ዛፍ ተጥሏል አሉኝ ማዶ ከዚያ መንደር
ጉዞ ጀምሬያለሁ ማገዶ ልበደር።
መንደርተኛው ሁሉ መጥረቢያውን ታጥቆ
ግንድ ይሸነሽናል ሥሩን ሰነጣጥቆ።
ፍልጡስ ይጠቅመናል ግዴለም ፍለጡ
ግን አደራችሁን ችግኝ አትርገጡ።
ቡቃያውም ይዟል አምሮበታል ሰብሉ
ምነው ባያረግፉት ወፎች እየበሉ።
*
ወፍዬ ወፊቱ
ወፍዬ ወፊቱ
የታደልሽ ፍጥረት ባለጸጋይቱ።
አታርሺ አትዘሪ
ፍቅር ነሽ ስትዞሪ
ማንስ ይከስሻል አገዳ ብትሰብሪ።
*
እኔስ አልዘረጋም፣ ወንጭፌን ጨክኜ
የደም ጎጆ አልሰራም፣ ጠጠር አባክኜ።
ይድላት ትፈንጭበት፣ ያውላት እርሻዬ
የተረፈው ይበቃል፣ አይጠፋም ድርሻዬ
ወፍዬን አትንካት፣ በል ተዋት ባሻዬ።
አንዳንዴ ደግ ነው፣ አንዳንዴም ይከፋል
የቀበሌው ባሻ፣ ያለማል ያጠፋል።
ዝንጉርጉር ነው ሆዱ፣ አይለይም መልኩ
ይጠባል ይሰፋል፣ አይታወቅ ልኩ
ለወፍ ይታጠቃል፣ ጀግና ነው ምትኩ።
*
ወፍዬ ወፊቷ
ወፍዬ ወፊቷ
አልጠረጠርሽም ወይ ልበ መልካሚቷ።
ባታርሺ ባትዘሪ
ፍቅር ብትዘምሪ
አይተዉሽም እኮ ተይ አትዳፈሪ።