እዩት ያንን በሬ በቀንዱ ተማምኖ
ያሸብረን ይዟል ላሞች ላይ ጀግኖ
ላሞች እንደሆኑ መጠቃት ልምዳቸው
ወተት እንዲያጠጡ ኮርማ ነው ግዳቸው።
በሬ እየሸለለ፣ በሬ እየፎከረ
በሬው እያጓራ፣ ስንቱ ደጅ አደረ፤
ይወጋል ይረግጣል፣ ሲሻው ያንሳፍፋል
በሬ ሆይ አይምሬው፣ ትውልድ ያጣድፋል።
ተው በሬ … ተው ኮርማ
እባክህ ተመከር፣ ያገር ምክር ስማ
ተጥለህ እንዳናይህ፣ ከቄራው አውድማ።
የሚሮጥ፣ የሚሸሽ፣ የሚበረግገው፣
ቀንድህን በመፍራት፣ የሚያደገድገው፣
ገና ብቅ ስትል መንገድ የሚጠርገው ᎐᎐᎐
ይሄ ሁሉ ፈሪ፣ ይህ ሁሉ ቦቅቧቃ
ከዘመን ፍራቻው፣ ሲባንን ሲነቃ
ሆ! ያለብህ እንደሁ ታጥቆ በቆንጨራ
ያዝ ያለህ እንደሆን ከቦ በገጀራ
ማምለጫም አይኖርህ ለአንገትህ ካራ።
“በሬ ሆይይ
በሬ ሆይይ
ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ
መግባትህ ነው ወይይይይ”
ብለን እንዳናለቅስ ቆዳህን ሲገፉ
ዛሬን አታስጀግር ተው ሰዎች ይለፉ
በሰላም፣ በጤና፣ በፍቅር ይረፉ
ላንተም አይበጅህም፣ ያጠፋሃል ግፉ።
________
አብዲ ሰዒድ
2005 E.C