ቃሌን ተቀበይኝ በብቅል በጌሾ
ተጠርጎ እንዲወጣ የቂማችን ቁርሾ
ሰክረው ያስቀየሙት ማግስቱን ይረሳል
በጨብሲ የገነቡት አይዘልቅም ይፈርሳል
ቢሆንም ዛሬን ነይ ነገ እንደሁ ይደርሳል።
ውዴ ሆይ ነይልኝ
በይ ጠጪ እንጠጣ
ሰላምና ፍቅር ባገር እንዲመጣ !
ደግሞ ይሄን ጡትሽን እስቲ ሸፈን አርጊው
የባላገር ነፍሴን ሰው ፊት አታባልጊው።
እናልሽ ዓለሜ . . .
አፈር የሚገፋው ያ ሚስኪን ገበሬ
ተስፋው እየፈጀው ልክ እንደ በርበሬ
አንጀቱን አጥብቆ ወኔውን ሰንቆ
ለዓላማው ፅናት እግሩን ሰነጣጥቆ
በደደረው መዳፍ ላቦቱን ሞዥቆ …
“አንተ ስትደርስልኝ አደርጋለሁ ጫማ
ለክብርህ ለግብሬ ለስምህ ሚስማማ
በል በርታልኝ ልጄ ዝመት ወደ አስኳላ
ቀለም የለየ ነው ደህነኛ ‘ሚበላ!”
ብሎ የሸኘኝን ከዚያ ከገብስ እርሻ
የጀግናው አባቴን ድህነት ማስረሻ
እንዲሆነኝ ፍጠኝ
ነይ ጠጪ እንጠጣ
ችጋር ድንቁርና ካገር እንዲወጣ !
ኧረ ተይ ጭንሽን አንሺው ከፊቴ ላይ
አልታይ ይለኛል ካንቺ ወዲያ ሰማይ።
ደግሞም ብትፈልጊ ግብርና ማጥናቴ
በሰብል ምርምር ጥበብ መገብየቴ
ያባቴን ገብስ እርሻ ላዘምን ላስፋፋ
በጉልበት ሳይደክም በእውቀት ላፋፋ
አልሜ ወጥኜ ግቤን አሰልፌ
ነበር የተማርኩት ከሰው ተጣድፌ
ቀረሁኝ ፒያሳ ቢራዬን ታቅፌ።
ኦሆሆይ ፒያሳ …
አሃይ ቼቺኒያ …
የደፈረሽ ይውደም እናት ኢትዮጵያ!
ዘራፍ ብሎ ገዳይ የጀግና ልጅ ጀግና
ድህነቱን ታቅፎ፣
እውቀቱን ጨንግፎ፣
ሽል ተስፋውም ረግፎ፣ ይጠጣል ያውና!
እኔ ምልሽ ውዴ . . .
ባለፈው ከኮሌጅ የተመረቅሽ ለታ
መንደርተኛው ሁሉ ሲጨፍር በሆታ
እናትሽ በኩራት ኮንጎዋን ተጫምታ
ዘመኗን በዚያች ለት ሹሩባ ተሰርታ
በበለዘ መልኳ በቅን ልቧ ፈክታ …
“ብሞትም አይቆጨኝ አልቀረሁ ለፍቼ
አንቺን መሳይ ሃኪም ለቀበሌ አፍርቼ
የትልቋ እህትሽ የገነት መካሻ
የከሰለ ልቤን ሃዘኔን ማስረሻ
እሷ እንደው ተቀጨች አዋላጅ ነርስ አጥታ
አምላክ ባንቺ ካሰኝ ለወገን መከታ”
ብላ እንደሳመችሽ ባስታወስኩት ጊዜ
ያንዘፍዝፈኛል የያዘኝ አባዜ።
የቀዬው ሰው ሁሉ ዶክተር መጣች ሲሉ
ካዛንችስ ተገኘች ልጅት በመሃሉ
ምነው በሌሊቱ?!
ምነው በውድቅቱ?!
አይሻልሽም ወይ ቀን መርፌ መውጋቱ?!
እያለ እንዳይዝሽ ይህ ነዝናዥ ህሊና
በይ ጨለጥ አርጊበት ደብል አስቀጂና
ውዴ ሆይ በይ ጠጪ
አይዞሽ እንጠጣ
እድገት ብልፅግና ባገር እንዲመጣ !
ኧረ ተይ አንቺ ልጅ …
ባጭር ቀሚስሽ ላይ ፍም ጭንሽ ተጋልጦ
እንደ እናትሽ ቅቤ ጨረሰኝ አቅልጦ።
ኦሆሆይ ካዛንቺስ …
አሃይ ቼቺኒያ …
ደህና ቀን ይውጣልሽ እናት ኢትዮጵያ።
________
አብዲ ሰዒድ
2006 E.C