እስቲ ዝም በል አፌ!
__ አንዲትም ቃል አታውጣ
ከንቱ ነገር እያራገብክ
__ ከንቱነቴን አታሳጣ::
*
አይኔም ተው አትቆጥቁጠኝ
__ እባክህ አትፍሰስ እምባዬ
አለ ሲሉት የለም ነው
__ ሰው የመሆን እጣዬ::
*
ጆሮዬም ተወው ይቅርብህ
__ እስቲ አትለቃቅም ወሬ
ደግሞ ጨርሳ እንዳትጠልቅ
__ ያዘቀዘቀች ጀምበሬ . . .
*
ልቤም ተው አተክዝብኝ
__ ግድ የለም ሃዘን አታብዛ
አገር እንደሆን ሰው ነው
__ ፍቅር ነው ህዝብን ‘ሚገዛ . . .
*
ነፍሴ ሆይ ተሰብሰቢ
__ በይ ተነሽ ግቢ ሱባኤ
ጥሞና ነው የሚበጅሽ
__ ከራስሽ ጋር ጉባኤ . . .
*
መሄድ መምጣት ነው ዓለም
__ እንደዚህ ነው ተፈጥሮ
ቀናውን መሻት ነው ደጉ
__ የነፍስን ፅናት መርምሮ . . .
___ // © አብዲ ሰዒድ // ___
ተጻፈ: ነሐሴ፣ 2004 E.C
ኡፕሳላ፣ ስውዲን።