♪♪ ውቢቱ ጎጃሜ
. . . ውቢቱ ጎጃሜ
ትመጫለሽ በህልሜ ♪♪
♪♪ ዓለም ዓለምዬ
ዓለም ዓለምዬ . . .
እስቲ ዝምድናሽን ቆጥረሽ ንገሪኝ፤
ከእህት ከወንድሜ የበለጥሽብኝ።
እመጣለሁ ብለሽ መቅረትሽ ምነው?
የነማንን ጸባይ ልታመጭብኝ ነው?!
ትሁኔ . . . ትሁኔ . . .
አንቺ አትመላልሽ እምጠለሁ እኔ። ♪♪
. . . ከአሶሳ ማዶ ያለች ትንሽዬ መንደር ውስጥ ያንጎራጉራል… እንደወጣች ቀርታ… እንደዋዛ ጠፍታ ከቀዬዋ የተሰወረችበት የጎጃም ኮረዳ ስትናፍቀው ይተካክዛል… ተስፋዬ ወርቅነህ የተባለ ዘፋኝ ለሱ ብቻ የዘፈነለት ይመስለዋል… በዚያ በሩቅ አገር በመሃል አዲስ አበባ… በስም ብቻ በሚያውቀው ጎጃም በረንዳ ላይ ክርትት ብሎ የተከተተውን ይህን ቅን ዘፋኝ ፈጣሪ ነፍሱን ከደጋጎች ተርታ እንዲያሰልፍለት እየተመኘ ይቀጥላል…
“እውን ግን ተስፋዬ እጅግ ድንቅ የሆነ ድምጻዊ አይደለምን?… ድምጹ?… ግጥሙ?… ዜማው?…” እያለ ሊተነትን ይቃጣዋል… እራሱ ጠያቂ እራሱ መላሽ ይሆንና ሙዚቃ እናውቃለን የሚሉ ተንታኞች ስለዚህ ዘፋኝ ሲተነትኑ ሰምቶ ባለማወቁ ይንቃቸዋል… “አያውቁማ!… ሙዚቃ የት ያውቃሉ?… ዝም ብለው በመንጋ ወደነፈሰበት ያጨበጭባሉ እንጂ!” ይሳደባል…
ምንም እንኳን ከአሶሳ ማዶ ቢኖር ስለ ወሎ፣ ስለ ጎንደር፣ ስለ ጎጃም፣ ስለ ትግሬ፣ ስለ ኦሮሞ፣ ስለ ደቡብ ህዝቦች የተዘፈኑ ዘፈኖችን አዘውትሮ ያደምጣል… ያቺን ውብ ጎጃሜ ከወደደ ወዲህ ደግሞ ጎጃም ጎጃም ማለቱ ብሶበታል… አሁን ግን ካጠገቡ የለችም!… ስትናፍቀው… ባይኑ ላይ ስትመላለስበት… ይይዘው ይጨብጠው ሲያጣ… ከአሶሳ ማዶ አያመጣት ነገር መላው ሲጠፋበት… ጠቅልሎ አይሄድ ነገር አቅሙም ጉልበቱም ሲያንሰው…. ዝምምም ብሎ ያንጎራጉራል… ምስጋና ለተስፋዬ ወርቅነህ…
♪♪ አስደግመሽብኝ አለቃ ፈንቴን
ሳር ቅጠሉ ሁሉ መሰለኝ አንቺን
አስተብትበሽብኝ የኔ ኩንስንስ
ወገቤ ያላንቺ አይንቀሳቀስ …
ትሁኔ . . . ትሁኔ . . .
አንቺ አትመላልሽ እምጠለሁ እኔ። ♪♪
. . . እሷ ብቻ ሳትሆን የማያውቃቸው አለቃ ፈንቴ ይናፍቁታል… “ምነው ለኔም መተው በደገሙልኝ… ምነው በደገሙብኝ… ምነው በዚህ ሕዝብ ላይ ሁሉ የፍቅር፣ የሰላም፣ አብሮ የመኖር ድግምታቸውን በተበተቡበት… ምናለ ፍቅር በፍቅር ቢያንበሸብሹንና ያለ ፍቅር መንቀሳቀስ ቢሳነን” … … “አይ አለቃ ፈንቴ!… ይበሉ እስቲ!… ወይ እሷን ያምጧት ወይ እኔን ይውሰዱኝ… እስቲ እንዮት!… ይድገሙ!… እስቲ ይሄ እንጉርጉሮዬ እውን እንዲሆን ይተብትቡ!”… የቀትር ጸሃዩ እንደወረደበት በትዝታ ይንከላወሳል ተስፋዬም ያስታምመዋል…
♪♪ እናናንዬ … እናናኔዋ …
እናናንዬ … እናናኔዋ …
ሰባት ሰዓት ሲሆን ከብት ውሃ ሲጠጣ፤
ደግሞ አገረሸብኝ ትዝታዬ መጣ።
አቤት ያንቺ ጸባይ ለፍቅር ሲመች፤
ድፍን የጎጃም ልጅ አለ ወይ እንዳንቺ። ♪♪
♪♪ እናናይ ነይ ነይ …
እናናይ ነይ ነይ …
ሃብትና ንብረትሽ ምን ያደርግልኛል?
ካንቺ ጋር አድሬ ብሞት ይሻለኛል።
ጨረቃ ስትወጣ ስትንቀለቀል፤
ላርግሽ ከደሬት እንደብር መስቀል።
እናናይ ነይ ነይ …
እናናይ ነይ ነይ … ♪♪
. . . እናና እያሉ የሚጠሯት እናቷ ሳይቀሩ ትዝ ይሉታል… ግልምጫቸው… ቁጣቸው… ኩርፊያቸው… አሽሙራቸው… ተረታቸው ሳይቀር እየተፈራረቀ ይመላለስበታል… ይህ የተፈጠረ ከንቱ እንቶ ፈንቶ… ይህ የተንሰራፋ አጓጉል ድንቁርና ወደሚሄድበት ሄዶ… ያመጣው ጋኔል በሚወጣበት ምሱ ወጥቶ… ዳግም ጎጃሚትን ሊቀበላት ይጓጓል… እንደሚሆን ደግሞ ጥርጥር የለውም!… ፍቅር ጥግ የለውማ!… ፍቅር አሸናፊ ነዋ!… ልክ ባለፈው እንደሆነው ተሰብስበው ሲመጡ ተሰብስቦ ሊቀበላቸው ይጓጓል… አበባ ይዞ ወደቀዬዋ ሲያደርሳት ይታየዋል…
♪♪ ደሞ አለው አበባ
ደሞ አለው አበባ
ጎጃሜው ሲገባ ♪♪
♪♪ ደሞ አለው አበባ
ደሞ አለው አበባ
ጎንደሬው ሲገባ ♪♪
♪♪ ደሞ አለው አበባ
ደሞ አለው አበባ
ወለዬው ሲገባ ♪♪
♪♪ ደሞ አለው ደስ ደስ
ደሞ አለው ደስ ደስ
አዲስ ላይ ስንደርስ ♪♪
. . . አዲስ መሄድ ያምረዋል… እዚህ እሷ የሌለችበት መንደር ውስጥ በትዝታ ከሚያላዝን የማንም ባልሆነችው ሸገር ላይ በባዱ ኪሱ መንሸራሸር ያምረዋል… “አፈር ምን ያደርጋል?… እርሻ ምን ይሰራል?… ንግድስ ምን ፋይዳ አለው?.. እኚህ ሁሉ ጥቅማቸው ትርጉም የሚኖረው በፍቅር ውስጥ አይደል እንዴ?!… ፍቅር ከሌለ ሁሉም የለም!… አለቀ… ደቀቀ!” ሊፈላሰፍ ይቃጣዋል… “ምድሪቷን የሰሯት ይመስል የኔ የኔ እየተባባሉ ይፋጃሉ… ከንቱዎች!… ይሄን ከንቱ ኮተታቸውን ወስደው ፍቅሬን በመለሱልኝ… ውቢቷ ጎጃሜን!… ድህነቴን የምታስረሳኝን ውዴን!” …
♪♪ ዓለም ዓለምዬ
ዓለም ዓለምዬ . . .
ሰላሌ ራስ ካሳ ቢያስፈልጉ አጡሽ
ጎንደር አጼ ፋሲል ቢያስፈልጉ አጡሽ
ጎጃም ራስ ኅይሉ ቢያስፈልጉ አጡሽ
ደቡብ ንጉስ ጦና ቢያስፈልጉ አጡሽ
የሸዋው ምኒሊክ ቢያስፈልጉ አጡሽ
ደሃ ቁርጠኛ ነው እኔ አገኘሁሽ ♪♪
. . . ቁርጠኛነቱን የሰለቡበትን… ተስፋውን ያደበዘዙበትን ሁሉ ይራገማል!… በፍቅራቸው ላይ የተጋረጠውን ጋሬጣ ከመፍታት ይልቅ “ውሻ በቀደደው ምን ይገባበታል” እንደሚባለው አይነት አጋጣሚውን ተጠቅመው የነፍሳቸውን ከንቱ መሻት እየፈተፈቱ የበለጠ ሊያቆራርጧቸው የሚማስኑትን ሁሉ የበለጠ ይራገማል… ከንቱዎች!
ልክ እሱ እዚህ ውቢቱ ጎጃሜን እንደሚያንጎራጉረው ሁሉ እሷም ፍኖተ ሰላም ላይ የምጽዋት ስንዴ እየተሰፈረላትም ቢሆን ዙምባራን እየዘፈነች እሱን እየናፈቀች እንደሚሆን ቅንጣት አይጠራጠረም… የዙምባራ ጭፈራዋ ሁሉ ይታየዋል . . .
♪♪ ይኸው ተነሳሁ
. . . ልሄድ አሶሳ
__ ሲኞር ከተማ ማማይ …
ዙምባ በሉማ … ዙምባ በሉማ …
ዙምባ በሉማ … ዙምባ ዙምባ …
ሸኙኝ ወደዛ
ትዝታው በዛ
__ ሲኞር ከተማ ማማይ ..
ዙምባ በሉማ … ዙምባ በሉማ …
ዙምባ በሉማ … ዙምባ ዙምባ …
.
.
.
ዙምባራ… ዙምባራ… ዙምባራ… ዙምባ… ዙምባ…
ዙምባራ… ዙምባራ… ዙምባራ… ዙምባ… ዙምባ…
ቤኒ… ቤኒ… ቤንሻጉል!…
ቤኒ… ቤኒ… ቤንሻንጉል!… ♪♪
ትታየዋለች!… ስትዘፍን… ስትጨፍር… ደግሞም የዘመን ኮተት ሲያስቆዝማት!… ይተካክዛል ተስፋው ግን አይደበዝዝም… የሱ አገር የሱ መንደር… ልቦናው ውስጥ ያለችው ፍቅር ናትና! . . .
. . .
ዙምባራና ጎጃም አንድም ሁለት ናቸው
የፍቅር ሰንሰለት ያስተሳሰራቸው
ማነው የሚበጥስ የልብን ቋጠሮ
ከአገር ይሰፋል ፍቅር እኮ ውሎ አድሮ::
. . .
______ // አብዲ ሰዒድ // _____