RSS

Monthly Archives: December 2013

“እናቴ ትሙት አንላቀቅም!”


“ሰማህ የኔ ውድ . . .
ሳፈቅርህ ከልቤ ባንተ ተረትቼ
ስላንተው ስባክን አቅሌን ነፍሴን ስቼ
በክንድህ እያሟሟህ ባፍህ እያቀለጥከኝ
ከማያውቁት ዓለም ወስደህ እየከተትከኝ
ነፍሴን አስክረሃት በሀሴት ዳንኪራ
እንዳልቆም እንዳልሄድ ያላንተ እንዳልሰራ
አድርገህ ጠፍረህ እንዲህ አሳስረኸኝ
እሄዳለሁ ብትል ከመንገድ ጥለኸኝ
እናቴ ትሙት አንላቀቅም
እኔ በፍቅር ቀልድ አላውቅም!”

ስትይኝ ፈራለሁ
አንዳንዴም ኮራለሁ
አንዴ ደስ ይለኛል
አንዳንዴ ይጨንቀኛል።


“እየውልህ ውዴ . . .
እኔማ ስወድህ ሁኚ ያልከኝን ሆኜ
የኔን ዓለም ትቼ ባንተ ዓለም መንኜ
ጠቅልዬ ግብቼ ከገዳምህ ዋሻ
በስምህ ፀልዬ ሃጢያቴን ማስረሻ
እንደሆነ መቼም አንተም ታውቀዋለህ
ከቶ ያልሰጠውህ ኧረ እንደው ምን አለህ
ታዲያ ሁሉን ወስደህ ባዶዬን ቀርቼ
ኑሮዬን በሞላ አንተው ላይ ገንብቼ
ስታውቀው እንዳልኖር አንተን ተለይቼ
እሄዳለሁ ብትል ድንገት አንቺን ትቼ
እናቴ ትሙት አንላቀቅም
እኔ በህወት ቀልድ አላውቅም!”

ስትይኝ ፈራለሁ
አንዳንዴም ኮራለሁ
አንዴ ደስ ይለኛል
አንዳንዴ ይጨንቀኛል።


ሰማሽ የኔ እመቤት . . .
እውነት አንቺን ርቄ
እምነትሽን ፍቄ
በፍቅርሽ ቀልጄ
ሌላ ሴት ለምጄ
ምኖር ይመስልሻል ?!
እውነት እውነት እውነት
በእውነት ተሳስተሻል !
ደግሞ ፉከራሽን ዛቻሽን ፈርቼ
እንዳይመስልሽ ውዴ እኔስ ተረትቼ!

ይልቅ እኔም አልኩሽ . . .
እናቴ ትሙት አንላቀቅም
ካንቺስ ወዲያ ሴት አላውቅም።
_______
አብዲ ሰዒድ
2004 E.C

Image

 
Leave a comment

Posted by on December 31, 2013 in ግጥም

 

ጌሾና ፍቅር

ቃሌን ተቀበይኝ በብቅል በጌሾ
ተጠርጎ እንዲወጣ የቂማችን ቁርሾ
ሰክረው ያስቀየሙት ማግስቱን ይረሳል 
በጨብሲ የገነቡት አይዘልቅም ይፈርሳል
ቢሆንም ዛሬን ነይ ነገ እንደሁ ይደርሳል።

ውዴ ሆይ ነይልኝ 
በይ ጠጪ እንጠጣ
ሰላምና ፍቅር ባገር እንዲመጣ !

ደግሞ ይሄን ጡትሽን እስቲ ሸፈን አርጊው
የባላገር ነፍሴን ሰው ፊት አታባልጊው። 

እናልሽ ዓለሜ . . . 
አፈር የሚገፋው ያ ሚስኪን ገበሬ 
ተስፋው እየፈጀው ልክ እንደ በርበሬ
አንጀቱን አጥብቆ ወኔውን ሰንቆ 
ለዓላማው ፅናት እግሩን ሰነጣጥቆ
በደደረው መዳፍ ላቦቱን ሞዥቆ …

“አንተ ስትደርስልኝ አደርጋለሁ ጫማ
ለክብርህ ለግብሬ ለስምህ ሚስማማ 
በል በርታልኝ ልጄ ዝመት ወደ አስኳላ
ቀለም የለየ ነው ደህነኛ ‘ሚበላ!” 
ብሎ የሸኘኝን ከዚያ ከገብስ እርሻ 
የጀግናው አባቴን ድህነት ማስረሻ 

እንዲሆነኝ ፍጠኝ 
ነይ ጠጪ እንጠጣ
ችጋር ድንቁርና ካገር እንዲወጣ !

ኧረ ተይ ጭንሽን አንሺው ከፊቴ ላይ
አልታይ ይለኛል ካንቺ ወዲያ ሰማይ። 

ደግሞም ብትፈልጊ ግብርና ማጥናቴ
በሰብል ምርምር ጥበብ መገብየቴ 
ያባቴን ገብስ እርሻ ላዘምን ላስፋፋ
በጉልበት ሳይደክም በእውቀት ላፋፋ
አልሜ ወጥኜ ግቤን አሰልፌ
ነበር የተማርኩት ከሰው ተጣድፌ
ቀረሁኝ ፒያሳ ቢራዬን ታቅፌ።

ኦሆሆይ ፒያሳ …
አሃይ ቼቺኒያ …
የደፈረሽ ይውደም እናት ኢትዮጵያ!
ዘራፍ ብሎ ገዳይ የጀግና ልጅ ጀግና
ድህነቱን ታቅፎ፣
እውቀቱን ጨንግፎ፣
ሽል ተስፋውም ረግፎ፣ ይጠጣል ያውና!

እኔ ምልሽ ውዴ . . . 
ባለፈው ከኮሌጅ የተመረቅሽ ለታ
መንደርተኛው ሁሉ ሲጨፍር በሆታ
እናትሽ በኩራት ኮንጎዋን ተጫምታ
ዘመኗን በዚያች ለት ሹሩባ ተሰርታ
በበለዘ መልኳ በቅን ልቧ ፈክታ …

“ብሞትም አይቆጨኝ አልቀረሁ ለፍቼ
አንቺን መሳይ ሃኪም ለቀበሌ አፍርቼ
የትልቋ እህትሽ የገነት መካሻ 
የከሰለ ልቤን ሃዘኔን ማስረሻ
እሷ እንደው ተቀጨች አዋላጅ ነርስ አጥታ
አምላክ ባንቺ ካሰኝ ለወገን መከታ”
ብላ እንደሳመችሽ ባስታወስኩት ጊዜ
ያንዘፍዝፈኛል የያዘኝ አባዜ። 

የቀዬው ሰው ሁሉ ዶክተር መጣች ሲሉ
ካዛንችስ ተገኘች ልጅት በመሃሉ 
ምነው በሌሊቱ?!
ምነው በውድቅቱ?! 
አይሻልሽም ወይ ቀን መርፌ መውጋቱ?! 

እያለ እንዳይዝሽ ይህ ነዝናዥ ህሊና
በይ ጨለጥ አርጊበት ደብል አስቀጂና
ውዴ ሆይ በይ ጠጪ
አይዞሽ እንጠጣ
እድገት ብልፅግና ባገር እንዲመጣ !

ኧረ ተይ አንቺ ልጅ …
ባጭር ቀሚስሽ ላይ ፍም ጭንሽ ተጋልጦ
እንደ እናትሽ ቅቤ ጨረሰኝ አቅልጦ።

ኦሆሆይ ካዛንቺስ …
አሃይ ቼቺኒያ …
ደህና ቀን ይውጣልሽ እናት ኢትዮጵያ።
________
አብዲ ሰዒድ 
2006 E.C

Image

 
Leave a comment

Posted by on December 28, 2013 in ግጥም

 

የኤልያስ መንገድ

 

ኤልያስ መልካን የማያውቅ ይኖራል ብዬ አልገምትም። ካለም ዓለማዊ ሙዚቃ ሰምቶ የማያውቅ ሰማያዊ ሰው መሆን አለበት። ለነገሩ ኤልያስ ሰማያዊ ፋይዳ ያላቸው መዝሙሮችም አቀናባሪ ስለነበር ቢያንስ በዚያም መንገድ የሚያውቀው ይኖራል። የሙዚቃ ሰዎቻችን ወርቃማው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመን እያሉ የሚያወዱስት የነናልባንዲያን፣ የነሙላቱ፣ የነሮሃ፣ የነዋሊያስ እና መሰል የሙዚቃ ዘመኖችን ነው።

ከሮሃ ባንድ መቋረጥ በኋላ (በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1980ዎቹ አጋማሽ ወዲህ) በሃገራችን ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ መፍጠር የቻለ የሙዚቃ ቅንብር ሂደት የነበረ አይመስለኝም። ከዚህ በኋላ የሰማናቸው ሙዚቃዎችም በአብዛኛው የከተፋና የአዝማሪ ቤት ስልቶች የሚጎላባቸው ለቀጥታ ጨዋታ እንደሆን እንጂ ሙዚቃዊ ጣዕማቸው እርካታን አጎናፅፎ በምሳጤ የሚያዳምጧቸው አልነበሩም። ይህን ማለት በዘመኑ የነበሩ ባለሙያዎችን ማጣጣል አይሆንም። ከነ ሮሃ በኋላ ኤሊያስና ሌሎች ብርቱ ወጣቶች እስኪመጡ ድረስ ሙዚቃው ፈዛዛ ነበር ብሎ በድፍረት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ታመነም አልታመነም የዚህን ዘመን የሙዚቃ ቅንብር ልዩ መልክ ከሰጡት ብርቅዬ ወጣቶች መካከል ኤልያስ ፊታውራሪው እንደሆነ የማይታበል ሃቅ ነው።

በዚህ ፅሑፍ ስለ ኤልያስ የቅንብር ርቀትና ጥልቀት ማውራት ጉዳዬ አይደለም፤ ላውጋው ቢባልም ተወርቶ አያልቅምና! እንደው ለመነካካት ያህል ጥቂት ስራዎቹን ልጠቃቅስና ወደ ሌላኛውና ወደምፈልገው የኤልያስ መንገድ አቀናለሁ። ከአፍሮ ሳውንድ፣ ከዜማ ላስታስ፣ ከደመራና ከሌሎች ባንዶች ጋር ኤልያስን ከሊድ ጊታሩ ጋር ማየት ምን አይነት ስሜት ይፈጥር እንደነበር የሚያውቅና የገባው ያስታውሰዋል። ከያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በፈረንጆቹ የሙዚቃ መሣሪያዎች በቼሎና በፒያኖ በሀገር ውስጥ የባህል መሳሪያ ደግሞ በክራር መመረቁን ማውጋትም ለቀባሪው ማርዳት ነው።

ቴዲ አፍሮ የሚባልን ዘፋኝ በ’አቦጊዳ’ የቅንብርና የድምፅን ልኬት ሀ-ሁ ያስቆጠረው ኤልያስ ነው፤ ሚካኤል በላይነህን በ’አንተ ጎዳና’ ወደ ስኬት ጎዳና ያመጣው ኤልያስ ነው፤ ዘሪቱ ከበደን የእርካታ ዘር የዘራባት ኤልያስ ነው፤ ሚካያ በኃይሉን በልዩ ቀለም ያስዋባትና በ’ሸማመተው’ ደስታን እንድትሸምት ያስቻላት ኤልያስ ነው (ሰላማዊ እረፍት ሚካያ)፤ ኢዮብ መኮንንን እንደዚህ ያለ ልዩ የጣዕም ለዛ ያላበሰውና ‘እንደ ቃል’ ሲል የእውቅና ቃሉን የነፋበት ኤልያስ ነው (ሰላማዊ እረፍት እዮባ)። ጌዲዮን፣ ኃይልዬ፣ ጎሳዬ ኧረ ስንቱ ተዘርዝሮ ይዘለቃል?!… እንደው ዝም ብሎ መደመምና ማድነቅ እንጂ ምን ይባላል። በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1990ዎቹ ወዲህ የታተመ ማንኛውንም አንድ አልበም ብታነሳና የተመቹህን ዘፈኖች ብትመረምራቸው ከጀርባቸው ኤልያስን የማግኝትህ እድል እጅግ ከፍተኛ ነው። እድሜህ ይለምልም አቦ!

ሌላኛው መንገድ – ግጥምና ዜማ

ኤልያስን ከአቀናባሪነቱ ባለፈ በግጥምና በዜማ ስራዎቹ ታደንቁት ይሆን?!… ከሆነ እሰየው!.. ካልሆነ ግን እንካችሁ አብዛኛዎቹ የኢዮብ መኮንን ግጥሞችም ዜማዎችም የኤልያስ መሆናቸውን ሳስታውስ በአድናቆት ነው፤ በተጨማሪም ለሚካያ፣ ለዘሪቱ፣ ለጎሳዬ፣ ለጌዲዮን እና ለሌሎችም ሰጥቷቸዋል። የትኞቹ እንደሆኑና በምን እንደሚለዩ… እነማንንን ከጀማሪነትና ከከታፊነት ወደ ዝና ማማ እንዳመጡ እናንተ ፍርዱባቸው፤ እኔ ግን በቅርቡ ዘመናችን ከወጡት ዘፈኖች መካከል አንድም በምልከታቸው (በግጥማቸው ይዘት)፣ ሌላም በዜማቸው ወይም በቅንብራቸው ለየት ያለ ነገር ይዘው ከመጡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኤልያስ እጅ አለበት የሚል የግሌ ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ። እስቲ ትዝ የሚሉኝን የኢዮብን ዘፈኖች ብቻ ልቆንጥርላችሁ

(1) ♫ እንዳጠፋሽ ♫

♫ እንዳጠፋሽ አጥፍቻለሁ
እንደሸፈትሽ ሸፍቻለሁ
ያየሽውን አይቻለሁ
ያለ ፅድቄ
ያለ ፍርድ ቆሜያለሁ ♫

♫ ቅጣትና ምህረት ዛሬ ሰው ለያዩ
አንዱን ከፍለው አንዱን አለፉ እንዳላዩ
ይማሩኝ ይክፈሉኝ ሳላውቅ የነገዬን
ልክ እንደ ንፁህ ሰው ተጠየፍኩት ያንቺን
ማነው ፃድቅ ሰው ሁሉም ሰው ሞኝ
እራሱም ሰርቆ ሌላ ሚዳኝ
ማነው ፃድቅ ሰው ካለ ይገኝ
እራሱም ሳይሰርቅ ሌላ ማይዳኝ ♫

(ግጥም፣ ዜማ፣ ቅንብር በሙሉ ኤልያስ መልካ)

(2) ♫ ደብዝዘሽ ♫

♫ መልክን የሻረው
አንቺ ጋር ምን ተሻለው
ከሩቅ ሳትስቢ
አየሁ ልቤ ስትገቢ ♫

♫ ካንቺ በላይ ቆንጆ ሞልቶ
ያውቃል ልቤም ቀርቦም አይቶ
ግን በምን በለጥሻቸው
ቆንጆዎቹን አስናቅሻቸው ♫

♫ ካንቺ በላይ እውቀታቸው
ስቄም ነበር በቀልዳቸው
ዝምታሽ በለጣቸው
ደብዝዘሽ አጋለጥሸቸው♫

♫ተቀይሯል ዓይኔ ወዷል መልክሽን
ሲመስሉሽ ያደንቃል ሲቀርቡሽ አንቺን
ቆንጆም ውብም ለኔ ያንቺ አይነት ብቻ
ባይም ልቤ አያምንም እንዳለሽ አቻ♫

(ግጥም፣ ዜማ፣ ቅንብር በሙሉ ኤልያስ መልካ)

(3) ♫ የቋንቋ ፈላስፋ ♫

♫ ይገርማል ይገርማል
ተርቦ ልብስ ይደርባል
ይደንቃል ይደንቃል
ተጠምቶ እሳት ይሞቃል ♫

♫ ለመናገር መጎምጀቱ
ለኛስ ነው ወይ መድሃኒቱ ?!
ተጠራርተን ከየቤቱ
ቃልን መርጠን መሻማቱ ♫

♫ ሃምሳ ሎሚ ከብዶት ሊሸከም ጉልበቴ
አታግዙኝ ይቅር ጌጤ ነው ቅርጫቴ
ለምን አደንቃለሁ ጥሩ ቃል መራጩን
በምናብ ውብ ስለት የምናብ ቆራጩን ♫

♫ ሁላችን ከሆንን የቋንቋ ፈላስፋ
በተግባር መስካሪ እማኝ እንዳይጠፋ
አንድም ሳይጨበጥ ሳይዳሰስ ስንኳን
ጀግና ልንባል ነው ቃል እንዳሰካካን ♫

(ግጥም፣ ዜማ፣ ቅንብር በሙሉ ኤልያስ መልካ)

ሁሉን መዘርዘር ድካም ነው። ብቻ ከኢዮብ ዘፈኖች መካከል ከሦስቱ በስተቀር በሙሉ የኤልያስ ናቸው። የ’እውነቷን ነው’ና ‘የኔ ቆንጆ’ የሚሉት ዘፈኖች ዜማውም ግጥሙም የዘሪቱ ከበደ ሲሆን ‘ረከዴ’ የሚለው የኦሮምኛ ዘፈን ደግሞ ግጥሙ የአብዲ ውቃና ጌታቸው ኃማሪያም ዜማውና ቅንብሩ ደግሞ የኤልያስ ነው። ‘ወኪል ነሽ’፣ ‘ማን እንደ ቃል’፣ ‘ደብዝዘሽ’፣ ‘ይዘባርቃሉ’፣ ‘የምድር ድርሻዬ’ በሙሉ የኤልያስ ናቸው። ግጥሞቹ ደግሞ ተስፋን፣ ብርሃንንና መልካምነትን እንጂ እዬዬን አያላዝኑም… ከሜሪ ዮናስ ጋር በትብብር የፃፉትን ግጥም ቆንጥሬ ላብቃ መሰለኝ …

♫ ነገን ላየው እጓጓለሁ
በል ሂድ ዛሬ ጠግቤያለሁ
ከንግዲህ መቼም ላትመጣ
ደህና ሁን በል ሌላ መጣ

በል ሸኘኝ በሰላም ልሂድ
ልጀምር የነገን መንገድ

ባዶ ቢመስልም ላንተ
በቅቶት የተቆረጠ
አለው የሁሉም ድርሻ
ጨለማውን ማስረሻ
በል በርታ አይቀርም ያንተ
ይመጣል ያንተን በእጁ ያካበተ♫

♫ ባይኖቼ እስካይ . . .
እጠብቃለሁ…
ተስፋን ይዣለሁ…
ድቅድቅ ቢሆንም…
ጨልሞ አይቀርም…
አብሬ አላልፍም… ከዛሬ ጋራ…
አላንቀላፋም… የነገን ጮራ… ♫

(ግጥም: ኤልያስ መልካና ሜሪ ዮናስ
ዜማ: ኤልያስ መልካና ጎሳዬ ተስፋዬ
ቅንብር: ኤልያስ መልካ)

ኤልያስ ሆይ!… ባለህበት አክብሮቴ ይድረስህ !
________
አብዲ ሰዒድ

Image

 
Leave a comment

Posted by on December 26, 2013 in ስብጥርጥር