RSS

የዓለም ፀሐይ ዓለም . . .

21 May

ዓለም ፀሐይ ወዳጆ . . .

alem1
አርቲስት ዓለም ፀሐይ ወዳጆን የማያውቅ የጥበብ ቤተሰብ ይኖራል ብዬ አልገምትም… ከኖረም ከቲያትሩም፣ ከትወናውም፣ ከዘፈኑም፣ ከግጥሙም ዓለም ራሱን ያራቀ… በስሚ ስሚ ወሬ እንኳን በኪነ ጥበብ ዘርፍ ነፍሱን ያላፀደቀ መሆን አለበት… ዓለም ፀሐይ ዘርፈ ብዙ የሆነች የጥበብ ፈርጥ ናት!… የተውኔት ጸሐፊ፣ የቲያትር አዘጋጅ፣ ተዋናይ፣ ገጣሚ ከመሆኗም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሕጻናት ቲያትር መስራች እንዱሁም በውጭው ዓለም በተለይም በአሜሪካ ኢትዮጵያዊ የጥበብ ስራዎች ከኢትዮጵያዊያን ልቦች እንዳይጠፉ በብርቱ የምትንቀሳቀስ የጥበብ አድባር ናት!… ጣይቱ የጥበብ ማእከልን ይጠቅሷል…

የሷን የጥበብ ስራዎች በሙሉ ልዘረዝር አልተነሳሁም!… ሁሉም በየመስኩ እንደመልካቸው ለየብቻ ሊዘርዘሩና ሙያዊ ትንተና ሊሰጥባቸው የሚችሉ ናቸው… ስለ ትያትር ስራዎቿ ለብቻ… በመጽሃፍና በሲዲ ስላሳተመቻቸው ግጥሞቿ ለብቻ… ለበርካታ ዘፋኞች ስለሰጠቻቸው የዘፈን ግጥሞች ለብቻ.. እያልን ከጥበብ ባሕሯ ልንጨልፍ ይቻለናል!… እናም ይህ ጽሁፍ ትኩረት የሚያደርገው የዘፈን ግጥሞቿ ላይ ብቻ መሆኑን መግለጹ ያስፈልገኛል…

አብዛኞቻችን ብዙውን ጊዜ ትኩረት የምንሰጠው ለዘፋኞች እንጂ ለግጥምና ዜማ ደራሲዎችም ሆነ ለአቀናባሪዎች አይደለም… በእርግጥ ዘፈን የድምጽ ስራ በመሆኑ ዘፋኙን ማወደስና ማክበር የተገባ ነው… አንድ ሙዚቃ ሙሉእ ሆኖ ቀልብን እንዲገዛ የሁሉም አስተዋጽኦ የየራሱ ዋጋ እንዳለው መዘንጋቱ ግን የጥበብን ውህደት እንደመዘንጋት ይቆጠራል… ዜማ ያለ ግጥም… ግጥምም ያለ ዜማ… ሁለቱም ያለ ጥሩ ቅንብር ለመንፈስ እርካታን የሚለግስ ዘፈን ሊሰጡን አይቻላቸውም… ሶስትም አንድም እንደማለት ነው… የማይነጣጠሉ!… ዓለም ፀሐይ የምትታወቀው ውስጥ ዘልቀው በሚገቡ ግጥሞቿ ነው… እናም ግጥም ላይ ብቻ ትኩረት አደርጋለሁ…

ከወራት በፊት ስለ ዘፈን ግጥሞቿ አወራኋት… ባጋጣሚ ውይይታችንን የቀረጽኩበት ድምጽ መቅጃ ከጄ ወጣ… በሲዲ አሊያም በሌላ መሰል ነገር አልገለበጥኩትም ነበርና ተበሳጨሁ… በድጋሚ ላውራሽ ማለቱ ደግሞ እሷን ማድከም እንደሆነ ተሰማኝ… እፍረትም ሸንቆጥ አደረገኝ… እናም መልሼ እስካገኘው መጠባበቅ ግድ ሆነብኝና እስካሁን ቆየሁ… መቼም ቅር እንደማትሰኝብኝ እምነቴ ነው… ከራሷ የሰማሁትን ለማጠናቀር ስለፈለግኩ እንጂ በተባራሪ የሰማኋቸውን እንዲሁም ካሴቶች ላይ ያየኋቸውን ለቃቅሞ መጻፍ እንደሚቻለኝ ዘንግቼው አይደለም… ጊዜዋን ሰውታ ስለ ስራዎቿ ስላዋየችኝ እጅግ እያመሰገንኩ ከራሷ አንደበት የሰማሁትን በራሴ መንገድ ለመነካካት እሞክራለሁ…. እጅግ ከባድ ቢሆንም…

ከ400 በላይ የዘፈን ግጥሞች . . .

ስለ ሙሉ የዘፈን ግጥሞቿ በዚህ ጽሁፍ ለመዘርዘር መሞከር የማይታሰብ ነው… ምን ያህል ግጥሞች ለምን ያህል ዘፋኞች እንደሰጠች በእርግጠኝነት ለመናገር ይቸግራታል… “የማታ እንጀራ” የተሰኘው የግጥም መጽሐፏ ሲመረቅ በድምጽ ባለሙያዎችና በጓደኞቿ ትብብር የተዘጋጀ ‘ሰርፕራይዝ’ አይነት ስጦታ ተበረከተላት… ስጦታው ሲታይ እስካሁን የሰራቻቸውን የዘፈን ስራዎች ያሰባሰቡ ሲዲዎች ነበሩ… በደስታና በአግራሞት መሃል ሆና አመስግና ተቀበለቻቸው… በኋላም ከ400 በላይ የዘፈን ግጥሞች ለ47 ዘፋኞች እንደሰጠች ተረዳች… ተገረመችም… ተደሰተችም… አመሰገነችም…

ምንም እንኳ ወዳጆቿ የቻሉትን ያህል ለማሰባሰብ ቢሞክሩም ሙሉ ነው ለማለት ግን አይቻልም… ምክኒያቱም በካሴት የመቀረጽ እድል ያላገኙ በድሮው ጊዜ በቲያትር ቤቱ የባሕል ክፍል ይዘፈኑ የነበሩ ዘፈኖችን ማካተት አልተቻለምና ነው… እንደ ምሳሌም የነ ጠለላ ከበደን፣ የነ ፀሐይ እንዳለን፣ የነ መልካሙ ተበጀን በካሴት ያልታተሙ ዘፈኖች መጠቃቀስ ይቻላል….

የሷን ግጥም ያልዘፈነ ዝነኛ ድምጻዊ ማግኘት ይከብዳል ከክቡር ዶክተር ጥላሁን ገሠሠ ጀምሮ እነ ማሕሙድ አህመድ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ፀሐዬ ዮሐንስ፣ ሻምበል በላይነህ፣ ዳዊት መለሰ፣ ኅይልዬ ታደሰ፣ ግርማ ተፈራ፣ ብዙአየሁ ደምሴ፣ ሰጠኝ አጣናው እንዲሁም ከሴቶች አስናቀች ወርቁ፣ አስቴር አወቀ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ በዛወርቅ አስፋው፣ አቦነሽ አድነው፣ ሂሩት በቀለ፣ ፋንትሽ በቀለ፣ አሰፉ ደባልቄ እያልን ከብዙ በጥቂቱ መጠቃቀስ ይቻለናል… የቻልኩትን ያህል በቀጣይ ለመነካካት እንደምሞክር ቃል እየገባሁ ላሁኑ ሙሉቀን መለሰ ላይ ብቻ ትኩረት አደርጋለሁ…

ሙሉቀን መለሰና የዓለም ፀሐይ ግጥሞች . . .

muluken
ሙሉቀን በተነሳ ቁጥር የዘፈኖቹን ግጥሞች ውበትና ጥልቀት… የተሸከሙትን መልእክትና ቁምነገር ያለማንሳት አይቻልም!… ዘመናችንን ሙሉ ካጣጣምናቸው ከአብዛኛዎቹ ድንቅ ግጥሞች ጀርባ ደግሞ ዓለም ፀሐይ አለች… ሙሉቀን በአብዛኛው የእሷን ግጥሞች ሲጫወት ነው የኖረው… “ሌቦ ነይ” ከሚለው የመጀመሪያ የካሴት ስራው ጀምሮ ዘፈን እስካቆመበት ጊዜ ድረስ የዓለም ፀሐይን ግጥሞች አዚሟቸዋል… ባጋጣሚ ሙሉቀንን ብታገኘውና “እንትን የሚለው ዘፈንህ ግጥሙን ማን ነው የጻፈው?” ብትለው ድንገት የሰጠውን ገጣሚ ቢዘነጋው አልያም በጊዜያዊነት ግር ቢለው በርግጠኝነት “ያው ዓለም ፀሐይ ትሆናለች” ብሎ ነው የሚመልስልህ….

ሙሉቀን እጅግ ውብ የሆኑ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎቹን ለኢትዮጵያ ሙዚቃ አበርክቶ ዓለማዊውን ዘፈን የተሰናበተና መንፈሳዊውን ዓለም የተቀላቀለ ብርቅዬ አርቲስት ነው… የቋንቋው ውበት… የአዘፋፈኑ ለዛ… የሚጫወታቸው ግጥሞችና ዜማዎች… ቅንብሮቹ… ብቻ በሁሉም የተዋጣለትና የተለየ ቦታ መቀመጥ የቻለ ድምጻዊ ነው… ዓለም ፀሐይ ራሷ ምንም እንኳ ስራዎቿን የተጫወቱላትን ዘፋኞች በሙሉ እንደየመልካቸው ብትወዳቸውም… ብታከብራቸውም… ብታደንቃቸውም… ለሙሉቀን ያላት ስሜት ግን ይለያል….

ሙሉቀን ቋንቋ አዋቂ ነው… ቋንቋን የማሳመር ተክኖ አለው… ዜማ መርማሪ ነው… አንድን ዘፈን የሚሰራው ብዙ ተጨንቆና ተጠቦ… ብዙ ዜማዎችን አጥንቶና መርምሮ… ብዙ ጊዜ ወስዶ… ከነፍሲያው ጋር አዋህዶ ነው… ጥድፍ ጥድፍ ያለ ጥናት አይወድም!… የተዋከበ ቀረጻም አይዋጥለትም!… ያልመሰለውን ቅንብር አይቀበለም!… በወቅቱ የነጋዴዎችን ተጽእኖ ተጋፍጦ ለጥበቡና ለስሜቱ ያደረ በሳል አርቲስት ነው!… በዚህም የኢትዮጵያ ሙዚቃ በቅንብር ረገድ እንዲያድግ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል… እነ ሙላቱ አስታጥቄን የመሳሰሉ ሊቅ አቀናባሪዎች ስራዎቹን ተግተው እንዲያቀናብሩለት ድርሻውን ተወጥቷል… በክፍያም ረገድ በዘመኑ ለዘፋኞች የሚከፈለው ክፍያ ከፍ እንዲል ፈር የቀደደ ነው…

ዓለም ፀሐይን የሚያበሳጫት አንድ ችግር ግን ነበረበት… ግጥሞቿ ውስጥ የባህል፣ የህዝብ፣ አሊያም ገጣሚያቸው በውል የማይታወቁ ስንኞችን እያመጣ ይጨምራል… አንዳንድ ዘፈኖቹ ላይ ግማሹ ግጥም የሷ ይሆንና ግማሹ የሌላ ይሆናል… ይህን ስራውን አትወድለትም!… “እንደዚህ አታድርግ ግጥሞቹን እንዳሻሽላቸው ከፈለግክ እራሴው ላሻሽላቸው እንጂ የሌላን አምጥተህ ስራዎቼ ውስጥ አትጨምርብኝ!” ብትለውም እሱ ከወደደና ካመነበት ያደርገዋል… ካሴቱ ከወጣ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ከፊቷ ይሸሻል… “እስቲ ጥይቋት… ምን አለች?… ተቆጣች?…” እያለ ይጠይቃል… በኋላም ስራው ይቀጥላል… እንዲህ አይነቶቹን ዘፈኖች በሙሉ ልብ የኔ ናቸው ለማለት አትደፍርም… ይህ ግን ባንዳንዶቹ ስራዎቿ እንጂ በሁሉም ላይ አይደለም…

በአብዛኛው ሙዚቃ አፍቃሪ እጅግ የሚወደዱት እነ “ገላዬዋ”… “ሰውነቷ”… “ወይ እዳዬ”… “አልዘገየሽም ወይ”… “ቁመትሽ ሎጋ ነው”… “መውደዴን ወደድኩት”… “ቁረጥልኝ ሆዴ” እና ሌሎች በርካታ ስራዎቹ የሷ ግጥሞች ናቸው… ጥቂት ስንኞችን ልቆነጣጥርና ለዛሬ ላብቃ…

1) ♪♪ ገላዬዋ ♪♪

♪♪ ገላዬዋ ነይ ነይ
ገላዬዋ ነይ ነይ
ሰው በገላው ውበት ይናፈቅ የለም ወይ♪♪

♪♪ ያይን ሽፋሽቷን ቅንድቧን አድንቁ
ጣቷን አስተውሉ ስትተዋወቁ
ዓይኗን ተመልከቱት እኔው ፈቅጃለሁ
ከኔው ጋር እያለ ሲዋሽ ይዤዋለሁ ♪♪

♪♪ አንገቷን አድንቁ መቃ ነው ብላችሁ
አካባቢ ሲቃኝ ታገኙታላችሁ
ቁጣ ግልምጫውን እችላለሁ ያለ
ጡቷን ቢመለከት ከልካይ አንድም የለ ♪♪

♪♪ ጥርሷን አሳስቁት ዝምታን አያውቅም
ፈገግታ በሷ ዘንድ ብዙ አያስጨንቅም
ዳሌ አቀማመጡን እዩት ለናሙና
እግሯን አትንኩብኝ መምጫዋ ነውና♪♪

♪♪ ገላዬዋ ነይ ነይ
ገላዬዋ ነይ ነይ ♪♪

2) ♪♪ ቁመትሽ ሎጋ ነው ♪♪

♪♪ ቁመትሽ ሎጋ ነው ሰንደቅ ያሰቅላል
የሰላም የፍቅር ምልክት ያሳያል ♪♪

♪♪ አሸን ክታብ ድሪ አልቦ ለቋ* ቀርቶ
ሽመል ሰውንተሽ ይታያል አብርቶ
ድሪውን ጠልሰሙን ገላሽ ባያደርግም
የፍኝ እኩሌታ ውበትሽን አይነፍግም ♪♪

♪♪ ለምድና ጎፈሬ ምን ይሆነኝ ብለሽ
ጌጤ መድመቂያዬ እራስ ወርቄ አንቺ ነሽ
የኔ በትረ ሙሴ መጥፎሽን አልወድም
ጠምበለል ነሽ ሎጋ ይህንን አልክድም ♪♪

♪♪ ቁመትሽ ሎጋ ነው ሰንደቅ ያሰቅላል
የሰላም የፍቅር ምልክት ያሳያል ♪♪

3) ♪♪ መውደዴን ወደድኩት ♪♪

♪♪ አንቺን መሳይ ቆንጆ ለኔ የሰጠኝን
መውደዴን ወደድኩት ያንቺ ያረገኝን
የኔ ያረገሽን መውደዴን ወደድኩት
ሳስብ ሳሰላስል ቆየሁ ከወሰንኩት ♪♪

♪♪ ሃር ከመሰለው ከጸጉርሽ ጀምሮ
እንከን የሌለብሽ ውብ ነሽ በተፈጥሮ
ትኩስ የፈነዳው ጽጌሬዳ ከንፈር
እስኪ አፍ ያውጣና ውብትሽን ይናገር ♪♪

♪♪ የሐረር መንደሪን የመስከረም አደይ
የሞጆ ብርትኳን የነሐሴ እንጉዳይ
ከንፈርሽ እንጆሪ ቀይ ጽጌሬዳ
ወፍ ጭጭጭ ሳይል ማልዶ የፈነዳ ♪♪

♪♪ አንቺን መሳይ ቆንጆ ለኔ የሰጠኝን
መውደዴን ወደድኩት ያንቺ ያረገኝን
የኔ ያረገሽን መውደዴን ወደድኩት
ሳስብ ሳሰላስል ቆየሁ ከወሰንኩት ♪♪

. . . በመጨረሻም እስቲ እናንተም የምታውቁትን ስራዎቿን ጻፍ ጻፍ አድርጉልኝ… ከዓለም ፀሐይ ጋር ያወጋነው ብዙ ነው… በቀጣይ ደግሞ ከሌላ ብርቅዬ ድምጻዊ ጋር ይዣት እመለሳለሁ… ረጅም እድሜ ላንቺ ዓለም ፀሐይ… ሰላም ለሁላችን!!!

ክብር ለጥበበኞች!
አብዲ ሰዒድ
2005 E.C

 
Leave a comment

Posted by on May 21, 2013 in ስብጥርጥር

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: