RSS

ብቃት!

 

ከመውለድ ከመክበድ ከ’ናትነት በላይ
ከእልፍኝ ከማጀት ከኩሽናም በላይ
ይልቃል ይርቃል የተሰጠሽ ፀሐይ
ተ – ነ – ሽ !
አ – ት – ል – ፈ – ስ – ፈ – ሽ
ን – ቂ !
አ – ት – ው – ደ – ቂ
የትም አታርክሽው የውስጥሽን ሲሳይ!
____________________

ከዚህ ፅሁፍ ጋር የተያያዘው ምስል J. Howard Miller በተባለ አሜሪካዊ ግራፊክ አርቲስት የዛሬ 70 አመት ገደማ የተሰናዳ ነው። ይህ ግለሰብ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ለጦርነቱ ማነሳሻነት የሚውሉ የፕሮፓጋንዳ ምስሎችን በማዘጋጀት ይታወቃል። “We Can Do It!” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ ምስልም ከስራዎቹ አንዱ ነው።

በምስሉ ላይ የምትመለከቷት ሴት Geraldine Hoff Doyle ትባላለች። በ1942 በአሜሪካ ሚቺጋን በሚገኝ የማሽነሪ ፋብሪካ ውስጥ የብረታ ብረት ሰራተኛ ነበረች። በወቅቱ የ18 ዓመት ወጣት የነበረችውን ይህችን የብረት ሰራተኛ አንድ የዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል ፎቶ አንሺ በስራዋ ላይ ሳለች ፎቶ አነሳት… ይህን ፎቶ ደግሞ ሚለር በዚህ መልኩ አሰናዳው… ከዚያም ይህ ፎቶ ሴቶችን ለፋብሪካ ስራና ለጦርነቱ እገዛ እንዲያደርጉ በማነሳሳት በኩል ብርቱ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይገመታል።

በዘመኑ የፋብሪካ ስራዎች በአብዛኛው የሚከወኑት በወንዶች ነበር… የወንዶች ስራ ብቻ ተደርገው ይቆጠሩም ነበር… በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክኒያት በርካታ ወንዶች ወደ ውትድርናው በመሰማራታቸው ሴቶችን ማበርታት ግድ ሆነ… በዚህም በርካታ ሴቶች የብረታ ብረትና የተለያዩ የፋብሪካ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ጦርነቱን እንዲያግዙ ሆነዋል። አግዘዋልም!

ምንም እንኳን በ1943 ገደማ ለተካሄዱ ጥቂት የጦርነት ቅስቀሳዎች ያገለገለ ቢሆንም ያን ያህል ለማላው ጦርነት ጥቅም ሰጥቷል ማለት ግን አይቻልም… ጦርነቱም አበቃ… ፎቶውም ተረሳ!…

በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ግን ምስሉ ከተመሸገበት ስርቻ ተጎተተ… ከ40 አመታት በኋላ ዳግም ነፍስ ዘርቶ ተነሳ… የምስሉ ትንሳኤም ሆነ!… ያሁኑ አነሳስ ግን ለጦርነት ቅስቀሳ አልነበረም… ይልቁንም ለሴቶች መብት ተሟጋቾች ልሳን ሆኖ ለማገልገል እንጂ!

ምስሉ በብዙ ሺህ ኮፒዎች ተባዛ… በርካቶች አደባባይ ይዘውት ወጡ… መጽሐፎች፣ መፅሄቶች፣ ቴምብሮች፣ እና በርካታ የጥናት ስራዋችም ይህን ምስል ተጠቅመዋል… በቤት ውስጥ… በትምህርት ቤት… በስራ ቦታ እና በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄዱ ቅስቀሳዎች ተጧጧፈውበታል…

“ሴቶችን ማሳነሱ ይቁም!”…
“አትችይም የሚል አስተሳሰባችሁን ዋጡት!”…
“እችላለሁ!”
“እንችላለን!”
“ትችላለች!”
ለሚሉ ዘመቻዎች በሚገባ አገለገለ… አሁንም ድረስ እያገለገለ ይገኛል… የተጠቀሙበት ተጠቀሙ!… በርግጥም ሁሉም ሴቶች ይችላሉ… እመኚኝ ትችያለሽ!

ይህን ማራኪና አነቃቂ ምስል እንዳስታውሰው ያደረገኝ World Economic Forum በሰሞኑ ያወጣው የ2013 Global Gender Gap Report ነው… ይህ ሪፖርት አገሮች በሴቶች ተሳትፎ ዙሪያ ያለቸውን ደረጃ ያስቀምጣል…

በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው፣ በትምህርቱ እና በጤናው ዘርፍ የሴቶች እኩልነት የት ድረስ እንደደረሰ በተለያዩ መመዘኛዎቹ መዝኖ ደረጃውን ይሰጣል… በዚህ አመት በወጣው ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያችን ከ136 ሃገሮች 118ኛ ደረጃን ይዛለች… ይህ ማለት ሴቶች ከላይ በተዘረዘሩት መስኮች ያላቸው ተሳትፎ እንዲያው ዝም የሚያሰኝ መሆኑን የሚያሳይ ነው!!…

በዚህ ሪፖርት አይስላንድ 1ኛ ስትሆን… የመን የመጨረሻ ደረጃን ይዛለች… የኖርዲክ ሃገሮቹ እነ ፊንላንድ፣ ኖርዌይ እና ስውዲን አይስላንድን ሲከተሉ እነ ደቡብ አፍሪካ ሌሴቶ እና ፊሊፒንስ ደህና ተስፋ ያላቸው በሚል ተፈርጀዋል… ጎረቤታችን ኬንያ እንኳ ኢትዮጵያን ታስከነዳታለች (ያው የሷም ገና ቢሆንም)…

አዎ ኢትዮጵያ ዛሬም ለሴቶች የምትመች አይደለችም!… ብትመችም እጅግ ጥቂት ለሆኑና ከቁጥር ለማይገቡ የከተማ ሴቶች ነው (እሱም ምቾት ከተባለ ማለቴ ነው)… የሴቶችን ምቾት ሳትጠብቅ መሰልጠንና ማደግ ደግሞ ከቶም የማይታሰብ ቅዠት ነው… ሴቶችን የዘነጋህበት ጉዞህ አንተም የተዘነጋህ ያደርግሃል… ሴትን ስታቀና መንገድህ ይቀናል… ሴትን ስትንቅ በርግጥም ትናቃለህ!… ይህን ደግሞ ባይናችን እያየን ነው… ያከበሩት ሃገራት ከብረዋልና!

እናም ፈረንጆቹ ከ60ና 70 አመት በፊት የተጠቀሙት አይነት ዘመቻ ሳያስፈልገን አይቀርም… ከ20ና 30 አመት በፊት ጀምረው የተጓዙበት ጎዳና ሳይጠቅመን አይቀርም… “አትችይም!”… “አይሆንም!”… ምናምን የሚሉሽን አትስሚያቸው… እመኚ አሳምረሽ ትችያለሽ!…

ምናልባት ይህን የምታነብ ነቃ ያለች ከተሜ ሴት ብትገኝ…

“ምን ትችያለሽ ትሽያለሽ ይለኛል?… ይህ አባባል በራሱ የበታች ነሽ አይነት ነው!… እናም ይህ አይነት ቅስቀሳ አይመቸኝም!”… ምናምን የሚል ፍልስፍና ይቃጣት ይሆናል…
ለዚህች አይነቷ ነቄ… አየሽ ነፍሴ… ይኸው መልሴ እንላታለን… “ትችያለሽ!” የሚል ቃል እንደውሃ የጠማት… ህልሟን አጉል ልማድ የጨፈለቀባት… ውጥኗን ከንቱ ቃል ያጨነገፈባት… ትችያለሽ… ተነሽ የሚለው ቃል ብቻውን የሚያለመልማት በሚሊዮን የምትቆጠር ኢትዮጵያዊት ሴት አለች ነው …

እናም ተነሽ… አንቺ ስትነሽ ሃገር ትነሳለችና!
YES YOU CAN DO IT !!!

Image

 
Leave a comment

Posted by on November 3, 2013 in ስብጥርጥር

 

ተስፋ ስንት ያወጣል?!

 

ሰው በሰው ጨክኖ ቀን ሲለብስ ጥቀርሻ
ሕልሙ የጨለመበት ያስሳል መሸሻ
እግሩን ተከትሎ
ተስፋን አንጠልሎ
አዲስ ቀንን ስሎ
በሄደበት መንገድ በጀመረው ጉዞ
ወየው ማለት ሆነ እሬሳውን ይዞ።

ወየው!… ወየው!… ወየው!…
ሰዉስ ስንቱን አየው …

ተስፋ ስንት ያወጣል ምንድነው ተመኑ?
በይሆናል ምኞት ስንቶቹ ባከኑ
ስንቱ መንገድ ቀረ… ስንቶቹ ረገፉ?!
ስንቶቹ ሰመጡ… ስንቶች ተቀጠፉ?!

ዋይታ ብቻ ሆነ ዝምምም ብሎ ለቅሶ
ለድጋፍ የሚሆን ጉልበታችን አንሶ
አቅማችን ኮስሶ
በደላችን ብሶ . . .

እንጉርጉሮ ቢወርድ ቢደረደር ሙሾ
በግፍ ለጨቀየው ለዚያ ለቂም ቁርሾ
ላይሆን መተንፈሻ ሃዘን ማስታገሻ
ለከሰሉ ነፍሶች የእምባ ስር ማበሻ

በቃኝ ማለቃቀስ
እምቢኝ ወይኔ ወይኔ
የትም አይቅርብኝ ቸር ይደር ወገኔ።

አጥንቱ አይቆጠር አይለቀም አፅሙ
በቀለም በገፁ አይለይ በስሙ
ለክቡር ሰው ገላ ወፎች አይሻሙ
አይብላው አሞራ
አይከታትፈው አውሬ
ዝም አትበይ ተነሽ!… እሪ በይ አገሬ !!!

ተስፋ ስንት ያወጣል ምንድነው ተመኑ?!
በይሆናል ምኞት ስንቶቹ ባከኑ
ስንቱ መንገድ ቀረ… ስንቶቹ ረገፉ
ስንቶቹ ሰመጡ … ስንቶች ተቀጠፉ?!…
__________________
__________________

በይሆናል ተስፋ…. በይሳካል ተስፋ… በየበረሐው ለሚባክኑና ለባከኑ ነፍሶች!!
ሰላም ፍቅርና ሕብረት ከለሁላችን ጋር ይሁን!!!

አብዲ ሰዒድ
ብጥስጣሽ ሃሳቦች (bT’sT’ash) . . .

Image

 
Leave a comment

Posted by on October 20, 2013 in ግጥም

 

ዘ – ም – ዘ – ም !

 

በዚያ ሐሩር ምድር፣ በዚያ ጠፍ በረሐ
ከደም ተቆራርጠው የሰው ልጅና ውሃ
ሕይወት ልታከትም ተይዛ ገርገራ
በዘምዘም ጠብታ ሕላዌዋ በራ።

ሃጀር ተራወጠች ሰፍዋና መርዋ
ለአንድ ልጇ ጥማት መች ዛለ ገላዋ
እሪ በል እስማኢል አልቅስ ተንዘፍዝፈህ
በእንባህ ዘለላዎች በል ያዛት ቀስፈህ።

እናት ዓለም ልፊ፣ ወዲህ ወዲያ ቃኚ፤
ያንቺን ጥማት ሽረሽ፣
በአሸዋው ዳክረሽ፣
ለአብራክሽ ክፋይ፣ ለእስትንፋስሽ ባክኚ።

በመካከል ሩጪ፣ በላይ ተራመጂ
ከወደዚህ ማትሪ፣ ደግሞም ከዚያ ሂጂ፤
ጠብቂው በዓይንሽ፣
ፈልጊው በእግርሽ፣
ርሃብ ጥማትሽን ለልጅ ፍቅርሽ ማግጂ።

አንድ! ሁለት! ሶስት! አራት!
ጉልበት እያጠራት . . .
አምስት! ስድስት! ሰባት!
ሕልሟ እየራቀባት …
ቀልቧ እየሳሳባት …
እ – ና – ት!
አቤት እናት!

በዚያ ሐሩር ምድር፣ በዚያ ጠፍ በረሐ
ከደም ተቆራርጠው የሰው ልጅና ውሃ
በዘምዘም አገኙት የነፍስን ፍሰኃ።

በል እስማኢል ጠጣ፣ ሃጀር ሆይ ጥገቢ
ላንቺም ለልጅሽም ዘምዘምን መግቢ።
እፈሽው በእጅሽ፣
አዳርሽው በዓይንሽ፣
ርኪበት በነፍስሽ፣
በአሸዋ፣ በኮረት፣ ከልይው በድንጋይ
የ’ናትነትሽ ጥግ ዝንታለም እንዲታይ።

“ዞሚ!” … “ዝሚ!” … “ዞሚ!” …
ድምፅሽን አሰሚ!
ትውልድሽን ካድሚ።

ተጓዥ መንገደኛው ይረፍ ባንቺ መንደር
“ሻባእ” “ሻባእህ” እያለ መርካቱን ይናገር።
ኃይል ብርታት ይሁን ለመኖርሽ ተስፋ
የጤናሽ ምልክት ይኑር እንዳይጠፋ።

“ዞሚ!”… “ዝሚ!”… “ዞሚ!”
ድምፅሽን አሰሚ!
ዓለምሽን ካድሚ።
___________
2006 E.C
አብዲ ሰዒድ
ኡፕሳላ፣ ስውዲን

HAPPY EID TO ALL MUSLIMS
❤ EID MUBAREK ❤

Image

 
2 Comments

Posted by on October 15, 2013 in ግጥም

 

ጀ – ሚ – ላ !

የዓይንን አሰራር ጥበብ ያላወቀ፣
የጥርስን ተፈጥሮ ልክ ያላደነቀ፣
የቁመናን ልኬት ሚዛን ያልጠበቀ፣
ጀሚላን ቢያገኛት አወቀም ፀደቀ።

ቁም ነገር ወዴት ነው በማን ተወሰነ?
መልካምነት የታል እንዴት ተከወነ?
እውቀትስ ምንድን ነው የት ተተነተነ?
ከጀሚላ ወዲያስ ይህ ሁሉ ባከነ።

አልሐምዱሊላሂ ደርሶናል በረካ
በጀሚላ ፍቅር ቀልባችን ተነካ።

የቀሚሷ ፀዳል፣ የሂጃቧ ግርማ
የእርምጃዋ ስክነት፣ የገጿ ከራማ
የአንደበቷ ለዛ፣ የቃሏ ጥፍጥና
ማር ተምር ቢሏትስ መች ይበቃትና።

በዚህ ቁንጅና ላይ የአምላክ ፍራቻ
ተጣጥባ ተጣጥና ወደ መስጅድ ብቻ
ባያት አልሰለቻት አይነቀል ዓይኔ
የፍቅር ዓለም ሱሴ የነፍስ ኹረልዓይኔ።

አልሐምዱሊላሂ ደርሶናል በረካ
በጀሚላ ፍቅር ልባችን ተነካ።

እይዋት ስትመጣ . . .

ሽውው አለ ነፋሱ ሞገዱም ረገበ፣
ቀሚሷም ለአመል ያው ተርገበገበ፣
(ሸርተት አለ ሻሿ መልሰችው በእጇ
አምባሯን አየሁት ሲገለጥ ግዳጇ)
አትሞቅም አትበርድም ፀሐይዋም ልከኛ፣
ዛፎች ቅጠሎቹ ሆነዋት ምርኮኛ።

አበባውም ፈካ፣ ችግኙም ፀደቀ፣
ያገር ሽማግሌው በስሟ አስታረቀ፣
እናቶች ለክብሯ አወጡላት ዜማ፣
የጓዳ እድርተኛው ለቅሶውን ተቀማ።

ጀሚላ መኣረይ፣ ጀሚላ በሬዱ
ጀሚል ሸኮሪና፣ ጀሚል የውዱዱ
ጀሙ ጀሚላዬ፣ የሰው መጨረሻ
በፍቅር የሰራሽ፣ የውብ መዳረሻ።

አልሐምዱሊላሂ ደርሶናል በረካ
በጀሚላ ፍቅር ልባችን ተነካ።

እዪዋት ብቅ ስትል

’ሚያላዝነው ውሻ ብሶቱን አቆመ
ጭራውን ቆላና ፊቷ ተጋደመ።
ድመት ተንጠራራች ስስ እግሯ ረዘመ
‘አጃኢበ ረቢ’ ፍጥረት ተደመመ።

እርግቦች በዜማ እርግብኛ አወሩ
ጎጆአቸውን ረስተው በሽቶ ሰከሩ
ደነሱ ዘመሩ፣
ጨፈሩ ፎከሩ፣
ክንፋቸው ተማታ፣ ወደ ላይ በረሩ
”ምን አይነት ውበት ነው?!”
”ምን አይነት ሽታ ነው?!” እያሉ እያወሩ።

ጀሚላ መኣረይ፣ ጀሚላ በሬዱ
ጀሚል ሸኮሪና፣ ጀሚል የውዱዱ
ጀሙ ጀሚላዬ፣ የሰው መጨረሻ
በፍቅር የሰራሽ፣ የውብ መዳረሻ።

አልሐምዱሊላሂ ደርሶናል በረካ
በጀሚላ ፍቅር ስስ ልባችን ተነካ።

ምነው ባደረገኘ ቁርአን ማስቀመጫ
በስስ እጇ ዳብሳኝ ባገኝ መተጫጫ
ኧረ ምነው በሆንኩ ምንጣፍ ወይ ስጋጃ
ግንባሯ እንዲነካኝ ስታስገባ ምልጃ።

እንደመታጠቢያሽ እንደ ውዱእ ውኃ
ልቤ ፈሰሰልሽ በፍቅርሽ በረሃ
እስቲ በይ ቁጠሪኝ ልክ እንደ ሙስበሃ
በሚፈትለኝ ጣትሽ እንዳገኝ ፍሠሐ።

ጀሙ ጀሚላዬ፣ የሰው መጨረሻ
በፍቅር የሰራሽ፣ የውብ መዳረሻ።
ስለፍቅር ብለሽ፣ በአላህ በነቢ
የኒካውን ቀልቤን፣ ከቀልብሽ አስገቢ፤
አቤት ያንቺስ ውበት …
አቤት ያንቺስ ፍቅር …
. . . አ
. . . . . . ጃ
. . . . . . . . . ኢ
. . . . . . . . . . . . በ
. . . . . . . . . . . . . . . ረቢ።

/አብዲ ሰዒድ/
ተፃፈ 2005 E.C
ስቶክሆልም፣ ስውዲን

 Image

 
Leave a comment

Posted by on September 21, 2013 in ግጥም

 

እዚህ እና እዚያ

እዚህ ᎐ ᎐ ᎐

ነጋሪት፣ ከበሮ ፡ ሲጎሰም ሲመታ
ጋሻ ጦር ተሰብቆ ፡ ሲነፋ በእምቢልታ
መለከት፣ ጸናጽል፣ አታሞ ሻኩራ
በሕብረ ዝማሬ ፡ በመድፍ እያጓራ …
ሽለላ እየደራ
ሻማም እየበራ
ፉከራ ቀረርቶ ፡ ያፈኞች ቱማታ
እዩልኝ ስሙልኝ ፡ ያድር ባይ ድንፋታ
ያደነቁረናል ፡ ያለ ቅንጣት ፋታ !

ስሟቸው !…
“የምልጃ ታቦቴ
አድባር ጉልላቴ
ምልክቴ ጌጤ
ማተቤ ነህ ፈርጤ…”
ሲሉ ሲባባሉ
በስም ሲማማሉ
ሲ – ሸ – ነ – ጋ – ገ – ሉ !


. . . ያ
. . . . . . ስ
. . . . . . . . . ጠ
. . . . . . . . . . . . ሉ !!!

እዚያ ᎐ ᎐ ᎐

እዬዬና መርዶ፣ የእድር ጡሩንባ
ያስለቃሾች ዋሽንት፣ ያላቃሽ አዞ እምባ
ለዛ የለሽ ዜማ፣ ጣዕም የለሽ ንፍሮ
ቅጥ የለሽ ንፍረቃ፣ ገጽ አልባ እንጉርጉሮ …

ዝርጠጣ፣ ፍርጠጣ
የስሜት ሽምጠጣ
ልዝቡን ከግልቡ ብረዛ ቅየጣ . . .

ደራሽና ገስጋሽ ፡ ላይሆኑ ዘላቂ
በጅምላ ሲነዱ ፡ ሕዝቤን አሳቃቂ
ደግሞም አስጨናቂ
“ስስ ብርሃን ፈንጣቂ”
ግርዶሽ አሟሟቂ
ውዥንብር ናፋቂ . . .

ስሟቸው !…
“ተፋጀ ተጣላ
እርስ በርስ ተባላ
ሞተ ተሰደደ
ተቃጠለ አበደ …

አትነሳም ወይ አትለውም ጎኑን
ደምህን ታቅፈህ ከምትድህ ዘመኑን”
እያሉ እያስባሉ እሳት እየጫሩ
በስም ላይ ስም ጭነው እየተሞሸሩ…

“አዋቂው … ልሒቁ
ረቂቁ … ምጡቁ
ታጋዩ … አርበኛው
የፍትህ እረኛው
አንተ ብቻ ዳኛው “

“ከኛስ ወዲያ ላሳር – ለሕዝባችን ግርማ
እጃችን ያልነካው – ሁሉም ነው ጨለማ።”
ሲሉ ሲፈርጁ በመንጋ ሲያስቡ
ጽድቅና ኩነኔን ባንድ ገጽ ሲከትቡ
ሲያረቁ ሲያፀድቁ
በቃል ሲያስመርቁ
ሲ – ያ – ጨ – መ – ላ – ል – ቁ !


. . . ያ
. . . . . . በ
. . . . . . . . . ሽ
. . . . . . . . . . . . ቁ !!!

እዚያና እዚህ ሆኖ የህልማችን ጫፉ
ስንፋተግ አለን ቀኖች ሲቀጠፉ
እስኪ እንጠጋጋ ወፎቹ እንዳይረግፉ።

/ አብዲ ሰዒድ – 2005 E.C /

Image

 
Leave a comment

Posted by on August 26, 2013 in ግጥም

 

ፋጡማ ሮባ

Image

ይህ ፎቶ ታሪካዊ ነው። የኢትዮጵያ የሴቶች የማራቶን ጀብዱ በኦሎምፒክ መንደር ሲበረበር በቅድሚያ የሚገኘው ይህ ፎቶ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም። ይህች ብርቅዬ ሴት በ23 ዓመቷ ኢትዮጵያ ከዚያ በፊት በሴቶች ማራቶን በኦሎምፒክ ውድድር አግኝታ የማታውቀውን ክብር አላብሳታለች። 

እ. ኤ. አ በ1996 በአታላንታ ተካሂዶ በነበረው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያችን 2 የወርቅ ሜዳሊያ ነበር ያገኘችው። አንዱን ይህች የኔ ጀግና ፋጡማ ሮባ በማራቶን ስታስመዘግብ ሌላኛው ደግሞ በ10ሺህ ሜትር በኃይሌ ገብረ ሥላሴ ነበር የተመዘገበው። በዚያ ውድድር የጌጤ ዋሚን ነሃስ ጨምረን ባጠቃላይ ሦስት ሜዳሊያ ይዘን ተመልሰናል።

በወንዶች ማራቶን አበበ ቢቂላን በሮም እንደምንዘክረው፣ በሴቶች 10ሺህ ደራርቱን በባርሴሎና እንደምንዘክራት ሁሉ በሴቶች ማራቶን የምናነሳትና ፋጡማን ነው። አይና አፋሯ ፋጡማ ህያው ታሪክ ሰርታለች። እንስፍስፉ ደምሴ ዳምጤ ሲቃ እየተናነቀው የመጀመሪያዋ እያለ ያወራላት ፋጡማን ነው። ዋዋዋ ደምሴ አወራሩ መጣብኝ ;( 

አሁን በቅርቡ ሎንዶን ላይ ያስቦረቀችን ቲኪ ገላና ከድሏ በኋላ በሰጠችው ቃለ ምልልስ ይህችን ብርቅዬ ሴት አልዘነጋቻትም – 
“. . . ፋጡማ ሮባ የኔ ጀግና ናት፤ የርሷን ታሪክ በመጋራቴ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ይህን የወርቅ ሜዳልያዬን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን አበርክቻለሁ፡፡ . . . ” ቲኪ ገላና።

እነሆኝ እኔም ነገ (Aug, 2013) በሚጀመረው የሞስኮ 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በውድድሩ መጀመሪያ ቀን ቲኪን ጨምሮ በማራቶን ለሚወዳደሩት ሴቶቻችን መልካም ውጤት ስመኝ ፋጡማን እያስታወስኩ ነው። 

ሴቶቻችን ሆይ ብርታት፣ ጥንካሬ፣ መረጋጋትና ድል ከናንተ ጋር ይሁን!… ይቅናችሁ!

> ቲኪ ገላና ይቅናሽ !
> መሰለች መልካሙ ይቅናሽ !
> ፈይሴ ታደሰ ይቅናሽ !
> አበሩ ከበደ ይቅናሽ !
> መሠረት ኃይሉ ይቅናሽ ! 
> መሪማ መሐመድ ይቅናሽ ! 
(መሪማ ተጠባባቂ ናት)

ሁሌም ክብር ለጀግኖቻችን! 
ሰላም ኢትዮጵያዬ ❤

___________
አብዲ ሰዒድ 
ነሐሴ 2005 E.C

 
Leave a comment

Posted by on August 9, 2013 in ስብጥርጥር

 

የሩጫችን ፈርጥ – ዋሚ ቢራቱ

14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሊጀመር በአንድ እጅ ጣቶች የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተውታል… እኛም በአትሌቶቻችን ድል ልንሸልልና ልንፎክር አሰፍስፈናል… ይቅናቸው አቦ!… ይህ እንዲህ ከጫፍ እስከ ጫፍ በአንድነት የሚያስፈነድቀን የአትሌቶቻችን ድል በዓለም መለያችን ከሆነ ዘመን ውሎ አድሯል- እድሜ ለሯጮቻችን ብርታት!…

እስቲ አጋጣሚውን አስታከን ህያው ታሪክ እንቆንጥር!… ክቡር ስም እንዘክር!…

ከ50 ዓመት በፊት አበበ ቢቂላ የሮምን ማራቶን በባዶ እግሩ ፉት ሲላትና ሕዝቡን አጃኢብ ሲያሰኝ… 42 ኪሎ ሜትር ይቅርና 42 ሜትር የሮጠ በማይመስል መልኩ ሩጫ እንደሚጀምር አይነት ሰውነቱን ሲያፍታታ… ዘና ብሎ ዱብ ዱብ ሲል… ጎንበስ ቀናውን ሲያጧጡፈው ያዩት ሲደመሙ… “ምን ያለው ሰው ነው?… አይደክምምን?” ሲባባሉ… ተሸክመውት ሲጨፍሩ… በአድናቆት ሲጠይቁት… የአበበ መልስ ይበልጥ አስደንግጧቸው ነበር…

“እኔ የዓለም አንደኛ፣ የኢትዮጵያ ግን ሁለተኛ ሯጭ ነኝ”
“እንዴት?… ኢትዮጵያ ካንተም የተሻለ ሯጭ አላትን?
“አዎን… እሱ ስለታመመ ነው እኔ የመጣሁት!”

ጋዜጠኞችም ተገረሙ… ተገርመውም ወሬውን አራገቡት… ኢትዮጵያ በሁለተኛ ሯጯ ድል አደረገች ሲሉ አጧጧፉት… ያ አንደኛ የተባለውን አትሌት ለማየትም ጉጉታቸውን ገለፁ… ይህ አበበ ቢቂላ በኩራትና በአድናቆት አክብሮቱን የገለጸለት ታላቅ አትሌት ሻምበል ባሻ ዋሚ ቢራቱ ነው… ይህ ሰው ወደድንም ጠላንም… አመንም አላመንም…. በኢትዮጵያ ሩጫ እና ፉክክር በወጉ እንዲታወቁ ካደረጉ በጣም ጥቂት ፊታውራሪዎች ዋነኛው ነው!

አንጋፋው የብስክሌት ተወዳዳሪ ገረመው ደንቦባም ይህን ያረጋግጣል “በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ውድድር ላይ ማንም ሰው ተከትሎት አይገባም ነበር… ቁመናው፣ ጥንካሬው፣ ብርታቱ፣ ሁሉ ነገሩ ለሩጫ የተፈጠረ ነው… የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀውንና እንዲህ በአድናቆት የሚመለከተውን ሩጫ በሚገባ ያስተዋወቀ ዋሚ ነው… በየቀኑ ከሱሉልታ አዲስ አበባ ጠዋትና ማታ ይሮጥ ነበር…. “

በ1909 ዓ.ም ሱሉልታ የተወለደው ዋሚ ሩጫን ለውድድር ማሰብ የጀመረበት ሁኔታ የሚገርም ነበር… እናቱ በጋዜጣ የተጠቀለለ ቡና ከገበያ ገዝታ ትመጣለች… አዲስ አበባ ውላ ከግብይት የተመለሰችው እናቱ ቡናዋን ቆልታ ጋዜጣውን ትጥለዋለች… አንስቶ ሲያየው አንድ አጭር ሰው ሲሮጥ የተነሳውን ፎቶ ያያል… “እኔ እዚህ ጋራ ሸንተረሩን ስወጣ ስወርድ የምውል ሰውዬ ብወዳደር አሸንፋለሁ”… ሲል ተነሸጠ… ተነሽጦም አልቀረ… ሩጫውን ተያያዘው…

ከዓመታት በኋላ በ1945 ዓም አዲስ አበባ መጣ… በዘበኝነት ሥራ ተሰማራ… ጦር ሰራዊትን ከዛም ክቡር ዘበኛን ተቀላቀለ… ከዚያ በኋላማ የ5 ሺህ… የ10ሺህ እያለ የበርካታ ሩጫዎች ባለድል ሆነ… የሜዳሊያ እና የማእረግ ሽልማቶችንም ከንጉሡ እጅ ተቀበለ… በዘመኑ የሚፎካከረው እንዳልነበር ብዙዎች ይስማማሉ… የዋሚን ታዋቂ መሆን ተከትሎ ብዙ ጥሩ ጥሩ ሯጮች እንደመጡም እሙን ነው…
በዘመኑ ድንቅ የነበሩት እነ ማሞ ወልዴ… እነ ባሻዬ ፈለቀ… እነ አበበ ዋቅጅራ… እነ ገብሬ… እያልን ብናወራ ሁሉም የሚወራ ታሪክ ይኖራቸዋል…

ለኢትዮጵያ ሁለተኛ ተሳትፎዋ ለነበረው የሮም ኦሎምፒክ ከታጩት ፊታውራሪ አትሌቶች መካከል አንዱና ተስፋ የተጣለበት ዋሚ ቢራቱ ነበር… አበበ ቢቂላ ምንም እንኳ ጎበዝ ሯጭ ቢሆንም በእድሜ ልጅ ስለነበር (ከነ ዋሚ አንፃር) ብሎም ሌሎቹ ከሱ የተሻለ ሰዓት ስለነበራቸው በሮም ኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ አልተካተተም ነበር… የወቀቱ ስውዲናዊ አሰልጣኝ አበበን እምነት የጣሉበት ለቀጣዩ ኦሎምፒክ ነበር…

መጨረሻ ላይ ግን ታሪክ ተለወጠ… ደብረዘይት ስልጠና ቆይተው የጉዞ ዝግጅት ሲጠናቀቅ ዋሚ ታመመ መሄድ እንደማይችልም ተረጋገጠ… አሰልጣኙም “በሉ አበበን አምጡልኝ!” አሉ… አበበም ዋሚን ተክቶ ሄደ… ታሪክ ጠራችው… ዋሚን ግን ታሪክ ረሳችው…

አበበ ጀግና ነው ሁላችንም እንወደዋለን… እናከብረዋለን… እናደንቀዋለን… ነገር ግን ራሱ አበበ የሚያደንቀውን ዋሚን ብንዘነጋ ልክ አይሆንም… በነገራችን ላይ የዘንድሮን አላውቅም እንጂ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ እኝህ ታላቅ የሩጫ አባት በሕይወት እንደነበሩ አውቃለሁ… በ96 ዓመት እድሜያቸው እንኳ ይሮጡ ነበር…

ተረስተው ከከረሙበት ጥቂት አስታዋሽ አግኝተው በጣም መጠነኛ የሆነች ድጎማ ተደርጋላቸው እንደነበርም አስታውሳለሁ…
ዋሚ
. . . ዋሚ
. . . . . . ዋሚ!

ሁሌም ክብር ለታላላቆቻችን!

 

Image

 
Leave a comment

Posted by on August 6, 2013 in ስብጥርጥር