RSS

ትንሽ ማስታወሻ . . .

03 May

ቀደም ብሎ ኃይለ ማርያም ይሰኙ የነበሩት በኋላም ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የተባሉትና በኢትዮጵያ የሰላሌና የዎሎ ጳጳስ የነበሩት የነጻነት ታጋይ አባት ላመኑበትና ለቆረጡበት አላማቸው ሕይወታቸውን የሰዉበትን የጀብዱ ታሪክ ለመዘከር ብሎም በነዚያ አምስት ዓመታት (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1928-1933) የጣልያን ቆይታ ኢትዮጵያችን ያለፈችበትን ውጥንቅጥ… የባንዳና ያገር ወዳድ ምጥ… የሻጭና ያሻሻጭ እሽቅብጥብጥ… የሃቀኛና የእውነተኛን መንጓጠጥ… ከ5 ዓመት የግዞት ኑሮ መልስ በኃላ የነበረውን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መልመጥመጥና መቁረጥረጥ… ብሎም ብዙ መሰል ታሪኮችን ሲያስታውሰን የኖረው የአቡነ ጴጥሮስ መታሰቢያ ሐውልት ተነሳ… (ፈረሰ አላልኩም!… መነሳትና መፍረስ በጣም የተለያዩ ናቸው።)

እናም ትንሽ ምልልስ ከጸጋዬ ገብረ መድህኅን “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” ከተሰኘ ተውኔት ላይ ብንቆነጣጥርስ… ይህ ምልልስ በእስር ላይ የሚገኙት አቡነ ጴጥሮስና ለጣሊያን አድሮ እጃቸውን እንዲሰጡ የሚያግባባቸው ግርሻ የሚያደርጉት ነው።

ልብ በሉ እኔ እንደመሰጠኝ ቆነጣጠርኩት እንጂ ምልልሱ ሙሉ አይደለም… እናም ሙሉ ታሪኩን ትረዱት ዘንድ ”ጴጥሮስ ያቺን” ሰዓት የተሰኘውን ተውኔት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2003 ከታተመው የጸጋዬ ገብረ መድኅን ታሪካዊ ተውኔቶች መጽሐፍ ላይ እንድታነቡ ይመከራል።

ኃይሉ:
. . . ስለዚህ ልጄ ካንተም ሆነ ያገር አዛውንት ካልካቸው ጋር ያው እንደግራዚያኒ መቸጋገር እንጂ መመካከር አይኖረንምና ፍቃድህ ሆኖ የመጨረሻ ሰዓቴን በግል እንዳሳልፋት ለጊዜው ብቻዬን ተወኝ።

ግርሻ:
አባቲላ ለምን ቸኰሉ? ገና ለዘለዓለሙ ዓለም ብቻዎን ይሆኑ የለም?

ኃይሉ:
እሱንም ቢሆን እናንተ ወስናችሁልኝ ሳይሆን እኔ መርጨ ነው ልጄ።

ግርሻ:
ለርስዎ እንጂ ለሌላውማ እንዳይመርጡ አቅም የለዎትም።

ኃይሉ:
ለራሱ ለመምረጥ አቅም ያጣ እንኳን ተስፋ የተስፋ ጭላንጭል አይኖረውም። መሳሪያነቱ እንኳን ጭለማ እንጂ ብርሃንነት የማይኖረው፣ ጨዋ ወገኑን እንስሳ በማስደረግና፣ የተስፋቸው ጮራ ፍንጣቂ መሆኑ ቀርቶ፣ የተስፋቸው አሽቃባጭ ጥንብ-አንሳነት ብቻ ነው እሚተርፈው።

ግርሻ:
እኔስ በጄ፣ ለኔስ በጄ እንደምንም፣ እንደማናቸውም ለራሴ ልኑርለት፣ ከሞት ማዶ ያለ ተሥፋ የራዕይ ወይም የባለመለኰት ጠባይ ነውና ራሴን አላመጻድቅም።

ኃይሉ:
ትህትናህ ከግብዝነት እንጂ ከመንፈሣዊነት እንዳልፈለቀ ላንተ እንደሚታወቅህ እኔንም ያጠራጥረኛል። ይሁንና ከሞት ማዶ ያለ ተስፋ የራዕይነት ብቻ ሳይሆን የህይወትነትም፣ የሥጋዊነትም ጠባይ አለው ልጄ፣ ድፍን በድፍን እንቁላል ካልተፈረከሰ በዉስጡ ያለው አዲስ ህይወት ብር ትር ብሎ አይበርም። የስንዴ ፍሬ ወድቃ ካልበሰበሰች በቀር አታፈራም፣ አትበዛም። መውደቅና መሞት የሚያስተላልፈውን፣ የሚያፈራውን የተሥፋ አይነት መች አጣኸው?
የንፍገትና የስስት ኑሮህን እምታባብልበት ዘዴ፣ የምታሸንፍበት ልቦና አጥሮብህ ነው እንጂ።

ግርሻ:
ሞትማ ተሥፋ ከሆነ፣ ስንቱ ሽፍታ ሞቶ የለ፤
ተሥፋ ያለ በመግባባት ነው፣ በሕይወት ነው ተሥፋ ያለ።

ኃይሉ:
ያንተ ብጤው ሕይወት ለሕዝብ ተሥፋ የሞትነት መሣሪያ ነው።
የነሱ ብጤው ሞት ለሕዝቡ ተሥፋ የሕይወትነት መሣሪያ ነው።
ባላንጣን በተሥፋና በጦር መሣሪያነት እንጂ በልምምጥ፣ በእምባ ያሸነፈ የለም።

ግርሻ:
አቅም ያጣ ቢለማመጥ ተግባባ፣ ተመካከረ ነው እንጂ ባነባ ተለማመጠ አይደለም እሚባል። መግባባት የደከመ ወገን ውል ነው።

ኃይሉ:
ባሪያን በፈንጋዩ መሃል ደፍቶ መግዛትና መገዛት እንጂ ሌላ ምን ውል ሊኖር?

ግርሻ:
ትርጉም ሁሉ እንየአስተያየቱ ነው እሚራባ አባቴ። በቃል ኪዳንና በውል የሠፈረ ፊርማ ግን በሕግ የጸደቀ የተረጋገጠ የእውነት ፍሬ ነው።

ኃይሉ:
የተረጋገጠ የእውነት ፍሬ ቃል-ኪዳን? የማን እውነት? የማን ቃል-ኪዳን? ያንተ እውነት? ወይስ የኔ እውነት?

ግርሻ:
የጋራችን እውነት። የውላችን እውነት።

ኃይሉ:
ጠፊ ካጥፊው ከተዋዋለ መጥፊያውን አፀደቀ እንጂ ተዋዋለ አይባልም።

.
.
.

/ጥሩምባ/

. . . አቡነ ጴጥሮስ የተባሉት፣ በገናናው የኢጣሊያ መንግሥት ላይ ስለሸፈቱ፣ በሞት ይቀጣሉና ነገ ጠዋት ባምስት ሰዓት፣ አራዳ ጊዮርጊስ ቤተስኪያን አጠገብ እንትሰበሰቡ ተብላችኋል። . . .

.
.
.
/ጥሩምባ/
. . . አቡነ ጴጥሮስ የተባሉት፣ . . .
.
.
.

ምንጭ:
ታሪካዊ ተውኔቶች፣ ጸጋዬ ገብረ መድኅን
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ፣ 2003 E.C

Image

 
 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: