14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሊጀመር በአንድ እጅ ጣቶች የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተውታል… እኛም በአትሌቶቻችን ድል ልንሸልልና ልንፎክር አሰፍስፈናል… ይቅናቸው አቦ!… ይህ እንዲህ ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድነት የሚያስፈነድቀን የአትሌቶቻችን ድል በዓለም መለያችን ከሆነ ዘመን ውሎ አድሯል- እድሜ ለሯጮቻችን ብርታት!…
እስቲ አጋጣሚውን አስታከን ህያው ታሪክ እንቆንጥር!… ክቡር ስም እንዘክር!…
ከ50 ዓመት በፊት አበበ ቢቂላ የሮምን ማራቶን በባዶ እግሩ ፉት ሲላትና ሕዝቡን አጃኢብ ሲያሰኝ… 42 ኪሎ ሜትር ይቅርና 42 ሜትር የሮጠ በማይመስል መልኩ ሩጫ እንደሚጀምር አይነት ሰውነቱን ሲያፍታታ… ዘና ብሎ ዱብ ዱብ ሲል… ጎንበስ ቀናውን ሲያጧጡፈው ያዩት ሲደመሙ… “ምን ያለው ሰው ነው?… አይደክምምን?” ሲባባሉ… ተሸክመውት ሲጨፍሩ… በአድናቆት ሲጠይቁት… የአበበ መልስ ይበልጥ አስደንግጧቸው ነበር…
“እኔ የዓለም አንደኛ፣ የኢትዮጵያ ግን ሁለተኛ ሯጭ ነኝ”
“እንዴት?… ኢትዮጵያ ካንተም የተሻለ ሯጭ አላትን?
“አዎን… እሱ ስለታመመ ነው እኔ የመጣሁት!”
ጋዜጠኞችም ተገረሙ… ተገርመውም ወሬውን አራገቡት… ኢትዮጵያ በሁለተኛ ሯጯ ድል አደረገች ሲሉ አጧጧፉት… ያ አንደኛ የተባለውን አትሌት ለማየትም ጉጉታቸውን ገለፁ… ይህ አበበ ቢቂላ በኩራትና በአድናቆት አክብሮቱን የገለጸለት ታላቅ አትሌት ሻምበል ባሻ ዋሚ ቢራቱ ነው… ይህ ሰው ወደድንም ጠላንም… አመንም አላመንም…. በኢትዮጵያ ሩጫ እና ፉክክር በወጉ እንዲታወቁ ካደረጉ በጣም ጥቂት ፊታውራሪዎች ዋነኛው ነው!
አንጋፋው የብስክሌት ተወዳዳሪ ገረመው ደንቦባም ይህን ያረጋግጣል “በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ውድድር ላይ ማንም ሰው ተከትሎት አይገባም ነበር… ቁመናው፣ ጥንካሬው፣ ብርታቱ፣ ሁሉ ነገሩ ለሩጫ የተፈጠረ ነው… የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀውንና እንዲህ በአድናቆት የሚመለከተውን ሩጫ በሚገባ ያስተዋወቀ ዋሚ ነው… በየቀኑ ከሱሉልታ አዲስ አበባ ጠዋትና ማታ ይሮጥ ነበር…. “
በ1909 ዓ.ም ሱሉልታ የተወለደው ዋሚ ሩጫን ለውድድር ማሰብ የጀመረበት ሁኔታ የሚገርም ነበር… እናቱ በጋዜጣ የተጠቀለለ ቡና ከገበያ ገዝታ ትመጣለች… አዲስ አበባ ውላ ከግብይት የተመለሰችው እናቱ ቡናዋን ቆልታ ጋዜጣውን ትጥለዋለች… አንስቶ ሲያየው አንድ አጭር ሰው ሲሮጥ የተነሳውን ፎቶ ያያል… “እኔ እዚህ ጋራ ሸንተረሩን ስወጣ ስወርድ የምውል ሰውዬ ብወዳደር አሸንፋለሁ”… ሲል ተነሸጠ… ተነሽጦም አልቀረ… ሩጫውን ተያያዘው…
ከዓመታት በኋላ በ1945 ዓም አዲስ አበባ መጣ… በዘበኝነት ሥራ ተሰማራ… ጦር ሰራዊትን ከዛም ክቡር ዘበኛን ተቀላቀለ… ከዚያ በኋላማ የ5 ሺህ… የ10ሺህ እያለ የበርካታ ሩጫዎች ባለድል ሆነ… የሜዳሊያ እና የማእረግ ሽልማቶችንም ከንጉሡ እጅ ተቀበለ… በዘመኑ የሚፎካከረው እንዳልነበር ብዙዎች ይስማማሉ… የዋሚን ታዋቂ መሆን ተከትሎ ብዙ ጥሩ ጥሩ ሯጮች እንደመጡም እሙን ነው…
በዘመኑ ድንቅ የነበሩት እነ ማሞ ወልዴ… እነ ባሻዬ ፈለቀ… እነ አበበ ዋቅጅራ… እነ ገብሬ… እያልን ብናወራ ሁሉም የሚወራ ታሪክ ይኖራቸዋል…
ለኢትዮጵያ ሁለተኛ ተሳትፎዋ ለነበረው የሮም ኦሎምፒክ ከታጩት ፊታውራሪ አትሌቶች መካከል አንዱና ተስፋ የተጣለበት ዋሚ ቢራቱ ነበር… አበበ ቢቂላ ምንም እንኳ ጎበዝ ሯጭ ቢሆንም በእድሜ ልጅ ስለነበር (ከነ ዋሚ አንፃር) ብሎም ሌሎቹ ከሱ የተሻለ ሰዓት ስለነበራቸው በሮም ኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ አልተካተተም ነበር… የወቀቱ ስውዲናዊ አሰልጣኝ አበበን እምነት የጣሉበት ለቀጣዩ ኦሎምፒክ ነበር…
መጨረሻ ላይ ግን ታሪክ ተለወጠ… ደብረዘይት ስልጠና ቆይተው የጉዞ ዝግጅት ሲጠናቀቅ ዋሚ ታመመ መሄድ እንደማይችልም ተረጋገጠ… አሰልጣኙም “በሉ አበበን አምጡልኝ!” አሉ… አበበም ዋሚን ተክቶ ሄደ… ታሪክ ጠራችው… ዋሚን ግን ታሪክ ረሳችው…
አበበ ጀግና ነው ሁላችንም እንወደዋለን… እናከብረዋለን… እናደንቀዋለን… ነገር ግን ራሱ አበበ የሚያደንቀውን ዋሚን ብንዘነጋ ልክ አይሆንም… በነገራችን ላይ የዘንድሮን አላውቅም እንጂ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ እኝህ ታላቅ የሩጫ አባት በሕይወት እንደነበሩ አውቃለሁ… በ96 ዓመት እድሜያቸው እንኳ ይሮጡ ነበር…
ተረስተው ከከረሙበት ጥቂት አስታዋሽ አግኝተው በጣም መጠነኛ የሆነች ድጎማ ተደርጋላቸው እንደነበርም አስታውሳለሁ…
ዋሚ
. . . ዋሚ
. . . . . . ዋሚ!
ሁሌም ክብር ለታላላቆቻችን!
