RSS

Category Archives: ግጥም

. . . በሬው! . . .

Image
እዩት ያንን በሬ በቀንዱ ተማምኖ
ያሸብረን ይዟል ላሞች ላይ ጀግኖ
ላሞች እንደሆኑ መጠቃት ልምዳቸው
ወተት እንዲያጠጡ ኮርማ ነው ግዳቸው።

በሬ እየሸለለ፣ በሬ እየፎከረ 
በሬው እያጓራ፣ ስንቱ ደጅ አደረ፤
ይወጋል ይረግጣል፣ ሲሻው ያንሳፍፋል
በሬ ሆይ አይምሬው፣ ትውልድ ያጣድፋል።

ተው በሬ … ተው ኮርማ 
እባክህ ተመከር፣ ያገር ምክር ስማ 
ተጥለህ እንዳናይህ፣ ከቄራው አውድማ።

የሚሮጥ፣ የሚሸሽ፣ የሚበረግገው፣ 
ቀንድህን በመፍራት፣ የሚያደገድገው፣
ገና ብቅ ስትል መንገድ የሚጠርገው ᎐᎐᎐ 

ይሄ ሁሉ ፈሪ፣ ይህ ሁሉ ቦቅቧቃ
ከዘመን ፍራቻው፣ ሲባንን ሲነቃ
ሆ! ያለብህ እንደሁ ታጥቆ በቆንጨራ
ያዝ ያለህ እንደሆን ከቦ በገጀራ 
ማምለጫም አይኖርህ ለአንገትህ ካራ። 

“በሬ ሆይይ 
በሬ ሆይይ 
ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ 
መግባትህ ነው ወይይይይ”

ብለን እንዳናለቅስ ቆዳህን ሲገፉ
ዛሬን አታስጀግር ተው ሰዎች ይለፉ
በሰላም፣ በጤና፣ በፍቅር ይረፉ 
ላንተም አይበጅህም፣ ያጠፋሃል ግፉ።

________
አብዲ ሰዒድ 
2005 E.C

 
Leave a comment

Posted by on August 2, 2013 in ግጥም

 

እናት እሙ ገላ !

ደግሞ አንድ ቀን ላንቺ ከቶ ምን ሊረባ?
ዓመት ሙሉ ማሰብ 
ዓመት ሙሉ ማክበር 
ዓመት ሙሉ መውደድ 
ዓመት ሙሉ ማፍቀር
በዘመን ቢመተር ከአንጀት ላይገባ !

ሰማሽ እሙ ገላ …

ተወርቶ ተነግሮ 
በጽሁፍ ተሞንጭሮ
በፎቶ ተሰቅሎ
በቃል ተሸልሎ 
ብዙ ተፎክሮ ያልቅ እንደሆን እንጃ
የተራመድኩበት የፍቅር ስጋጃ..

እማምዬ ውዴ …

አንቺ የኔ ምንጣፍ መረማመጃዬ
የኑሮ ግብግብ መለማመጃዬ 
መውጣቴ መውረዴ
መውደቅ መነሳቴ 
ደስታዬ ኩራቴ 
ሃዘኔ ክሳቴ 
ጉስቁልና ጥጌ
ጌጤና ማረጌ…

ደግሞ አንድ ቀን ላንቺ ከቶ ምን ሊረባ?
ዓመት ሙሉ ማሰብ 
ዓመት ሙሉ ማክበር 
ዓመት ሙሉ መውደድ 
ዓመት ሙሉ ማፍቀር
በዘመን ቢመተር ከአንጀት ላይገባ!

___ // አብዲ ሰዒድ // ___

. . . ዛሬ እለቱ የእናቶች ነው ቢሉ ላስብ ሞከርኩና ድክም አለኝ… እውን ታስቦ ይቻላልን?… 
እንዲያው ዝምምምም እንጂ!…

ለማናቸውም HAPPY MOTHERS DAY !

ፍቅር ለሁሉም እናቶች ❤
ሰላም ለሁሉም እናቶች ❤
ጤና ለሁሉም እናቶች ❤

LOVE YOU ENATEE
LOVE YOU UUMMII
LOVE YOU MOMMM

ONE LOVE !
Image

Picture Source: 
http://anguloart.wordpress.com/2012/01/19/animation-portfolio-motherhood/

 
2 Comments

Posted by on May 12, 2013 in ግጥም

 

የመድረሳ ፍቅር

(ለሐሊማ)

አሊፍ፣ ባ፣ ታ፣ ሣ . . . *
አሊፍ፣ ባ፣ ታ፣ ሣ . . .
ፊደላት ስንለይ ተቀምጠን መድረሳ
ልሳንና ቀለም ስንመጥን በአበሳ. . .

የኡስታዝን ቁጣ ትንሽ ነፍሴ ፈርታ
ለማሃፈዝ ስጣጣር ሳፋቅድ ስፈታ…

ደግሞ ባንቺ ፍቅር ቀልቤ ሩኋን ስታ
ሰርቄ እያየሁሽ በኩርኩም ስመታ
ያደግኩብሽ ውዴ ናፍቆቴ ሐሊማ
የልጅነት ገዴ ነይ ድምጽሽን ልስማ…

አሊፍ፣ ባ፣ ታ፣ ሣ . . .
አሊፍ፣ ባ፣ ታ፣ ሣ . . .
ኹሩፍ ስንለያይ ተቀምጠን መድረሳ
ልሳንና ቀለም ስንመጥን በአበሳ…

ቁርአኑን ወጣሁት ጨረስኩት ሃፍዤ
አንቺን ለማስደሰት በፍቅርሽ ተይዤ

ታዲያ አሁን ዛሬ ትልቅ ሰው ተብዬ
በትልቆች መሃል በክብር ቁጭ ብዬ
ቁርአኑን ልቀራው በገለጽኩት ቁጥር
ጀነትን ያሳየኝ ቀናው የልጅ ፍቅር
ድቅን እያለብኝ ተቸገርኩ ሐሊማ
ለበይክ አለሁ በይኝ በይ ድምጽሽን ልስማ…

አሊፍ፣ ባ፣ ታ፣ ሣ . . .
አሊፍ፣ ባ፣ ታ፣ ሣ . . .
ፊደላት ስንለይ ተቀምጠን መድረሳ
ልሳንና ቀለም ስንመጥን በአበሳ…

ትዝ ይልሽ እንደሆን ያኔ ልጆች ሳለን
ሐራም ሐላል ሳንል በቅን አብረን ዘለን
አንቺም እጄን ይዘሽ እኔም አንቺን ይዤ
ቁርአኑን ስትወጭው እኔም ባንዴ ሃፍዤ
ቦርቀን ነበረ ለዱንያም ላኼራ
ዛሬ ድምጽሽ ጠፋ በይ ስሚኝ ስጣራ
የኒካው ቀለበት ተቀምጧል በአደራ …

አሊፍ፣ ባ፣ ታ፣ ሣ . . .
አሊፍ፣ ባ፣ ታ፣ ሣ . . .
ፊደላት ስንለይ ተቀምጠን መድረሳ
ልሳንና ቀለም ስንመጥን በአበሳ…

__ // © አብዲ ሰዒድ // __
ተጻፈ: 2004 E.C
ኡፕሳላ፣ ስውዲን።

ማስታወሻ:

ከአረብኛ የተወሰዱና ምናልባት መድረሳ ላልተማረ ሰው ግር ይሉ እንደሁ ብዬ ያሰብኳቸውን ቃላት እንደሚከተለው ትርጓሜያቸውን አስቀምጫለሁ… የተሻለ የአረብኛም ሆነ የመድረሳ ትምህርት እውቀት ያለው ሰው ፍቺዎቹን ቢያሻሽላቸው ደስታዬ ነው…

መድረሳ: የቁርአን ትምህርት ቤት
አሊፍ፣ ባ፣ ታ፣ ሳ፣ . . . የአረብኛ ፍደል ቆጠራ
ኡስታዝ… የቁርአን ወይም የሃይማኖታዊ ትምህርት አስተማሪ
ማሃፈዝ… በቃል ሸምድዶ መያዝ… ወይም በቃል ብቻ መውጣት…
ኹሩፍ… የአረብኛ ፊደል ወይም ፊደል ቆጠራ
ለበይክ … አቤት.. አለሁ እንደማለት
ሐራም… የተከለለ… በሃይማኖት አስተምህሮት የማይፈቀድ
ሐላል… የተፈቀደ… ሊደረግ የሚቻል

 Image

 
3 Comments

Posted by on May 9, 2013 in ግጥም

 

. . . የኔታና ሚስ . . .

abdi2

ሀ – ሁ . . . አ – ቡ – ጊ – ዳ
ሀ – ሁ . . . አ – ቡ – ጊ – ዳ
ገና ከማለዳ ልጅነቴን ለምዳ
ከስትንፋስ ከደሜ ከነፍሴ ተዋህዳ . . .

ሀ – ግእዝ . . . ሁ – ካእብ
ሂ – ሳልስ . . . ሃ – ራብእ
ሄ – ኻምስ . . . ህ – ሳድስ
ሆ – ሳብእ . . . ስክልስ . . .

በዜማ ስለቅም፣ በህብር ሳወድስ
መልእክተ ዮሐንስ፣ መልክተ ዮሐንስ
ስከልስ ስከልስ፣ ለነፍሴ ሳሰልስ . . .

በአገራዊ ቃና
ሕይወቴ እንዲቃና
የኔነት፣ እኔነት፣ በደሜ እንዲዘራ
የኔታ በኩርኩም፣ አባም በከዘራ
የለፉልኝ እኔ፣ ያደድኩት ልጃቸው
ዛሬ ወጉ ደርሶኝ አባት ሆኜላቸው . . .

ልጄን ከቀለም ቤት በኩራት ሰድጄ
አቡጊዳም እዳ፣
እኔነትም ባዳ፥
ሆኖበት ሲቸገር አይቼ ነድጄ! . . .

እ – ን – ደ – ተ – ብ – ከ – ነ – ከ – ን – ኩ
እ – ን – ደ – ተ – ብ – ሰ – ለ – ሰ – ል – ኩ

“ኤ ፎር አፕል” ብሎ ልጄ አፉን ፈታ
“ኤን ብቻ!” የምትሰብክ ከፊደል ገበታ
ግእዝ የማታዜም፣ ቅኔ የማትፈታ
ማንነት ‘ማይገዳት፣ ለ’ሱ የሌላት ቦታ
ሚስ ናት የሱ የኔታ
ሚስ ናት የሱ ጌታ::
_____ // _____

___ // © አብዲ ሰዒድ // ___
ተጻፈ: 2000 E.C
ሐዋሳ፣ ኢትዮጵያ።

 
Leave a comment

Posted by on May 2, 2013 in ግጥም

 

ከ – ን – ቱ . . . !

እስቲ ዝም በል አፌ!
__ አንዲትም ቃል አታውጣ
ከንቱ ነገር እያራገብክ
__ ከንቱነቴን አታሳጣ::

*
አይኔም ተው አትቆጥቁጠኝ
__ እባክህ አትፍሰስ እምባዬ
አለ ሲሉት የለም ነው
__ ሰው የመሆን እጣዬ::

*
ጆሮዬም ተወው ይቅርብህ
__ እስቲ አትለቃቅም ወሬ
ደግሞ ጨርሳ እንዳትጠልቅ
__ ያዘቀዘቀች ጀምበሬ . . .

*
ልቤም ተው አተክዝብኝ
__ ግድ የለም ሃዘን አታብዛ
አገር እንደሆን ሰው ነው
__ ፍቅር ነው ህዝብን ‘ሚገዛ . . .

*
ነፍሴ ሆይ ተሰብሰቢ
__ በይ ተነሽ ግቢ ሱባኤ
ጥሞና ነው የሚበጅሽ
__ ከራስሽ ጋር ጉባኤ . . .

*
መሄድ መምጣት ነው ዓለም
__ እንደዚህ ነው ተፈጥሮ
ቀናውን መሻት ነው ደጉ
__ የነፍስን ፅናት መርምሮ . . .

___ // © አብዲ ሰዒድ // ___
ተጻፈ: ነሐሴ፣ 2004 E.C
ኡፕሳላ፣ ስውዲን።

Image

 
Leave a comment

Posted by on May 1, 2013 in ግጥም

 

መልከ ብዙ . . .

melkebezu
አንቺ መልከ ብዙ ውበትሽ በዛና

ወዝሽን ሰፈሩት በአሲዳም ቁና።

ዓይንሽን፣ ጥርስሽን፣ ጸጉርሽን እያሉ፣
የአካልሽ ቀበኞች ሰርክ ሲጋደሉ፣
ወይ አንዱ ድል ነስቶ በስስት ሳይዝሽ፣
እንዲሁ በከንቱ ደም ሲፋሰሱብሽ፣

ዘመን መሽቶ ነጋ።
ዘመን መሽቶ ነጋ።

አንቺም ከዘመን ጋር ውበትሽ ረገፈ፣
የሞተልሽ ቀረ፣
የተረፈው ንቆሽ ተራምዶሽ አለፈ።

____ // © አብዲ ሰዒድ // ____
ተጻፈ: 2003 እ. ኢ. አ
ኡፕሳላ፣ ስውዲን።

 
Leave a comment

Posted by on April 12, 2013 in ግጥም

 

___ “በጀት አልተያዘም።” ___

በእንትን ጦርነት፣ 

_ አhumanityደጋ ደርሶበት አካሉ የተጎዳ፤
ጠይቋቸው ኖሮ፣
_ የሚታከምበት ገንዘብ እንዲረዳ፤

እነ እንትና ሲመልሱለት …

“በጦርነቱ ወቅት ንጹሃን ሲመቱ፣
ብትመታም ያኔ ቢደርስም ጉዳቱ፣
ለጊዜው ላሁኑ በጀት የተያዘው
ሰለባ የሆኑት የሚታሰቡበት
__ ሐውልት ማሰሪያ ነው።”

___ // አብዲ ሰዒድ // ___
ተጻፈ: 1997 እ. ኢ. አ
መቐለ፣ ኢትዮጵያ
(የኑሮ ቀለም፣ 1998 እ. ኢ. አ)

. . . የሰው ፍቅር ያብዛልን… ለሐውልት ብቻ ሳይሆን ለሰዎች ደህንነትም በጀት የሚይዝ አስተዳደር ያስፋልን …

 
Leave a comment

Posted by on April 12, 2013 in ግጥም

 

እትዬ አዛለች . . .

lie
የአድባሯ እመቤት እትዬ አዛሉ
አራት ክብሪት ጭረው አገር አቃጠሉ። 

ይኸው ሲያር ይስቃል ያገሬ ማሽላ 
ነበልባል ሲልፈው አካሉ ሲቆላ፤ 

አዛለች እንደሆን ከቶ ምን ገዷቸው
ወገን እያነባ ስድስት ነው ቀልዳቸው፤ 

አራትና ስድስት፣ ስድስትና አራት
ለደሃ ቤተሰብ መች ይሆናል ለ’ራት?!

መለስ ያለ እንደሆን የያዛቸው ጋኔል
ጸበሉ ካልሆነ ይወሰዱ አማኑኤል።

_________ / አብዲ ሰዒድ / _________

 
Leave a comment

Posted by on March 31, 2013 in ግጥም

 

ጸሎት ወ ዱዓ . . .

*** . . . አሃዱ ጸሎት . . . *** SA 29

በዕለተ አርብ ቀን፣ በዕለተ ከተራ፣
ለጥምቀት ዋዜማ፣ ወገን ሲጠራራ፣
ባንድ እየዘመረ፣ 
ባንድ እየጨፈረ፣
ሎሚ፣ ከረሜላ እየወረወረ …
በጸሎት ሊያነጋ፣ ውርጭ እየደፈረ፣
ሕዝበ ክርስቲያኑ፣ ጃን ሜዳ ሲያቀና፣
በክብሩ ማረፊያ፣ አዳሩን ሲያፀና፣
ለማለዳው ፀበል፣ ለግፊያው ሲዘጋጅ፣
ዋልያው ተጓዘ፣ ላገር ክብር ግዳጅ፡፡

ባህረ ጸበሉን፣ በፍቅር ተራጭቶ፣
ጽላቱን በክብር፣ ከደብሩ ሸኝቶ፣
ቃና ዘገሊላን፣ በጸሎት ተደፍቶ፣
የውስጠቱን መሻት፣ ላምላክ አስረድቶ፣
ጉዳዩ እንዲሞላ፣ በእምነት ተሞልቶ
ባሳለፈ ማግስት፣ በቀን መጀመሪያ፣
በዕለተ ሰኞ፣ ድል ይሁን ለኢትዮጵያ፡፡

እግዜር ያግዛችሁ፣
እግዜር ያበርታችሁ፣
ስንቱ በየደብሩ፣ ስለት ገባላችሁ፡፡

*** . . . ክልኤቱ ዱዓ . . . *** 

በዕለተ አርብ ቀን፣ በየውመል ጁመዓ፣
መስጂድ ተሰባስቦ፣ ወገን ሲያደርግ ዱዓ፣
ያ ረቢ!… ያ ረቢ!…
አትበለን እምቢ !
ብርቱ ሃጃ አለብን፣ ሕዝብ ፊት አቅራቢ፣
ʻድምፃችን ይሰማ!… ድምፃችን ይሰማ!ʼ…
ጥረት ልፋታችን፣ ከንቱ እንዳይታማ፡፡

የረሱል መከታ፣ መጠጊያና ጋሻ፣
የቢላል የዘር ግንድ፣ የቸር መናገሻ፣
የኡሙ አይመን ምድር፣ ፍቅር መጨረሻ፣
የሶሃቦች ደጀን፣ የክፋት ማርከሻ፣
የነጃሺ ቀዬ፣ የእምባችን ማበሻ፣
ለሆነችው ምድር፣ እናት ኢትዮጵያ
ያ ረቢ አደራህን፣ አግዛት በፍልሚያ፡፡

አላህ ያግዛችሁ፣
አላህ ያበርታችሁ፣
ሸሆች በየመስጂድ፣ ዱዓ ያዙላችሁ፡፡

*** . . . ሰልስቱ ፍቅር . . . ***

ኑሮ አልሞላ ብሎ፣ ድህነት ቢገፋኝ፣
አሊያም ፖለቲካው፣ ሰው አገር ቢደፋኝ፣
ምን ብኖር እርቄ፣ ወገኔን ናፍቄ፣ 
ለአገሬስ ልጆች፣ ወጣለሁ ደምቄ፡፡

ዘር ማንዘር አልቆጥርም፣
ሃረግ አልመትርም፣
ቡትለካውም የለኝ፣ በከንቱ አልዘምርም፤
አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ አርማዬን ይዤ፣
ዘመን የወለደው፣ ተስፋዬን አርግዤ፣

አለሁ ከጎናችሁ፣ 
የአገሬ ልጆች ብርታት አይራቃችሁ
ኧረ እንኳን በደህና በሰላም መጣችሁ፡፡

__________ // _________

አብዲ ሰዒድ
ስኬት ለብሔራዊ ቡድናችን!

ፎቶ ምንጭ: @ Dimitru (Facebooker), www.DireTube.com, EthioTube

 
Leave a comment

Posted by on January 18, 2013 in ግጥም

 

ያ ሆ… ‘ምቦምቤላ! . . .


በማዲባ ምድር፣ በአቦይ ማንዴላ፣africa cup
በፈርጡ ስቴዲየም፣ በዚያ በ’ምቦምቤላ፣
ያ ሆ በል! ያገር ልጅ፣ በል የ’ርግብ አሞራ፣
ለኩራት ለክብርህ፣ ለእትብትህ ባንዲራ፡፡

ጉሮ ወሸባዬ፣ ጉሮ ወሸባዬ፣ 
ቀና በይ ካንገትሽ፣ እናት ኢትዮጵያዬ፣
ዝናሽ ያንሰራራ፣ ክብርሽ ይድነቃቸው፣
የከርሞ ታሪክሽ፣ ሃይል ይሁን ስንቃቸው፡፡

በቼልፊኮ ጫማ፣ እግር እየደማ፣
በእናት አገር ፍቅር፣ ልብ እየተጠማ፣
ስንት ታሪክ ታየ፣ ስንት ጉድ ተሰማ፡፡ 

ኢታሎ ቫሳሎ፣ ሉችያኖ ቫሳሎ፣
መንግስቱና ግርማ፣ ዝናቸው ከፍ ብሎ፣
ለዘመን ያደረ፣ 
ለአፍ የከበረ፣ ታሪክ እንደጻፉ፣
የዛሬም ልጆችሽ፣ ክብርሽን ያትርፉ፡፡

አዳነ፣ ሳላሃዲን፣ ሳላሃዲን፣ አዳነ፣
አገር ከህመሙ፣ በናንተ እግር ዳነ፣
እንግዲህ ይቅናችሁ፣ ብርታት አይራቃችሁ፣
ሴሌሜ ሴሌሜ፣ በቸር ያድርሳችሁ፡፡

“ሴሌሜ ሴሌሜ፣ ሆ ያ ሴሌሜ፣”
በዋልያ ፍቅር፣ አለሁኝ ታምሜ፤
“ሴላ፣ ሴላ፣ ሴላ፣ 
ሴላላላ ላ ሚያ” 
ድል ካንቺ ጋር ይሁን እናት ኢትዮጵያ፡፡

__________ // __________

© አብዲ ሰዒድ 
ጥር፣ 2005 E.C
shegerewa@gmail.com

 
Leave a comment

Posted by on January 17, 2013 in ግጥም