RSS

ያገለገሉ ፓንቶች ሽቀላ . . .

28 Apr

እዚህ እኔ ያለሁበት አገር አገልግሎት የሰጡና የተጣሉ ፓንቶች ይነገዳሉ!… ይሸጣሉ!… ይለወጣሉ!… ገንዘብ ያመጣሉ!… ቀልድ እንዳይመስላችሁ የምር ነው!… ንግድ ፈቃድ ማውጣት ሳያስፈልገው… ግብር እንዲከፍል ሳይገደድበት… የስራ ቦታ ማደራጀት ግድ ሳይለው በቀላሉ ገንዘብ ማግኘት የፈለገ የትኛውም ግለሰብ ያለማንም ከልካይ ወደ ፓንት ሽቀላ ስራ ሊሰማራ ይችላል… 

ለዚህ ስራ የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር ቆራጥነት ብቻ ነው!… በየጎዳናው የሚገኙ የሕዝብ ቆሻሻ መጣያ ሳጥኖችን እየከፈቱ ፓንት ለመፈልግ የሚያስችል ቆራጥነት… ከየቆሻሻ ዉስጥ የሰበሰቧቸውን ፓንቶች በፌስታል፣ በቦርሳ አልያም ባመቸ ነገር ቋጠር አድርጎ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ቆራጥነት… በየገበያ ማዕከሉ በተተከሉ የፓንት መግዣ ማሽኖች ፓንቶቹን አንድ በአንድ እየደመሩ ለመክተትና ደረሰኝ ለመቀበል የሚያስችል ቆራጥነት… ምናልባት ማሽን የተፋቸውና ቃርዳ የወጡ ፓንቶች ቢኖሩ አሊያም ፓንት ሳይሆኑ ከፓንት ጋር ተደባልቀው የተሰበሰቡ ቢያጋጥሙ እነሱን በአግባቡ ወደቆሻሻ ማስወገጃ ሳጥኖች ለመጣል የሚያስችል ቆራጥነት… 

እንግዲህ ይህ ቆራጥነት ያለው ማንኛውም ሰው ዛሬዉኑ የፓንት ስራን መጀመርና ሽቀላውን ማጧጧፍ ምርጫው ነው… ለበለጠ ውጤታማነት በሳይክል አሊያም መሰል ተሽከርካሪ መንቀሳቀስ ይመከራል… የበዙ የቆሻሻ መጣያ ሳጥኖችን ለማዳረስ ከማስቻሉም በላይ ፓንቶቹን በቀላሉ ለመያዝ ያመቻልና … 

“አበስኩ ገበርኩ ጌታዬ!… ምኑን ታሰማኛለህ!”… “የተጣሉ ፓንቶች ንግድ?!… ፓንትም ደግሞ ሊለበስ?!”… “ሆሆ ጆሮ አይሰማው የለ መቼም!”… “ወይ ጉድ!… ጉድ እኮ ነው!”… “አኡዙቢላሂ!… ኧረ ይሄስ ስራ ተብሎ አይወራም!”… “አቦ ንካው እንዲህ አይነት ሂራር አታውራብን!… ወላ ሳይሰራ ቢቀርስ!”… እና መሰል ግርምቶች እየተባሉ ሊሆን ይችላል… ግን ስራ ነው!… ፈረንካው ይሸቀልበታል… 

ባንግላዴሹ… ፓኪስታኑ… ህንዱ… ካሜሮኑ.. ጋናው… ናይጄሪያው… ታይላንዱ… ፖላንዱ… ፊንላንዱ… ስፓኞሉ… ስውዲኑ… ኖርዌዩ… ቱርኪው… እና ሌሎች በርካቶች ፈታ ዘና ብለው ለቀማቸውን በጠራራ ጸሃይ ሲያቀላጥፉት ቀብራራው የሃበሻ ልጅ ግን እምብዛም አይደፍረውም…. ታጥቦ ታጥኖ ደጁ ላይ የተከመረው ቆሻሻ ልብሱን እንዳያበላሽበት እየዘለላት ያደገው ኩሩው የኢትዮጵያ ልጅ ግን ይህችን ይህችን አይነት ስራ ንክችም አያደርጋት!… እንደው አልፎ አልፎ አፈንጋጭ ካልተገኘ በስተቀር!…

“ዘ ይግረም ነገር እኮ ነው!”…. “አጃኢበ ረቢ!”… ምናምን ብላችሁ ሳትጨርሱ ካፋችሁ ልንጠቃችሁና ልቀጥል… 

ፓንት ሲባል እኛ በለመድነው እና በምናውቀው አማርኛችን እንደሚገባን የውስጥ አልባስትን የሚገልጽ ቃል አይደለም… ፓንት ባገርኛው ቋንቋ የታሸጉ መጠጦች ከተሸጡና ከተጠጡ በኋላ እቃዎቹ ለዳግም አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ያላቸው ዋጋ ማለት ነው… 

ባብዛኛው የታሸጉ መጠጦች የዳግም አገልግሎት ዋጋ አላቸው… የተለያዩ አይነት ለስላሳ መጠጦች… ቢራዎች… ዉሃዎች… ቫይታሚኖች… ጁሶች… ኢነርጂዎች… እና መሰል መጠጦች እሽጋቸው ላይ የፓንት ዋጋቸው ተጽፏል… እንደው ለምሳሌ ብንወስድ አንድ ባለ ሁለት ሌትር ኮካ ኮላ ገዝተን ከተጠቀምን በኋላ ኮካውን ይዞ የነበረው ፕላስቲክ ማሸጊያ በሁለት የስውዲን ክሮኖር (ወደ 6 ብር ገደማ) ይሸጣል… እና ይህ ነው ፓንት ማለት… የተጠቀሙበት ማሸጊያ ላይ PANT የሚል ጽሁፍ ከዋጋ ጋር ከተለጠፈበት ይሸጣል…. ወደ ገንዘብ ይለወጣል… ፕላስቲክም… ቆርቆሮም… ጠርሙስም ሊሆን ይችላል… 

የኔ ቢጤ ቋጣሪ የሆነ ሰው የጠጣባትን እቃ እቤቱ እያጠራቀመ ሰብሰብ አድርጎ ይሸጥና አስቤዛውን ሊሸማምትበት ይችላል… እንዴ ገንዘብ ነዋ!… መጀመሪያ ተከፍሎበታላ!… ገንዘብ እንዴት ይጣላል?… ወላሂ ሃራም ነው!… እንዲህ የማጠራቀም ትግስቱም ፍላጎቱም የሌለውና በየአጋጣሚው መንገድ ላይ ገዝቶ የሚጠቀመው ግን በየቆሻሻ መጣያው ይጥላቸዋል … ፓንት ሸቃዩ ደግሞ እያሳደደ ይለቅማቸዋል… ከዚያም ወደ ማሽኑ ያስገባቸዋል… ማሽኑም ደረሰኝ ይተፋለታል… በደረሰኙ ያሻውን መግዛት አልያም ፈረንካውን መቀበል ምርጫው ነው… 

በነገራችን ላይ ማሽኑ የእርዳታ አማራጭም አለው… የፓንቱን ገንዘብ መውሰድ የማይፈልግ ፓንቶቹን አምጥቶ ማሽን ውስጥ የሚጨምራቸው እቃው ለዳግም አገልግሎት ይውል ዘንድ ያለበትን ሃላፊነት ለመወጣት እንጂ ለገንዘብ ሽቀላ ካልሆነ… ለተራቡ… ለተጠሙ… እና ለተቸገሩ ህጻናት መርጃ ይውል ዘንድ ማበርከት ይችላል… ፓንቶቹን አስገብቶ ሲጨርስ የቢጫዋን በተን መጫን ብቻ ነው የሚጠበቅበት!… የረዳውን የብር መጠን የሚገልጽ የምስጋና ደረሰኝ እጁ ላይ ይወድቅለታል…. ግለሰቡም አከባቢውን ከቆሻሻ ታድጎ እግረ መንገዱንም የተቸገረን ህጻን ረድቶ ይመለሳል…. 

ዋናው ጉዳይ ለሸቃዩ የሚያስገኘው ገንዘብ ብቻ አይደለም!… ከአካባቢ ብክለት የጸዳች ከተማን ለመስራት ያለው አስተዋጽኦም ጭምር እንጂ!… ቸልተኛው ቢጥለው ገንዘብ ፈላጊው ያነሳዋል… በአግባቡም ለዳግም አገልግሎት እንዲውል ያደርገዋል… ከዚያም ለዚህ ጉዳይ በተሰማሩ ባለሙያዎችና ማሽኖች ታግዞ ይጨፈለቃል… ይቀጠቀጣል… ዳግም ይሰራል!… ጠርሙስ፣ ፕላስቲክና ቆርቆሮ ነክ በሆኑ ቆሻሻዎች የበከተች ከተማ ማየትም ብርቅ ይሆናል… የሰለጠነ ቆራሊዮ ይሏል ይህ ነው!… 

ውይ ውይ አዲስ አበባዬ… ውይ ውይ መርካቶዬ… ውይ ውይ ፒያሳዬ… ውይ ውይ ካዛንቺሴ… ውይ ውይ ኢትዮጵያዬ!…. እናንተስ መች ይሆን እንዲህ ያለው ወግ ደርሷችሁ የማየው ስትል የግድህን ትጠይቃለህ… 

አቦ እንዲህ ሰልጠን ያሉ ቆራሊዮዎች ይኑሩን… ይምጡልን… ድንገት የማናውቃቸው ካሉም ይታወቁ… ይንቀሳቀሱልን… አካባቢያችንን ከብክለት… ከተማችንንም ከቆሻሻ ይታደጓታልና!
Image

ሰላም! 
አብዲ ሰዒድ

 
Leave a comment

Posted by on April 28, 2013 in ስብጥርጥር

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: