RSS

ወፍዬ በእኔ እይታ

18 May

ይህ ጽሁፍ በአበባየሁ መሰለ የተጻፈ ነው… ግጥሙ በገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ ስለተጻፈውና ድምጻዊ አበበ ተካ ጥሩ አድርጎ ስለተጫወተው ወፍዬ ዘፈን ይተነትናል… አንብቡትማ!… የምትሉትም ካለ አካፍሉን እስቲ ….

ወፍዬ በእኔ እይታ . . .  
(በአበባየሁ መሰለ (ዶ/ር) )

አብዲ እኔም እንዳንተ በወፍዬ የሰከርኩ የወፍዬ ዘካሪ ነኝ። ወፍዬን ስሰማ አንዲት ጠንካራ ሴት ያለማንም ድጋፍ ራሷን ችላ ኑሮ ቀልሳ ለመኖር የቻለች፤ ደጋፊ እንደሌላት አውቀው፤ ብቸኝነቷን አይተው ጉልበተኞች ያበሳቅሏት፤ በሽታ ላይ የጣሏት፤ ለልጁዋ ኖራ ለልጁዋ ያለፈችን እናት አይበታለሁ። ይህንን እይታዬን ከግጥሙ እየቆነጠርኩ ላስረዳ።

ወፍዬ …

♪♪ ጭራ ጭራ የምታድረው 
ጭራ ለቅማ የምታድረው
እንዲህ አስናቀችኝ 
ቀድማኝ ጎጆ ወጥታ ጎጆ አስተማረችኝ
ጎጆ አቤት ጎጆን ወፍዬ አስቀናችኝ . . .♪♪

እነዚህ ስንኞች የዚህች አናት ቀድማ ጎጆ መውጣቷ፤ ቀድማ ቤት፤ ኑሮ መመስረቷ፤ ለፍታ-ጥራ ግራ መኖሯ ያስቀናው (መልካም ቅናት)፤ የሷን ጥንካሬ ያስመኘው ልጇ የሚለውን ነው የሚነግሩን። ይህች እናት ግጥሙን ገጣሚው ሲጽፈው በሕይወት የለችም የሚል እሳቤ ይዤ ነው የተነሳሁት። ይህ ልጇ “ጎጆ” ብሎ የሚመስለው የምድሩንም የሰማዩንም ቤቷን ነው። ያንቺን ኑሮ በሰጠኝ ብሎ የሚመኘውም አንድም በምድር አንድም በሰማይ መሆኑን በተለያየ መልኩ እንመለከታለን። ይህንን ምኞቱንና ፍልስፍናውን በጥልቀት ከሚቀጥሉት ስንኞች መረዳት ይቻላል።

♪♪ምነው ባደረገኝ የሷ ጋሻ ጃግሬ
እንደምንም ብዬ እኔም ጥሬ ግሬ
ያገዳ ጎጆዬን ባቆምኳት ማግሬ . . . ♪♪

♪♪ አጉል በቃኝ ላይል አይን አይቶ ገምቶ
ወይ ሞልቶ ላይሰላ ጆሮ አይችሉ ሰምቶ
እንዴት ጎጆ ይቅር አርሶና ሸምቶ . . .♪♪

የሚቀጥሉት ስንኞች በተለይ የምድሩንና የሰማይን ኑሮ በሚያምር አገላለጽ ይሉታል።

♪♪ገመና ከታቹ የሳር ቤት ያማረሽ 
ሚስጥረ መለኮት ማነው ያስተማረሽ
ካፈር ክዳን ጎጆ መሬቱን ፈልፍሎ 
ከሰማይ ቤት እጣሽ ማን በሰጠኝ ከፍሎ♪♪

ምልከታዬን በተሻለ መንገድ ለማስረዳት ይረዳኝ ዘንድ በተለይ እነዚህን ስንኞች በቅርበት መመልከት ያስፈልጋል። ብዙዎቻችን እንደምናውቀው በተለይ በገጠር ቤቶች ከሳር ክዳን ነው የሚሰሩት–በተለምዶ “ጎጆ-ቤት”ብለን የምንጠራው ማለት ነው። “ገመና ከታቹን የሳር ቤት ያማረሽ” ሲል የ’ድሃ’ መቃብር አስከሬኑ በኩታና በሰኔል ይጠቀለልና ሳር ተጎዝዩዞበት ይቀበርና አፈር ከተመለሰበት በሃላ ሳር ይጎዘጉዝበታል። የ’ድሃ’ መቃብር ወለሉም ጣራውም ሳር ነው። ስለዚሀ ይህ ስንኝ ቢያንስ ሁለት ተምሳሌቶችን የያዘ ነው ማለት ይቻላል፡ አንደኛው-ምድራዊ ጎጆ ቤትን፤ ሌላኛው ግብአተ መሬትን ማለት ነው። በተለይ የገጣሚው ትኩረት፤ በእነዚህ ስንኞች ማለቴ ነው፤ የሰማዩ ኑሮ ላይ እንደሆነ የሚታየው የቤቷ አሰራር መለኮታዊ ይዘት እንዳለው ይገልጥና “ካፈር ክዳን ጎጆ መሬቱን ፈልፍሎ” “ከሰማይ ቤት እጣሽ ማን በሰጠኝ ከፍሎ” በማለት አንቺ በገባሽበት የአፈር ቤት ውስጥ እኔንም ማን ቢያስገባኝና እሰማይ ብንገናኝ የሚል አይነት አንድምታ ያስይዘዋል። 

እንዲያው ከላይ ብቻ ላነበበው ወፎች አፈር ጭረው ሰማይ ላይ የአፈር ቤት ይሰራሉ ብሎ እሱን ሊነግረን ነው ሊያሰኝ ይችላል። እርግጥ ነው የግጥሙ ተምሳሌት እሱን የተከተለ ነው፤ መዳረሻው ረቂቅ ይሁን እንጂ። የሚከተሉት ስንኞች ውስጥ ደግሞ የበለጠ የሰው ልጅ “ሩቅ ሃሳቢ ቅርብ አዳሪ” እንደሆነ (ብዙ እያሰበ ባጭሩ ሊቀጭ እንደሚችል) ልብ በሚነካ እንጉርጉሮ አይነት ለዛ ይነግሩናል።

♪♪ እኔን እኔን እኔን ይብላኝ
እኔን አይኔን እኔን ይብላኝ
የቀን ሰው ሌት አፈር
ልቤ ሩቅ አሳቢው ቅርብ አድሮ ሲደፈር
ምን ነበር ቢቆጨው ጎጆ አጥቶ ከማፈር . . . ♪♪

የሰውን ልጀ ላፍታ ታይቶ እንደሚጠፋ፤ ይህንንም ሃቅ “የቀን ሰው ሌት አፈር” “ልቤ ሩቅ አሳቢው ቅርብ አድሮ ሲደፈር” ብሎ ባዋቀራቸው ስንኞች እያዋዛ ከታሪኩ ጋር በውበት ይለውሰዋል። 

♪♪ ፈጣሪዋን አምና ያፏን ጥሬ ሰጥታ 
ለጭሮ አዳር ውሎ በዝማሬ ወጥታ
አዳኝ እንዴት ያጥቃት ፍርድና ዳኛ አጥታ . . . ♪♪

♪♪ አጣሁ ነጣሁ ብላ እንደሰው ባይከፋት 
ምፅዋት ባትለምን ተርፎን ባንደግፋት
ጎጆዋ ለቻላት ምን ነበር ባንገፋት . . .♪♪

እነዚህ ስንኞች አሁንም ከላይ ከላይ ላነበባቸው ገጣሚው ወፍ ጭጭጭ እያለች እየዘመረች ሳታርስ ሳታርም በፈጣሪዋ ተማምና ጭራ ልትበላ በጠዋት ወጥታ እረኛ ወይም ሰብል ጠባቂ አጠቃት የሚለን ይመስላል። እርግጥ ነው የግጥሙ አርዕስት “ወፍዬ” ነውና ተምሳሌቱ የወፍ ኑሮ ነው። ነገር ግን ጥቂት ጠለቅ ብለን ብንመለከት፤ ያቺ ከርታታ እናት በጠዋት “ፈጣሪዋን አምና ያፏን ጥሬ ሰጥታ” ይለናል። እሷ በፈጣሪዋ ተማምና ያፏን ጥሬ ሰጥታ–ጾማ–ያላትን ለልጅዋ አጉርሳ..ጭራ ልታድር እያመሰገነች ወጣች። ግና የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታልና ለፍታ ባደረች፤ ጭራ በኖረች ጉልበተኞች አላኖር አሏት፤ ደበደቧት በሽተኛ አደረጓት። 

♪♪ ታማ ትንፋሽ አጥሯት ደክማ ስታጣጥር 
ማን ያቃናት ይሆን ውለታ ሳይቆጥር
ወልዶ ማሳደጉን ብዙ ሰው ቢያውቅበት
ያፉን ማን ይሰጣል የ’ጁ ሲርቅበት . . . ♪♪

ብቸኛ ናትና ደጋፊ የሌላትምና ታማ ስታጣጥር እንኳ ውለታ ሳይቆጥር ውሃ የሚያቀብላት አጣች። እንደዛ እየማቀቀች ወጥታ ጭራ ራሷንና ልጇን መመገብ ተሳናት። እጅ አጠራት፤ አጣች። ቢሆንም ግን እሷ ትራብ እንጂ ልጇን ታጎርሳላች። ይህንን የእናትነትና የመሷዕት ውድነት በመጨረሻዎቹ ሁለት ስንኞች ሙሉጌታ ልብ በሚነካ አይነት ይገልጠዋል። ልብ እንበል አሁንም ስለወፍ አኑኗር ነው የሚነግረን። ወፍ ደግሞ በአፏ ነው የመትበላው በአፏ ነው የምታበላው። “ወልዶ ማሳደጉን ብዙ ሰው ቢያውቅበት” “ያፉን ማን ይሰጣል የ’ጁ ሲርቅበት . . .” ይለናል። ያቺ እናት እጅ አጥሯታል፤ አጥታለች፤ እጇን ዘርግታ መስጠት አልቻለችም፤ የእጇ ራቀባት፤ ከየት ታምጣ? የእጄ ራቀ ብላ ግን ልጇን አላስራበችም። የምትቆርሰው ብታጣ ራሷ ልትጎርሰው ያዘጋጀችውን ካፏ ላይ ወስዳ ልጇን ታበላለች። 

ታዲያ…ማን አለ እንደ ወፍዬ? ይህስ ልጅ አማዬ እዚህ አልተመቸኝም እዚያው ከሰማይቤት እጣሽ ማን በሰጠኝ ከፍሎ ቢል እናቱ ለሱ ምን እንደሆነች ማን ይረዳል? ወፍዬ ድንቅ እናት!

♪♪ ወልዶ ማሳደጉን ብዙ ሰው ቢያውቅበት
ያፉን ማን ይሰጣል የ’ጁ ሲርቅበት . . .???♪♪

ሙሉጌታ ተስፋዬ ተባረክ!

እንግዲህ ይህ የኔ እይታ ነው…እናንተስ ምን ትላላችሁ?

 

Image

 

 
Leave a comment

Posted by on May 18, 2013 in ስብጥርጥር

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: