RSS

ከግርግሩ መልስ – ¶ እኛና እነሱ ¶

21 Nov

“ይህን መሬታችሁን ትታችሁ ወደ ሐበሻ ተሰደዱ! (ወደ ሐበሻ ሂዱ)፤ በእርሷ አንድ ንጉሥ አለ። እርሱ ፊት ማንም ተበዳይ አይሆንም። ሐበሻ የእውነት ምድር ነች።”- ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)

ይህ ነቢዩ ሙሐመድ በገዛ ወገኖቻቸው ተንኳሽነት በተከታዮቻቸው ላይ የሚፈጸመው ግፍና መከራ ሲበዛባቸውና ተከታዮቻቸውን ሊታደጓቸው እንደማይችሉ ሲገነዘቡ የተናገሩት ቃል ነው። ምክራቸውንም ተከትሎ 16 አባላትን የያዘው የመጀመሪያው የስደተኞች ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ተጓዘ፤ ከመካከላቸውም ልጃቸው ሩቅያና ሌሎች ሦስት ሴቶች ሲኖሩ የተቀሩት ወንዶች ነበሩ። ኢትዮጵያም መሸሸጊያ አጥተው የነበሩ አማኞች ማረፊያ ሆነች፤ ተቀበለቻቸው፣ አስተናገደቻቸው፣ ጋሻ መከታም ሆነቻቸው፤ ይህም ኢትዮጵያን የመጀመሪያዋ የኢስላም የስደት አገር አድርጓታል። ከዚያም በተከታታይ ስደተኞች እየመጡ ለዘመናት ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም እንደኖሩ ብዙ ማጣቀሻዎች ተፅፈዋል።

አስሐማ ኢብን አብሑር (በአረቡ ዓለም አጠራር) በአክሱም ከነገሱ ነገስታት አንዱ ሲሆን የንጉስ አብሑር ብቸኛ ልጅ እንደነበር ይነገራል። በኢትዮጵያ በኩል የሚገኙ ታሪኮች ስሙ አፄ አደርእዝ እንደሚባል ያስቀምጣሉ። ሙስሊሞች ነጃሺ ወይም ሰይድ አህመድ ነጋሽ ብለው ይጠሩታል። ሌሎች የታሪክ ሊቃውንት ደግሞ ነብዩ ሙሐመድ በአረቢያ ምድር ነብይ ነኝ ብሎ በተነሳ ዘመን (በ7ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ) የነበረው የኢትዮጵያ ንጉሥ አርማሐ (ዳግማዊ አርመሐ) በመባል እንደሚታወቅና በስሙም ቅንስናሽ ሳንቲም ታትሞ እንደነበር ይገልፃሉ፤ በሳንቲሞቹ ላይም “ንጉሥ አርመሐ አዛኙና ሰላማዊው” የሚል ተከትቧል ይላሉ። ይህ ክርስቲያን ንጉስ ፍፁም ፍትሃዊና ሰላማዊ እንደነበር በተለያዩ ፀሐፊዎች ተመስክሮለታል፤ እንግዲህ ይህ ንጉስ ነው የነቢዩ ሙሐመድን ተከታዮች ተቀብሎ ያስጠለላቸው።

እዚህ ላይ አንድ ነጥብ ማንሳት ግድ ነው፤ እነዚህ ስደተኞች ሳውዲ አረቢያ በሌላ አገር በደረሰባት በደል ምክኒያት ሸሽተው የመጡ አይደሉም፤ በኃይማኖታቸው ምክኒያት የተገፉ፣ በራሳቸው ወገኖች ግፍ የተፈፀመባቸው ተበዳዮች እንጂ። በዘመኑ ሳውዲ አረቢያ በሃብቱና በጎሳው የሚመካ ጉልበተኛ ሁሉ ፈለጭ ቆራጭ የሆነ አንባገነናዊ ስርአት የሚያራምድባት ነበረች። ይህ ነው የሚባል አስተዳደራዊም ሆነ ኃይማኖታዊ ስርአት አልነበራትም፤ ሁሉም ያሻውን ጣኦታት እያመለከ ጉልበተኛው ደካማውን ይረግጥባት ነበር።

እንግዲህ እነዚህ አማኞችም በገዛ ሃገራቸው መድረሻ ሲያጡ ነው ወደ ሐበሻ ምድር የተሰደዱት፤ እነዚያ ጉልበተኛ ባለስልጣኖቻቸው ቢሰደዱም አልተዋቸዉም ነበር፤ ሁለት አንደበት ርቱእ የሆኑ ተናጋሪዎቻቸውን መርጠው ለንጉሱና ለሹማምንቱ የሚሆኑ የተለያዩ ስጦታዎችን አስታቅፈው ወደ ሐበሻ ላኩዋቸው። ኢትዮጵያ ከደረሱም በኋላ ንጉሱን እጅ ነስተው ተናገሩ -“እነዚህ ያስጠለልካቸው ሰዎች አጥፊዎች ናቸውና አሳልፈህ ስጠን፤ ወደ አገራችንም ወስደን እንቅጣቸው!” አሉት። ንጉስም ከመወሰኑ በፊት ችሎት እንዲሰየም አደረገ፤ በችሎቱ ላይም ብርቱ ሙግት ተካሄደ፤ ከወሳኞቹ ጥያቄና መልሶች በኋላ የንጉሱ ፍርድ ተሰማ –

“እኔንና ሃገሬን አምነው የመጡ ሰዎች ከዛሬ ጀምሮ በኔ ሃገርና ግዛት ጥብቆች ናቸው። ተራራን የሚያህል ወርቅ እንኳ ብትሰጡኝ አሳልፌ አልሰጣችሁም። አይዟችሁ! አትፍሩ! ማንም አይነካችሁም! በክፉ የሚደርስባችሁ ቢኖር መቀጫ ደንግጌበታለሁ። በፈለጋችሁት ስፍራ መስፈር ትችላላችሁ። ከእንግዲህ በኢብራሒም ወገኖች ላይ ፍርሃት አይኖርም።” (የሐበሻው ንጉሥ ነጃሺ)

ይህ የንጉሱ ውሳኔ ተወካዮቹን ያስደነገጠ ነበር። በስልጣናቸውና በሃብታቸው ብቻ ለሚመኩት ጉልበተኞች ይሆናል ብለው ያልጠበቁት ነገር ነው። ልብ በል! ይህ ንጉሥ በዚህ ወቅት ክርስቲያን ነው፤ ስደተኞቹ ደግሞ ሙስሊሞች ናቸው፤ በስልጣንና በሃብት ቢታሰብም እነዛ ይበልጥ ይበጁታል፤ ቢሆንም ፍትህን ማጓደል አልፈቀደምና ውሳኔው አልተዛነፈችም፤ ውሳኔው ላይ ኃይማኖትም ሆነ ሌላ ተቀጥላ አልነበረበትም፤ በርግጥ ያለፈን ዘመን የሐይማኖት ታሪክ ማወቁ ለውሳኔም አስተዋፅኦ አድርጓል የሚሉ አሉ። የሆነው ሆኖ ይህ ማንም ኢትዮጵያዊ ሊኮራበት የሚገባ የፍትህ ታሪክ ነው። ስደተኞቹ ከማመናቸው በስተቀር አንዳች ጥፋት ያልሰሩ ነበሩና!… ንጉሱም የመዘናቸው በዛ ነበርና!…

ከዚህ ውሳኔ በኋላ የነብዩ ሙሐመድ ተከታዮች በኢትዮጵያ ምድር በሰላም ኖረዋል። አግብተዋል፣ ወልደዋል፤ የተመለሱም እዚሁ ኖረው የሞቱም ብዙ ናቸው። የዚህ ህያው ታሪክ መዘከሪያ የሆነው ነጃሺ መስጂድም ከመቐለ 65 ኪ.ሜ ርቃ ከምትገኘው ውቅሮ ከተማ ወጣ ብላ በምትታይ ጉብታ ላይ ጉብ ብሎ ይገኛል። የንጉሱንና የስደተኞችን ቀብርም መጎብኘት ይቻልል። በተወሰኑ ርቀቶች ደግሞ “ከዲሕ ማርያም!” ቤተ ክርስቲያን ትገኛለች። ከነጃሺ ጋር ተዛማጅ ታሪክ እንዳላት ይነገራል። በመስጂዱም ሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ እድሜ የጠገቡ ሽማግሌዎችን ማግኘትና ትረካቸውን ማዳመጥ እዚህ ከተፃፈው የሚያስከነዳ ቁም ነገር ያስጨብጣል። በተለይ ትግርኛ ለሚችል ጉብኝቱ ይበልጥ ያማረ ይሆንለታል፤ ዛሬ ይሄን ስፅፍ ከአምስት ዓመት በፊት በቦታው ያገኘሁዋቸው ሽማግሌዎች፣ እየተሯሯጡ የከበቡኝ አቧራ የጠገቡ ህፃናትና ከመስጂዱ ጎን ካልበላህ ካልጠጣህ ብለው ያስቸገሩኝ ልበ ቀና እናቶች ከነ ሙሉ ፍቅራቸው ውል እያሉኝ ነው . . .

በነገራችን ላይ በዓለም ላይ የሚገኝ የትኛውም ሙስሊም ከመካ ቀጥሎ ሊጎበኛቸው ከሚመኛቸው ኢስላማዊ ቦታዎች አንዱ ነጃሺ ነው። በርካታ ሙስሊሞች ከአመታዊው የሳውዲ የሃጅ ስነ ስርአት በኋላ ወደ ውቅሮ በመምጣት የንጉሱን መቃብርና መስጂዱን ይጎበኛሉ፤ ይህ ነው የሚባል ምቹ ነገር ባይኖረውም ቅሉ የእስልምና ባለውለታ የነበረውን ንጉስ ቦታ በመዘየራቸው ብቻ ምስጋና አቅርበው ይመለሳሉ።

በነጃሺና በነቢዩ ሙሐመድ መካከል የነበረው ግንኙነት ለዘመናት የቀጠለ ነበር። ሙስሊሞች ድል ካደረጉና ማስተዳደር ከጀመሩ በኋላም በርካታ ደብዳቤዎችና ስጦታዎች እንደተለዋወጡ ተፅፏል። ጫማ፣ መቋሚያ፣ ልብስና ሽቶዎች ከተለዋወጧቸው ስጦታዎች መካከል ናቸው። ነብዩ ሙሐመድ በዘመኑ ለነበሩ የዓለም መሪዎች የኃይማኖት ጥሪ ደብዳቤ መላክ ሲጀምሩ በቅድሚያ የሰደዱት ወደ ሐበሻ ምድር ነው። ኢትዮጵያ ኖረው የተመለሱ ስደተኞችም ኢትዮጵያ ሳሉ የነበራቸውን መልካም ቆይታ መዝግበው አቆይተዋል፤ ይህም በመላው አለም የሚኖሩ ሙስሊሞች ሐበሻን እንዲወዱና እንዲያከብሩ ያደርጋቸዋል።

“ሐበሻ ገባን፥ መልካም ጎረቤቶችም አገኘን፥ በኃይማኖታችን ምክኒያት የሚደረግብን ተጽዕኖ አልነበረም። አላህንም በሰላም መገዛት ጀመርን። አንድም ችግርና መከራ አላጋጠመንም። የምንጠላው ነገርም አልሰማንም።” ሶሐባዎች (የነቢዩ ተከታዮች)

በአንድ ወቅት የሐበሻ ንጉስ ልዑካን ቡድን ወደ ነቢዩ ሙሐመድ አገር ደረሰ። ነቢዩም እንግዶቹን እራሳቸው ማስተናገድ ጀመሩ። ባልደረቦቻቸውም አሏቸው –
“የአላህ መልክተኛ ሆይ!… እኛ እኮ እነሱን ለማስተናገድ እንበቃለን!” 
ነብዩም መለሱ – 
“እነኚህ ሰዎች ባልደረባዎቼን በሚገባ አስተናግደውልኛል። በመሆኑም ራሴ በማስተናገድ ውለታቸውን ልመልስ እወዳለሁ።” (ሐዲስ)

ታዲያ የዛሬዎቹ የሳውዲ ገዢዎች ለጎሳቸው እንኳን ያልሆኑትን… ነቢዩንና ተከታዮቻቸውን ያሰቃዩትን… የዛኔዎቹን አሳዳጆች አይነት መሆናቸው ለምን ነው?!… ሙስሊም የሆነ ሁሉ ይህን ውለታ እንደማይረሳና የነቢዩንም ቃል እንደሚያከብር ይታመናል። እነሱ ደግሞ ሙስሊሞች ናቸው። ምነው ታዲያ ቃላቸውን በሉ?… ግራ ያጋባል። ስለሆነም ታሪክ የሚያውቅ ሁሉ እውነታውን እያነሳ ለእኩይ ስራቸው ቢወቅሳቸው የተገባ ነው።

ይህ ሲባል ግን በሰሞኑ አንዳንዶች ሲያደርጉ እንደታዘብነው አይነት ኃይማኖታዊ በሆነ መልኩ መላው አረብን “ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” አይነት ፈሩን የለቀቀ ጭፍጨፋና የእስልምና መመሪያዎችን ረገጣ ሚዛናዊ አይደለም ብቻ ሳይሆን የሚያስከትለው መዘዝ የከፋ እንዳይሆንም መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ሳውዲ አረቢያ አገር ናት፤ እስልምና ኃይማኖት ነው። በጥንቱ ዘመን ኢትዮጵያና ንጉሷ ውለታ የዋሉት ለሙስሊሞች እንጂ ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያገኙበትት ዘንድ በሚል ለሳውዲ አረቢያ አይደለም። ንጉሳዊያኑ የሳውዲ ገዢዎች የለየላቸው አምባገነኖች ናቸው። ከዘመናዊው ዓለም አስተሳሰባዊ ስልጣኔም ቢሆን የራቁ ናቸው። ለዜጎቻቸውም ሆነ ለሙስሊሞችም የሚመቹ እንዳልሆኑ በበርካታ አጋጣሚዎች አሳይተዋል። ስለዚህም ቁጣና ውግዘት ሲያንሳቸው ነው!!!

ለነቢዩ ሙሐመድ የተደረገውን ውለታ እያስታወስን ችግር ላይ ያሉ ዜጎቻችን ያለ ስቃይና እንግልት ወደ ሃገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ግፊት ማድረጋችንን መቀጠሉ እጅግ መልካምና የሚገባ ነው። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከኃይማኖት ጋር ማደበበላለቁ ግን አይጠቅምም። ሰበካውን ማካሄድ የሚፈልግ የትኛውም ሃይማኖተኛ በየማምለኪያው ያድርገው፤ ይህ ጉዳይ የሰው ልጆች መበደል እንጂ የሰማይ ቤት ንግድ አይደለም። ሳውዲ አረቢያ ለምን ተነካች በሚል አጉል ጠበቃነት የሚቃጣቸው “ሙስሊሞችንም” ታዝበናል፤ ለነዚህኞቹ ደግሞ የጀነት መንገድ በሳውዲ አረቢያ በኩል ሳይሆን በልቦናችሁ በኩል ነውና ኢ-ሰብአዊ ድርጊትን ለማውገዝ ቅድመ ሁኔታ ማበጃጀት አያስፈልግም እንላለን። ሳውዲ አረቢያ ወገኖቻችን ላይ የምታደርገውን እንግልት ታቁም!!!

ሰላም ለወገኖች!
ሁላችሁም ያለ ስቃይና እንግልት በሰላም እንድትመጡ ይሁን! 
___________
አብዲ ሰዒድ

መረጃዎች: “እስልምናና ኢትዮጵያ” እና “የሰይድ አህመድ ነጋሽ ታሪክ” ከሚሉት መፃፎች ተጠናቅረዋል!

Image

 
Leave a comment

Posted by on November 21, 2013 in ስብጥርጥር

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: