RSS

. . . / የግራ ገቡ ደብዳቤ / . . .

04 May

ይህ ጽሁፍ አንድ ግራ-ገብ ግለሰብ የጻፈው ነው… ብዙ ነገሮች ግራ ግብት ቢሉት ግራ በተጋባች መጣፊያው ግራ ገብ ጥያቄዎችን ሊያነሳ ወደደ!…

እናንት የገባችሁ ተመራማሪዎች!… እናንት ያልገባችሁ ተደናቋሪዎች!… እናንት ግራ የገባችሁ ተደናባሪዎች ሆይ!…. በየትኛውም አቅጣጫ ቀፍድዶ ከያዘን ጽንፍ አሳብ ነጻ ሁናችሁ የግራ ገቡን አሳብ በመልካምነት ትመለከቱ ዘንድ… ጥያቄዎቹንም በቀናነት ለመመለስ ትሞክሩ ዘንድ ትለመናላችሁ… መመለስ ፈቃዳችሁ ባይሆን እንኳ ለራሳችሁ ብታብሰለስሉት ግራ ገብነትን እንደመጋራት ይቆጠራል….

ልብ በሉ!… ይህ ግለሰብ ግራ የተጋባው የሚያስበው አጥቶ አይደለም!…. የሚጸናበት አቋም የሌለው ዋዣቂ ስለሆነም አይደለም!… ነገሮች የሚደባለለቁበት ቀዥባራ ሆኖም አይደለም!…. ይልቁኑስ ከዚህምም ከዚያም የሚወራወሩትን ቅጥ የለሽ ዘለፋዎችና ውል የለሽ መናቆሮችን አጥርቶ ማወቅ ስለፈለገ እንጂ!… ከመደናቆር መመካከር በሚል መንፈስ ስለተነሳሳ እንጂ!…

ይህን ግራ ገብ ግለሰብ ሃይማኖቱን አትጠይቁት!…. ማንን እንደሚያመልክ አትመርምሩት!…. ከየት እንደመጣ ለማወቅም አትጣሩ!… ዘር ማንዘሩንም ለመቁጠር አትድከሙ!… “እንዲህ የሚያስበው የእንትን ፓርቲ አባል ስለሆነ ነው!… የነእንትና ደጋፊ ስለሆነ ነው!…. እነ እንትናን ስለሚጠላ ነው!”… ምናምን ብላችሁ በራሳችሁ መነጽር ለማየትም አትልፉ!… በመላ ምት ለመደምደምም አትጣደፉ!…

ይህ ሁሉ ኮተት አሳቡን ለመረዳትም ሆነ ጥያቄዎቹን ለመመለስ አያስፈልግም!… ግራ ገብነቱን ቢያባብሱት እንጂ አይቀንሱትምና!…. እናም ዝምምምም ብላችሁ ብቻ ግራ መጋባቱን ተረዱለት!… በቀናነት ሰው የመሆን መንፈስ ብቻ ተሞልታችሁ ጥያቄዎቹን መልሱለት… ልትመልሱ ካልቻላችሁም በባዶ ከመዘባረቅ ዝምታ ወርቅ ነው።

ጥያቄዎቹም ሆነ አሳቦቹ በሰሞኑ ከተነሳው የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት እና ከባቡር መንገድ ዝርጋታው ጋር ይያያዛሉ . . .

ከሐውልቱ መነሳት ጋር ተያይዘው ለተፈጠሩት መነታረኮች… መበጣበጦች… እና ግራ መጋባቶች ዋናው ተጠያቂ መንግስት እንደሆነ ግራ ገቡ ያምናል። ጥርት ያለ መረጃ ቀድሞውኑ በአግባቡ ተዳርሶ ቢሆን… አስፈላጊው ውይይት ከሕብረተሰቡ ጋር ተደርጎ ቢሆን… ቀደም ብሎ ባሳለፈው ታሪክ መንግስት ለታሪክና ለቅርስ ተቆርቋሪነቱን በጽናት አስመስክሮ ቢሆን… ይህ ሁሉ ያለመተማመን… ይህ ሁሉ መደበላለቅ… ይህ ሁሉ መቀበዣዠር ላይኖር ይችላል… በዚያ በኩል ብዙ ነገሮች እያጠፋ እያየን በዚህ በኩል ብዙ ነገሮች ሲያለማ ስናይ አናምንህም ብንለው አይፈረድብንም።

የምንግስት ችግሮች ዘርፈ ብዙ ናቸው… የመንግስት መልካም ስራዎችንም በብዛት እያየን ነው… እነዚህ ሁሉም በየመልካቸው ራሳቸውን የቻሉ መወያያ ጉዳዮች ናቸውና እዚህ አናደበላልቃቸውም።

ይሄ ጉዳይ ሐውልቱን ብቻ ስለሚመለከት እንጂ ሽሽት አይደለም!… አንዱን ችግር ከሌላው መልካም ስራ ጋር ማደባለቁ ግራ ከማጋባት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም!… እዚህ ላይ ግራ ገቡ የሚፈልገው ሙያ ነክ መልሶችን… የጋራ ጥቅምን የተመለከቱ ውይይቶችን እንጂ ከንቱ መደናቆርን አይደለም።

* * *
አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ነበሩ!… ብጹዕ አቡን ነበሩ!… ሐይማኖታዊ አባት ነበሩ!… ከነዚህም ጋር ተያይዞ የሚኖራቸው ሃይማኖታዊ ስልጣን ወይም ታላቅ የሆነ መለኮታዊ ቦታ ሊኖር ይችላል… ያ!… ሃይማኖታዊ ስለሆነ እዚህ ጋር አናመጣውም። ያ!… እምነቱ ለሚመለከታቸው ሰዎች ብቻ የሚያገለግል እንጂ የመላው ሕዝብ እውነታ አይደለምና ለዚህ ጉዳይ አያስፈልገንም።

አቡነ ጴጥሮስ የነጻነት ታጋይ ነበሩ!… አርበኛ ነበሩ!… ላመኑበት ሕይወታቸውን የገበሩ ባለውለታ ነበሩ!… የኢትዮጵያችን የቁርጥ ቀን ሰው ነበሩ!… የትግል አርማ ነበሩ!… ስንቱ ባንዳ አገሩን ሲሸጥ በአላማቸው ጸንተው ለበርካታ ታጋዮች አርአያ መሆን የቻሉ ታላቅ ሰው ነበሩ!…

“እምቢኝ አልገዛም!… እኔን እንደ አባት አምነው ለሚከተሉኝ ሕዝቦቼ የውድቀት ምሳሌ አልሆንም!” በማለታቸው ነው በግፍ የተገደሉት… ይህ ታሪካቸው ነው ሐውልት እንዲቆምላቸው ያደረገው…. በዚህ አኩሪ ታሪካቸው ማንም ነጻ ኢትዮጵያዊ እንዲያከብራቸው ይገደዳል!…. እዚህ ላይ ብቻ ነው ማተኮር የሚገባን… ለምንሰጠው ማንኛውም አስተያየት ከዚህ እይታ መውጣት ያለብን አይመስለኝም…. ሃይማኖትንና ታሪክን ማደበላለቅ እውነትን ከማጨመላለቅ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውምና።

የኚህን ታላቅ ሰው መታሰቢያ ሐውልት እንደማንም ተራ እቃ አንስቶ መጣል ይገባል… መንገድ እንጂ በመንገዱ ላይ በነጻነት እንድንራመድ ያደረጉን ባለታሪኮች ዋጋ የላቸውም…. ብሎ የሚከራከር ቢኖር አሳቡን ይመርምር!… ምልከታውን ይፈትሽ!….

በሌላም በኩል ደግሞ ጉዳዩን ከጽድቅ ጋር አያይዞ የእምነቱ ማራመጃ… የሃይማኖቱ ማካሄጃ… ከፈጣሪው ጋር መማለጃ… የሚያደርግ ስለ ሐውልቱ በተነሳ ቁጥር የማምለክ ያህል የሚጠበብ ቢኖር!…. እርሱም አሳቡን ይፈትሽ…. ምልከታውን ይመርምር….

እንዲሁም መንግስትን እንቃወማለንና…. አስተዳደሩን አንደግፍምና…. በዚህ ታሪካዊም ሐይማኖታዊም መልክ ባለው ሐውልት ተመርኩዘን ተቋውሟችንን እናራግብ… ብለው የሚንቀሳቀሱ ቢኖሩ አገርንና መንግስትን…. ወይም ፓርቲንና እድገትን ይለዩ!…. ራሳቸውንም ይፈትሹ!…. አሳባቸውንም ይመርምሩ!….

. . . ለእኛ ታሪኩም የሃዲድ ዝርጋታውም ያስፈልጉናል . . .

ታሪክ ብቻውን ዳቦ ሆኖ አይበላም!… የጦር ጀብደኝነት ብቻውን ርሃብና እርዛት ላይ ጀብደኛ ለመሆን አያስችልም!… ሃይማኖታዊ አምልኮ ብቻውን የእድገትና የስልጣኔን መና ከሰማይ አያወርድም!… ከጠኔ ለመውጣት ዋናው ጀብዱ ስራ መስራት ነው!…. ከጨለማ አስተሳሰብ ራስን አላቆ ዝም ብሎ መትጋት!… የተስፋ ብርሃን ተሞልቶ… ከጎጠኝነትን ተፋቶ… በጋራ መልፋት!…. ተግቶ የሰራ… በሕብረት የጣረ ሕዝብ የልፋቱን… የጥረቱን ዋጋ እንደሚያገኝ ግራ ገቡ ልቤ ያምናል።

የዛሬ መንገድና ህንጻ ብቻቸውን ቢገነቡ የድሮ ማንነታችንን እየናዱ ታሪክን እያጠፉ ሲሆንም ማደግ አይባልም!…. ማንነቱን የማያውቅ… ታሪኩን የዘነጋ… ባለውላታዎቹ ላይ የተኛ ትውልድ ለታናናሾቹ የሚያወርሰው ማንነት አይኖረውም…. ቢኖረውም የተበጫጨቀ እንጂ ሙሉ አይሆንምና!…. የአገር ማንነት ከትውልድ ትውልድ እየተቀጣጠለ የሚሰራ ብርቱ ሰንሰለት እንጂ በአንድ ቦታ ተወስኖ የሚኖር ግኡዝ የአደራ እቃ አይደለም። እናም ሁላችንም የመቀጣጠል ሃላፊነት አለብን!….

ነገር ግን ታሪክን እንዴት ነው የምናቆየው?…. በምን መልኩ ነው ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ህያው የምናደርገው?… ብሎ መጠየቁና መመካከሩ የሚያስፈልግ ይመስለኛል…

ጥንት አያቶቻችን ወይም አባቶቻችን ታሪክን የሚያቆዩበት መንገድና እኛ የምናቆይበት መንገድ ይለያያል… ነገ የሚመጣው ትውልድ ደግሞ በሌላ መንገድ ሊያቆያቸው ይችላል…. ዘመን ሲለዋወጥ ከዘመን ጋር የሚለወጥ… ከትውልድ አስተሳሰብ ጋር አብሮ የሚዘምን ታሪክን የምናቆይበት መንገድ ከሌለን ወይም እንዲኖረን ካልተጋን እንዲሁ እንደተጯጯህን ብዙ ነገሮች እናጣለን… ብዙ ታሪኮችም ይባክናሉ።

“በበኩሌ የሃዲድ ዝርጋታውን አልቃወምም!… ከተማችን ባቡር ቢኖራት አልጠላም!… እድገትን ማን ይጣላል?… ግን ለምን ሐውልቱን እንዳይነካ አልተደረገም?… ካልጠፋ መንገድ በሐውልቱ ላይ ማስኬድ ምን ይባላል?!… ታሪክን ማጥፋት እንጂ!…”

የሚሉና መሰል ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይጠየቃሉ… ምንም አይነት ድምዳሜ ላይ ባልደርስም ጥያቄዎቹን እጋራቸዋለሁ… ለምን በዚያ መንገድ አለፈ?… ወይም ለምን እንዳይነካው አልሆነም?… ለሚለው ጥያቄ ግን ሙያዊ ምላሽ ያስፈልጋል…

በበኩሌ ለመንገድ ዝርጋታም ሆነ ለባቡር መስመር ዝርጋታ ሙያ መሃይም ነኝ። ቅንጣት የሆነች የዲዛይኒንግ ወይም መሰል እውቀትም የለኝም!… ግን ሙያው እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ እንደሆነ ይሰማኛል!… እናም “ይቻላል!… አይቻልም!” ማለት አይቻለኝም። በዚህ አጋጣሚ ይህችን ጥሁፍ ድንገት የሚያነባት የዘርፉ ባለሙያ ቢኖርና ከየትኛውም ጽንፍ ነጻ ሆኖ ወይም ሆና ሙያዊ ማብራሪያ መስጠት ቢቻል ግራ ገብነትን መታደግ ብቻ ሳይሆን ለከተማችን እድገትም አስተዋጽኦ ማድረግም ነው. . .

ለመሆኑ መንገድ እንዴት ነው የሚቀየሰው?… የባቡር ሃዲድስ እንዴት ነው የሚዘረጋው?… የከተማ ፕላንስ እንዴት ነው የሚሰራው?… ለዘመናት የኖረች ከተማ ስትታደስስስ እንዴት ነው መታደስ ያለባት?… እኚህ ሁሉ የባለሙያን መልስ የሚሹ ጥያቄዎች እንጂ እንዲሁ በዘፈቀደ የሚዘባረቅባቸው ጉዳዮች አይመስሉኝም….

እስከዚያው ግን የሚመላለሱብኝን ጥያቄዎች እጠይቃለሁ…. የማያውቁትን መጠየቅ እውቀትን ከማስጨበጡም በላይ ከንቱ መደናቆርን ይቀንሳል…. እናም ጥያቄዎቹን ብቻ ትመልሱ ዘንድ በድጋሚ ትለመናላችሁ…

. . . 1 . . . ሐውልቱን እንዳይነካው ስንል እንዲቀየስ የምንፈልገው መንገድ የሌላውን መስመር ዝርጋታም የሚያጣምመው ቢሆንስ?

. . . 2 . . . ሐውልቱን እንዳይነካና በሌላ መስመር እንዲዘረጋ ስንፈልግ ፒያሳ የባቡር ሲሳይ እንዳታገኝ የሚያደርጋት ቢሆንስ?

. . . 3 . . . ሐውልቱን እንዳይነካ ስንል የምንከልሰው ፕላን የአዲስ አበባን ከተማ ማስተር ፕላን የሚረብሸው ቢሆንስ?

. . . 4 . . . የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት የቆመበት ቦታ እዛች ቦታ ላይ በግፈኛው የጣልያን ጦር መሪ ትእዛዝ እንዲረሸኑ ስለተደረገ እንጂ ከአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን አንጻር ሲታይ ቦታው የመንገድ እንጂ የሐውልት ማቆሚያ ባይሆንስ?… መንገዱ ይቅርብን ሐውልቱ ይኑልን ልንል ነው?…

. . . 5. ሐውልቱ ለዝርጋታው ተነሳ እንጂ አልፈረሰም አይደል?… አያስፈልግም ተብሎ አልተጣለም አይደል?… እና ምንድነው ችግሩ?… ከዝርጋታው በኋላ መልሶ መትከል እንደማይቻል የሚገልጽ መረጃ አለ?… በመሃል ለተነሳበት ጊዜ ከሆነ መልሶ ሲተከል ለምን ተነስቶ እንደነበረ መጻፍ አይቻልም?….

ደግሞስ ለምንድነው ተመልሶ አይተከልም ብለን ገና ሳይደርስ የምንደመድመው?… በመንግስት ላይ ያለን እምነት በመውረዱ ከሆነ አንድ ነገር ነው… አይ የለም “አይቻልም!” ተብሎ ታስቦ ከሆነ ግን አልስማማም… የተባለው ዝርጋታ በትክክል የሚከወን ከሆነ ምንም የሚከብድ አይመስለኝም!… ምንም እንኳ የዘርፉ ባለሙያ ባልሆን ባጋጣሚ ያየኋቸው ከተሞች ከአንድም ሁለት ሦስት ደረጃ የወረደ የምድር ለምድር ባቡር ከስራቸው እየተምዘገዘገ ላያቸው የደራ ከተማ ነው… አይደለም አንድ መታሰቢያ ሃውልት መመለስ ቀርቶ ከስር ባቡር እየሄደ ከላይ ሕንጻ መገንባት ይቻላል… ያ ስልጣኔ ብርቃችን ቢሆንም!… ስናሳዝን!… 😦 …

እነዚህን ጥያቄዎች የምጠይቀው ግራ ገብነቴን ለማጥራት እንጂ ለሌላ አይደለም.!… እስካሁን ባጋጣሚ የምጠይቀው ሁላ “ይቻላል ለምን አይቻልም!… ክፋት እንጂ!” እያለ ከመፎከር የዘለለ ሙያዊ ማብራሪያ የሰጠኝ አልገጠመኝም…

በቻይና የሆነ መንገድ መሃል አስፓልት ላይ በካሳ ክፍያ አለመስማማት ምክኒያት የተደነቀረ የአረጋዊያንን ቤት… የሆነ በረሃ መሃል ያለች ዛፍን እንዳይነካ የተጣመመን መንገድ…. እና መሰል ምስሎችን ከማሳየት በዘለለ “ይሄ እንደዚህ ነው… መንገድ ሲሰራ እንዲህ ነው!… የባቡር ሃዲድ ሲዘረጋ እንዲህ ነው!…. የአዲስ አበባ ፕላን እንዲህ ነው!… ስለዚህ በዚህ በኩል ቢያልፍ ጥሩ አማራጭ ነበር…” የሚል እውቀትን መሰረት ያደረገ… ማደግን መበልጸግን ከመመኘትና አብሮም ታሪክን ከማቆየት ጋር ያለውን ፋይዳ የሚገልጽ ሰው አልገጠመኝም… እንዲህ ያለ ጽሁፍም አላየሁም!…. ያጋጣምችሁ ካላችሁ ብታካፍሉኝ እጅጉን አመሰግናለሁ . . .

በበኩሌ ይህንን ጉዳይ አበክሬ የማነሳው ከሃይማኖትም ከፖለቲካም አንጻር አይደለም!… ይልቁንም አዲስ አበባዬን ከአንድም ሁለት ሦስቴ ከላይ ወደታች ቁልቁል ሳያት የተሰማኝን የተደበላለቀ ስሜት እያስታወስኩ እንጂ…

ብዙ ነገሯ የተዘበራረቀ!… መንገዷ የተጣመመና የተሽሎከለከ… ህንጻዎቿ አንድ አካባቢ በስርአት ሌላ አካባቢ ደግሞ ያለ ስርአት እዚም እዛም የተተከሉባት… ያን ተከትለው ለዛ የሌላቸው መብራቶች አንድ ቦታ እንደ ችቦ የሚደምቁባት… ሌላ ቦታ እንደ ኩራዝ ጭል ጭል ጭል የሚሉባት… የመኪናውና የእግረኛው መንገድ የማይታወቅባት… የአታክልቱ ስፍራና መኖሪያ ቤቱ የማይለይባት… የልጆች መጫወቻውና የኳስ ሜዳው የማይታወቅባት… ዝም ብላ በዘፈቀደ የምትወናበድ… ዝም ብላ በዘፈቀደ የምትወላገድ ከተማ ሆና ስላገኘኋት ነው።

… የምር ታስጠላለች!… ማስጠላት ብቻ ሳይሆን የከተማ መልክ ስለሌላት ትጨንቃለች!… ለካ ከከፍታ ነው መልክ የሚታይ!… ለካ ከሰማይ ነው ውበት የሚለይ!… ውይይይ አዲስ አበባዬ…

ከሌሎች ከተሞች የሰማይ መልክ ጋር ለማነጻጸር የሚቃጣው የኔ ቢጤ ጀዝባ ካለ ደግሞ ይታመማል!…. በበኩሌ ባጋጣሚ ካየኋቸው ከስቶክሆልም… ከሮም… ከአምስተስተርዳም… ከለንደን ጋር ላመሳስላት ሲቃጣኝ በጅልነቴ እስቃለሁ!… የምር ሰው ብቻ ሳይሆን ከተማም መልክ ያስፈልጋታል…. ታሪኳን ብቻ ሳይሆን… እድገቷን ብቻ ሳይሆን… ዉበቷንም ታሳቢ ያደረገ ውይይት… ውበቷንም ታሳቢ ያደረገ ግንባታ ሊደረግ ይገባል….

አዲስ አበባችን እንዲህ ለዛ ያጣችው… እንደዚህ መልከ ቢስ የሆነችው…. መንገዶችና ህንጻዎች “እንትንን እንዳይነኩ” እየተባለ ሲዘለሉና ተለዋጭ ሲሰራላቸው ስለኖረ እንጂ የከተማዋ ማስተር ፕላን ለዛ ቢስ ሆኖ አይመስለኝም!…. እና እዚህ ጋርም የምንለውጠው የበለጠ የሚያበላሻት ቢሆንስ?… ይህ ሁሉ እንግዲህ የማላውቃቸው ጥያቄዎች ናቸው… በባለሙያ የሚመለሱ!…

በመጨረሻም ታሪክን ለትውልድ ማቆየት የሚቻለው ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣና የዘመን ስልጣኔን መሰረት ያደረገ ውይይት በጋራ ሲካሄድ እንጂ አንድ ጽንፍ ላይ ተንጠልጥሎ ደሞ ከኔ ወዲያ ላገር አሳቢ ብሎ በመፎከር አይደለም እናም ጽንፋችሁን ተዉትና ኑ ስለጋራ ጥቅማችን በጋራ እንነጋገር . . .

ሰላም !
One Love !
_______ // አብዲ ሰዒድ // ________

 

Image

 
 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: