RSS

*** የጸጥታ ያለህ ?! ***

30 Mar

Image
ባለፈው ”በዣንዣድ ሰላም ሲናድ” ስል የዴርቶጋዳው ደራሲ በሐዋሳ ከተማ ስለከፈተው ”ዣንዣድ ባርና ሬስቶራንት” የቸከቸኳት ሚጢጢዬ ትዝብት ብዙ ሙገሳዎች እንዲሁም ድቆሳዎች አስነስታለች… እሰይ እንኳን አስነሳች!… ሙገሳውም ትንኮሳውም በቀና ልቦና እስከተንሸራሸረ ድረስ ለሚፈለገው ለውጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታልና! 

በበኩሌ ይስማዕከ ደራሲ ነውና አይነግድ!… ደራሲ የሆነ ሰው ከወረቀትና ከእስክሪብቶ በቀር ሃብት ሊኖረው አይገባም!… የህዝብ ልጅ ነውና ሲታመም በልመና ይታከም!… ሲሞትም ለቀብሩ ማስፈጸሚያ እርዳታ ይሰብሰብለት!… ደራሲ ነውና በድህነት ይፎክት!… ስለምን ይነግዳል?!… ስለምንስ ራሱን በሃብት ያበለጽጋል?!… አላልኩም!… አልወጣኝም!… ይቺው ሚጢጢዬ የሰውነት ልኬም እንደሱ እንድል አትፈቅድልኝም!… በፍጹም!

የጥበብ ሰው ሲነግድና ሲያስነግድ… ወደ ተሻለ የኑሮ ደረጃ ሲሸጋገር… ጸሃፊያንን ያበረታል፣ ለዘርፉ መበልጸግም አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያበረክታልና ወደ ንግድ ስራ ጎራ በማለቱ ልባዊ የሆነ ድጋፍ እንጂ ተቃውሞ የለኝም!… ነገር ግን ምንድነው የሚነግደው?… እንዴት ነው የሚነግደው?… የት ነው የሚነግደው?… የሚሉትን ጥያቄዎች ከሌላው ሰው በተለየ በትኩረት እጠይቃለሁ!… ምክኒያቱም ጥፋቱንም ልማቱንም የሚከተሉ ብዙ ተከታዮች አሉትና!… 

”ዣንዣድ ባርና ሬስቶራንት” የተከፈተው ፍጹም ሰላማዊ የሆነ መኖሪያ መንደር ውስጥ ነው… የአካባቢውን ሰው ሰላም እየረበሸ ነውና ተገቢ አይደለም!… ይህ አይነቱ ሰላምን የመንሳት ተግባር ደራሲ በሆነ ግለሰብ ሲፈጸም ደግሞ የበለጠ ያማል!… እናም የእርምት እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል… ለዚህ ጉዳይ ቦታውን የሚፈቅዱ የስራ አስፈጻሚዎችም ሊያስቡበት መንግስትም ለድምጽ ብክለት ችግር አበክሮ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ነው የኔ ሃሳብ!… አራት ነጥብ!

”ምነው መኖሪያ መንደር ውስጥ ጭፈራ ቤት ሲከፈት ብርቅ ነው እንዴ?… እኛ ያደግነውስ ከግድግዳችን ጎን እየተጨፈረብን አይደለም እንዴ?… ምነው እስከዛሬ አላንገበገበህም?… ምነው በሌሎቹ ላይ አልተነሳህም?… ምን ደርሶ ለአካባቢ ሰላም ተቆርቋሪ ይመስል የግል ጥላቻህን ትቀባጥርብናለህ?!”… ጃስ ገለመሌ ላላችሁኝ ሁሉ… … 

“እኛ የምንፈልገው የተዛመተን እኩይ ተግባር የሚቀንስ፣ ለተሻለ ለውጥ የሚያተጋን እንጂ የሚያባብስ አውቆ አጥፊን አይደለም ነው መልሴ!… እንደ ወረርሽኝ የተዛመተ አጉል ተግባር ሁሉ ሃይ የሚል እስካልተገኘ ድረስ ልክ ነው ማለትም አይደለም!… ኧረ በህግ ልንላቸው ይገባል (ህጉ ባይኖርም!… ህጉ ባይተገበርም!…)” 

በየሰፈሩ የነዋሪን ሰላም የሚነሱ ተግባሮች ሞልተዋል… በሃይማኖታዊ ትምህርት… በንግድ እንቅስቃሴ… በፖለቲካ ቅስቀሳ እና በሌሎች በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተሳበቡ የሚካሄዱ ረብሻዎች ልክ የላቸውም!… ለድምጽ ብክለት ያለን ምልከታ እጅግ አናሳ ከመሆኑ የተነሳ የየእለት ኑሯችን መደናቆር የበዛበት እንደሆነም አያጠያይቅም!… 

እናም እነዚህን የጤና ጠንቅ የሆኑ የመደማቆር ድርጊቶች ልናወግዛቸው ይገባል!… ባወገዝናቸው ልክ ወደ ሰላማዊ ኑሯችን እንጠጋለን… ሰባኪውም ያለ ብክለት ይሰብካል!… ነጋዴውም ያለ ብክለት ይነግዳል!… ተራማጁም ያለ ብክለት ይራመዳል!… ከድምጽ ብክለት የጸዱ ከተሞቻችንም ይበዛሉ!… ያብዛልን አቦ… 

ይህ ማለት ግን ትችቶች ሁሉ ስርአት በጎደለው መልኩ የግለሰብን ግላዊ ህይወት በሚያብጠለጥል ሁኔታ ይካሄዱ ማለት አይደለም… ደራሲውን በተመለከተም ምናልባት ስሜታዊ ሆኜ ስድብ ነገር ተጠቅሜ ከሆነ ከመናደድ የመነጨ ነውና ይቅርታ!… እታረማለሁ!… የጻፉኩት በሙሉ ግን ያየሁትን አንዳች ነገር ከራሴ አልጨመርኩም!… እታረማለሁ ስል ለስሜታዊነቱ ብቻ ነው!

ያነሳሁትን ጉዳይ ግን አሁንም ደግሜ አነሳለሁ… የሰፈር ሰላም ሊነሳ ፈጽሞ አይገባም!… ይህ አይነቱን የግዴለሽነት ተግባር ከደራሲ አልጠብቅም!… እናም ወይ ድርጅቱን ያስተካክል አልያም ለጫጫታና ለዳንኪራ በሚመቸው ሰፈር ወስዶ ይክፈተው… 

የሆነው ሆኖ ሃላፊነት የሚሰማው አስተዳደር ባይኖር እንኳ በሃላፊነት መነገድ የባለ ህሊና ግዴታ ይመስለኛል!… እናም ለድምጻችን ለከት እናብጅለት… 

መልካም ቅዳሜ!

አብዲ ሰዒድ

 
1 Comment

Posted by on March 30, 2013 in ስብጥርጥር

 

One response to “*** የጸጥታ ያለህ ?! ***

  1. Hudad

    March 30, 2013 at 8:33 am

    “እኛ የምንፈልገው የተዛመተን እኩይ ተግባር የሚቀንስ፣ ለተሻለ ለውጥ የሚያተጋን እንጂ የሚያባብስ አውቆ አጥፊን አይደለም ነው መልሴ! ሸጋ ብለሃል አብዲሾ! መልካም ቅዳሜ

     

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: