RSS

እግር ኳሳችን . . .

24 Jan

እኛና ተሳትፎ . . .  budinachen

ኢትዮጵያችን በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የመጨረሻዋን ተሳትፎ ያደረገቸው በ1982 (እ. አ. አ) በሊቢያ ተካሂዶ በነበረው 13ኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር እንደነበር ሰምተናል… እነሆ ከ31 አመት በኋላም ክብራችንን ለመለሱልን ዋልያዎቹ የላቀ ፍቅርና ምስጋናችንን እያዥጎደጎድን እንገኛለን… ከዚህም በላይ ይገባቸዋል!… የሽንፈት ከራማችንን እንደገፈፋችሁት በክፉ የሚያያችሁ ከራማው ይገፈፍ አቦ!… 

መሃመድ አሊ ሸዳድ . . . 

ኢትዮጵያችን ከተሳተፈች 31 አመታት ይቆጠሩ እንጂ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ግብ ካስቆጠረች 37 አመታትን ቆርጥማለች… የመጨረሻ ጎሏን ያስቆጠረችው በ1976 (እ. አ. አ) አዲስ አበባ ላይ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ተካሂዶ በነበረው 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ነበር… ይህች የመሃመድ አሊ (ሸዳድ) ጎል በወቅቱ ኢትዮጵያን ከግብጽ ጋር 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት እንዲለያዩ ያስቻለች ነበረች… 

አዳነ ግርማ . . . 

አገራችን ለመጨረሻ ጊዜ ባፍሪካ ዋንጫ ጎል ስታስቆጥር አዳነ ግርማ አልተወለደም ነበር… ኧረ ገና አልታሰበም!… እየተሰቃየንበት የከረምንበትን የጎል ረሃብ፣ የጎል ጥማት፣ የጎል ድርቅ ድራሹን ስላጠፋልን… ታሪካችንን ስለቀየረልን… በ’ርግጥ የትኛውም አይነት ሙገሳ ይገባዋል… ከንግዲህ የሸዳድ ጎል ቅርስ ብቻ ተደርጋ መወራቷ አብቅቷል… ከ’ንግዲህ በእግር ኳስ ተስፋ የራቃት ኢትዮጵያ እየጠፋች ነው… ከ’ንግዲህ የኳስ ተስፋዋ እየለመለመ ነው… 

በየሰፈሩ የኳስ ፍቅር ያላቸው ታዳጊ ልጆች በወኔ ኳስ እያንከባለሉ እንደሆነ እናምናለን… እንደ አዳነ፣ እንደ ሰለሃዲን፣ እንደ ጌታነህ፣ ባጠቃላይ እንደ ዋሊያዎቹ ዝናቸው እንዲወራ እየተመኙ እንደሆነ ጥርጥር የለኝም!… እነዚህን ልጆች አቅማቸውን ተረድቶ የሚደግፋቸው… በአግባቡ የሚንከባከባቸው እስካለ ድረስ ገና ብዙ ታሪክ ይሰራል!… 

መሃመድ ኡስማን (ሚግ) . . . 

መሃመድ ኡስማን (ሚግ)… 😦 … ልክ የዛሬ 31 አመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጊኒን ብሔራዊ ቡድን አሸንፎ ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ያስቻለ ሰው ነበር (ነፍሱን አላህ በጀነት ያኑርልንና)… ይህ ከድሬዳዋ የተገኘ ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋች በጣም ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ ሚግ በሚለው ቅጽል ስሙ ይታወቃል… እነሆ ከ’ሱ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሊያስገባን የሚችል ጎል ማስቆጠር ተስኖን 31 አመታት ጠብቀናል… ስለምን ግን 31 አመታት ፈጀብን?… እውን የጥንቶቹን ያህል ተጫዋቾች ማፍራት አቅቶን ነበርን?!… ብለን ብንጠይቅ የዚህ ሰው ታሪክ በከፊል ጥያቄያችንን ይመልስልናል… 

ይህ ለአገር ታላቅ ውለታ የሰራ ሰው ህይወቱ ያለፈው የመከራን ጽዋ እንደተጋተ ነበር… ለዚህ አኩሪ ታሪኩ ኢትዮጵያችን የከፈለችው እስር… ርሃብ… እርዛት…. መገፋት… እና ጎዳና ላይ ማደርን ነበር… ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ አገር ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ያበቃ ሰው በረንዳ እያደረ በረንዳ ላይ ሲሞት እያየ የትኛው ትውልድ ይሆን በተነሳሽነት ኳስ ሊጫወት የሚችለው?!…. ከቶም አይታሰብም!… ታሪክ መስራት የፈለገ ታሪክ ሰሪዎቹን ያከብራል!… አይከኖቹን ያልቃል!… 

ከሁለት ወይም ከሦስት አመት በፊት የስፖርት ጋዜጠኛው ሰኢድ ኪያር ለዚህ ድንቅ የኢትዮጵያ ልጅ እናትና ቤተሰቦች የተደረገን የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት አስቃኝቶን ነበር (በነገራችን ላይ ጋዜጠኛ ሰኢድ ኪያር ታላላቅ ስፖርተኛቻችንን እንድናውቃቸው በምታደርገው ጥርት በበኩሌ እጅግ አድርጌ አመሰግንሃለሁ) እናም የተመለከትነው የቤተሰቦቹ የኑሮ ደረጃ በ’ርግጥም ያማል!…

እስቲ እሰቡት ከወራት በፊት ላፍሪካ ዋንጫ እንድናልፍ ያስቻሉንን ጎሎች ያስቀጠሩትና እንዲያ ያስቦረቁን… ዛሬም ያስፈነደቁን… ሳላሃዲን ሰኢድ ወይም አዳነ ግርማ ወይም ሌላ የቡድኑ ተጫዋች ተጎሳቁለው ጎዳና ወድቀው ቢታዩ በርግጥ ኢትዮጵያችን አትጎሳቆልምን?… ኧረ ክፉ አይንካቸው!…

እናም እላለሁ አሁን ያገኘነው ክብር ይቀጥል ብሎም የተሻለ ስኬት በዘላቂነት እናስመዘግብ ዘንድ ባለታሪኮቻችንን እናክብር … ታላቁን ያወቀ… የታላቁን ስራ ያከበረ… ከታላቁ ስህተት የተማረ… በ’ርግጥም ታላቅ ነገር መስራት ይቻለዋልና!… መሃመድ ኡስማን ከ 8 አመት በፊት እንዳዘነብን፣ እንደተከፋብን፣ በረሃብና በእርዛት አልፏል!… እሱን ማክበር እስከፈለግን ድረስ ግን ዛሬም ልናስበው እንችላለን…

በየተሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ብርቱ ስራ የሰሩ ክብር ብሎም የተሻለ ኑሮ የሚገባቸው ብዙ ሰዎች ዛሬም አሉን… እናም አይናችንን ገልጠን እንመልከታቸው… እናመሰግናለን… እናከብራችኋለን… እንወዳችኋለን…. እንበላቸው!… እነሱን ስናከብር ኢትዮጵያችንን ትከብራለችና!… 

“ምን በደስታ ሰዓት ያላዝንብናል?”… የሚለኝ ቢኖር ልክ ነው!… ጊዜው የደስታ እንጂ የማስለቀሻ እና የችግር ወሬ የመዘብዘቢያ አይደለምና!… በደስታው ወቅት ደስታውን እንዴት ማስቀጠልና እንዴት ተደጋጋሚ ደስታን ማጣጣም እንደሚችል የሚያውጠነጥን ግን በ’ርግጥ ነገም ደስተኛ ይሆናል!… 

እንደው ተምሳሌት ስለ ሆኑ ሰዎች ካወራን አይቀር በነካ እጃችን የሙዚቃችንን ባለውለታ የሆነውን Abebe Melesse-አበበ መለሰንም እናስበው እስቲ!… ሁለቱም ኩላሊቶቹ ታመው ድጋፍ ፍለጋ ላይ ነው… ሁለት ብር ለሁለት ኩላሊቶቹ!… ሞባይሎን 832 ላይ ይጫኑ ከዚያም Z የሚል መልዕክት ይጻፉ… አቤን ያድኑ… በሙዚቃው ይዝናኑ… 

ክብር ለዋሊያዎቹ!… 
ዘላቂ እድገት ለእግር ኳሳችን!…. 
ብርቱ ጥንካሬና መልካም ውጤት ካናንተ ጋር ይሆን!

አብዲ ሰዒድ

 
1 Comment

Posted by on January 24, 2013 in ስብጥርጥር

 

One response to “እግር ኳሳችን . . .

  1. taomali

    April 1, 2013 at 2:50 am

    አበበ መለሰነ ፈጣሪ ምህረቱን ይላክለት፡፡ ለፈጣሪ የሚሳነው አንዳች የለምና! ሆኖም ግን አበበም በዚህ ክፉ ደዌ ተይዞ ሳለ ሁለት ነገሮችን ማቆም እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ አንድ መጠጥ ሌላው ደግሞ ፍትወት፡፡ በቅርቡ የማታ ክበቡን መሸጡን ሰማሁና ምነው ብል መጠጥ ሴት አሉኝ፡፡
    አበበ መለሰ ቤተ እስራኤላዊ ነውና ባለበት እስራኤል ለሚያስፈልገው ሕመም ሁሉ ሙሉ ሕክምና በነጻ ይሰጠዋል ታዲያ ስራውን እየሰራ ነጻ ሕክምነና እያለው፤ ዋስትናው ሳይጓደልበት ምንድን ነው ይሄ ሁሉ ጫጫታ

     

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: