የዓይንን አሰራር ጥበብ ያላወቀ፣
የጥርስን ተፈጥሮ ልክ ያላደነቀ፣
የቁመናን ልኬት ሚዛን ያልጠበቀ፣
ጀሚላን ቢያገኛት አወቀም ፀደቀ።
ቁም ነገር ወዴት ነው በማን ተወሰነ?
መልካምነት የታል እንዴት ተከወነ?
እውቀትስ ምንድን ነው የት ተተነተነ?
ከጀሚላ ወዲያስ ይህ ሁሉ ባከነ።
አልሐምዱሊላሂ ደርሶናል በረካ
በጀሚላ ፍቅር ቀልባችን ተነካ።
የቀሚሷ ፀዳል፣ የሂጃቧ ግርማ
የእርምጃዋ ስክነት፣ የገጿ ከራማ
የአንደበቷ ለዛ፣ የቃሏ ጥፍጥና
ማር ተምር ቢሏትስ መች ይበቃትና።
በዚህ ቁንጅና ላይ የአምላክ ፍራቻ
ተጣጥባ ተጣጥና ወደ መስጅድ ብቻ
ባያት አልሰለቻት አይነቀል ዓይኔ
የፍቅር ዓለም ሱሴ የነፍስ ኹረልዓይኔ።
አልሐምዱሊላሂ ደርሶናል በረካ
በጀሚላ ፍቅር ልባችን ተነካ።
እይዋት ስትመጣ . . .
ሽውው አለ ነፋሱ ሞገዱም ረገበ፣
ቀሚሷም ለአመል ያው ተርገበገበ፣
(ሸርተት አለ ሻሿ መልሰችው በእጇ
አምባሯን አየሁት ሲገለጥ ግዳጇ)
አትሞቅም አትበርድም ፀሐይዋም ልከኛ፣
ዛፎች ቅጠሎቹ ሆነዋት ምርኮኛ።
አበባውም ፈካ፣ ችግኙም ፀደቀ፣
ያገር ሽማግሌው በስሟ አስታረቀ፣
እናቶች ለክብሯ አወጡላት ዜማ፣
የጓዳ እድርተኛው ለቅሶውን ተቀማ።
ጀሚላ መኣረይ፣ ጀሚላ በሬዱ
ጀሚል ሸኮሪና፣ ጀሚል የውዱዱ
ጀሙ ጀሚላዬ፣ የሰው መጨረሻ
በፍቅር የሰራሽ፣ የውብ መዳረሻ።
አልሐምዱሊላሂ ደርሶናል በረካ
በጀሚላ ፍቅር ልባችን ተነካ።
እዪዋት ብቅ ስትል
’ሚያላዝነው ውሻ ብሶቱን አቆመ
ጭራውን ቆላና ፊቷ ተጋደመ።
ድመት ተንጠራራች ስስ እግሯ ረዘመ
‘አጃኢበ ረቢ’ ፍጥረት ተደመመ።
እርግቦች በዜማ እርግብኛ አወሩ
ጎጆአቸውን ረስተው በሽቶ ሰከሩ
ደነሱ ዘመሩ፣
ጨፈሩ ፎከሩ፣
ክንፋቸው ተማታ፣ ወደ ላይ በረሩ
”ምን አይነት ውበት ነው?!”
”ምን አይነት ሽታ ነው?!” እያሉ እያወሩ።
ጀሚላ መኣረይ፣ ጀሚላ በሬዱ
ጀሚል ሸኮሪና፣ ጀሚል የውዱዱ
ጀሙ ጀሚላዬ፣ የሰው መጨረሻ
በፍቅር የሰራሽ፣ የውብ መዳረሻ።
አልሐምዱሊላሂ ደርሶናል በረካ
በጀሚላ ፍቅር ስስ ልባችን ተነካ።
ምነው ባደረገኘ ቁርአን ማስቀመጫ
በስስ እጇ ዳብሳኝ ባገኝ መተጫጫ
ኧረ ምነው በሆንኩ ምንጣፍ ወይ ስጋጃ
ግንባሯ እንዲነካኝ ስታስገባ ምልጃ።
እንደመታጠቢያሽ እንደ ውዱእ ውኃ
ልቤ ፈሰሰልሽ በፍቅርሽ በረሃ
እስቲ በይ ቁጠሪኝ ልክ እንደ ሙስበሃ
በሚፈትለኝ ጣትሽ እንዳገኝ ፍሠሐ።
ጀሙ ጀሚላዬ፣ የሰው መጨረሻ
በፍቅር የሰራሽ፣ የውብ መዳረሻ።
ስለፍቅር ብለሽ፣ በአላህ በነቢ
የኒካውን ቀልቤን፣ ከቀልብሽ አስገቢ፤
አቤት ያንቺስ ውበት …
አቤት ያንቺስ ፍቅር …
. . . አ
. . . . . . ጃ
. . . . . . . . . ኢ
. . . . . . . . . . . . በ
. . . . . . . . . . . . . . . ረቢ።
/አብዲ ሰዒድ/
ተፃፈ 2005 E.C
ስቶክሆልም፣ ስውዲን