መስማት የለት ተዕለት ተግባር ያህል የለመድነው ክስተት እየሆነ ነው… ሁሌም ግን እንደ አዲስ ያስደነግጠናል… ያስጨንቀናል… ያስበረግገናል… አሁን በሰሞኑ የሰማነው ዜና ብቻውን እጅጉን ያሳዝናል!…

በረጅም ርቀት የሩጫ ውድድር (በማራቶን)የሚታወቀውና በናዝሬት ከተማ ተወልዶ ያደገው የ 27 አመቱ አትሌት አለማየሁ ሹምዬ በመኪና አደጋ ህይወቱ እንዳለፈች ሰምተናል… እጅግ ያሳዝናል… አትሌት አለማየሁ በ2008 በጣልያኗ Vercelli ከተማ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሩን በቀዳሚነት በማሸነፍ ጀምሮ በፖላንድ፣ በቤይሩት እና በሌሎች አገሮች ከማሸነፉም በላይ በፍራንክፈርት፣ በሮተርዳም እና በሌሎች ከተሞችም ባስመዘገባቸው ጥሩ ሰአቶች ብዙ ተስፋ የነበረው ወጣት ነው… እንደ ግለሰብ ቤተሰቦቹን፣ ጓደኞቹን፣ አጋሮቹንና ዘመዶቹን አጉድሏል… እንደ አገርም ብርቱ ተስፋ የነበረውን አትሌት ማጣት ብዙ ያጎድላል… ለቤተሰቦቹና ለወዳጆቹ መጽናናትን ይስጥልኝ…

ከዚህ በፊትም እንደ አለባቸው ተካ አይነት ውድ ሰዎችን በተመሳሳይ አጥተናል… በየቤቱ የጎደለውን፣ የተጎዳውን ቤቱ ይቁጠረው… በ’ርግጥ የአደጋ መንስዔ የሾፌር ችግር ብቻ አይደለም… ብዙ ለአደጋ የሚያጋልጡ ምክኒያቶች ይኖራሉ… ቢሆንም ግን እላለሁ አሽከርካሪዎች ያለባችሁን ከባድ ሃላፊነት በአግባቡ ተወጡ“ ከመሞት መሰንበት” ደግ ነውና… የሚመለከታችሁ አካላትም በወገን ነፍስ አታላግጡ…

♫… ቤቴ ከመንገድ ዳር … ካውራጎዳናው ነው
በጡሩምባህ ጠርተህ … ነይ ብትለኝ ምነው
በኔ አልተጀመረም … ሰውን ሰው መውደድ
ፏ!… ፏ!… ብለህ ጥራኝ … ልምጣ ከመንገድ… ♫

እያለች መንገድ መንገድ እያየች ቸኮላትህንና አረንቻታህን ለምትጠብቅ ወዳጅህ መኪናህን ፏ!… ፏ!… አረንቻታህን ሿ!… ሿ!… እያደረግክ በሰላም ግባላት!

መልካም መንገድ !
አብዲ ሰዒድ

 
Leave a comment

Posted by on January 14, 2013 in ስብጥርጥር

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: