RSS

የዞረው ጎዳና

06 Jan

በጠማማ መንገድ ጉዞ የጀመረ
ሲወድቅ ሲነሳ ባለበት አደረ።
መንገዱስ ከራቀ የህልሜ መድረሻ
አንቺንና መጠጥ ሃዘኔን ማስረሻ።
________

ይህ ፅሁፍ የአልኮል መጥጥ ማስታወቂያዎችን የሚነካካ ነው። ማንኛውንም ግለሰብ ወይም የትኛውምንም አይነት አምራች ድርጅት አይመለከትም። በአንዲት ነፍስ የሚብሰከሰክ ግለሰባዊ ትዝብት ነው። ሃሳቡ ቢስማማህ አንተም ውስጥ የሚብሰለሰል ነገር ስለነበረ ቢሆን እንጂ አዲስ ተዓምር ፈጥሬልህ አይደለም፤ ሃሳቡ ቢጎረብጥህ አላማዬ አንተን ማስደሰት አይደለምና ሃሳቤን አክብረህ ማስታወቂያህንም፣ ጨብሲህንም የመቀጠልና የማስቀጠል ምርጫው ያንተ ነው።

“ሸገር ላይ አብቦ ሸገር ላይ ያፈራ
የጥንት የማለዳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ
አብሮ እየዘመነ ከዘመኑ ጋራ
አራዳን ያሞቀ አራዳን ያደራ

ዘላለም ጥም ቆራጭ ዘላለም ፍሰሀ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ የነፍስ እህል ውሃ
ወዳጅነት ጠብቆ ጨዋታ እንዲደራ
ይንቆርቆር ይቀዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ!”

ይህ የማንቆለጳጰሻ ግጥም በጥላሁን ገሠሠ “የጥንቱ ትዝ አለኝ” ዜማ ታጅቦና በአንባቢው አስገምጋሚ ድምፅ ግርማ ሞገስ ተላብሶ በሸገር ኤፍ ኤም ሲቀርብ ለጆሮ ደስ ይላል። ደስ ማሰኘትና ለመጠጥ ማነሳሳት የማስታወቂያው አላማ በመሆኑ በዚህ በኩል ተሳክቶለታል። ፋብሪካው ለዚህ ሙገሳ የተጠየቀውን ቢከፍልም አይቆጨው፤ ለአርቲስቱም ለድርጅቱም የገቢ ምንጭ ሆኗልና ይቅናቸው።

በግጥሙ ውስጥ ከተካተቱት የማስዋቢዋ ቃላት ጋር ግን በግሌ ፀበኛ ነኝ። ‘ዘላለም ጥም ቆራጭ’… ‘ዘላለም ፍሰሃ’… ‘የነፍስ እህል ውሃ’… ‘ወዳጅነት አጥባቂ’… ምናምን የሚሏቸውን የውዳሴ ቃላት በሰማኋቸው ቁጥር ግርም ይሉኛል። ገንዘብ ስለተከፈለና እድሉ ስለተገኘ ብቻ የሚንፎለፎል ቅጥፈት አይጥመኝም። ቢራ በየትኛው ስሌት ዘላለማዊ ጥም ሊቆርጥ እንደቻለ አልገባኝም። ዝንታለም ፍሰሃ ሊለግስ ይቅርና በብዙ መከራዎች ተቀነጣጥሳ ያጠረች እድሜን የባሰ የሚያሳጥርም ይሄው ልኩ የማይታወቀው አልኮል ነው። የነፍስ እህል ውሃነቱም ጠግቦ ላላደረ አንጀት የሰማይ ያህል ሩቅ ነው፤ ጠግቦ ላደረው ግን ምን እንደሆነ አላውቅም።

“ስማ ይሄ እኮ ማስታወቂያ ነው!… ማሻሻጫ እንጂ ሃቅ አይደለም!… ጅል ነህ እንዴ?!… ምን ታካብዳለህ?… ክባዳም!” አይነት ሰልጠን ያለ ቡጢ ከሰለጠኑት አካባቢ የሚሰነዘር ከሆነም ይህችን ጣል አድርገን እንቀጥላለን …

ዘላለም ጥም ቆራጭ ከሆነማ አርኪ
ለዝንታለም ሃሴት ከተሰኘ ምልኪ
የነፍስ እህል ውሃው በወግ ተበጥብጦ
በብልቃጥ በሲኒ ተደርጎ በጡጦ
ልልጆች ለህፃናት ይመረት አደራ
ታላቋን ኢትዮጵያ በቶሎ እንድንሰራ።

ቺርስ
በጊዮርጊስ

በርግጥ የአልኮል መጠጦችን በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በተለያዩ የህትመት ውጤቶች እንዲሁም በእስፖንሰር መልክ ማስተዋወቅ በጭራሽ አይገባም የሚል ደረቅ አቋም የለኝም። መንግሥትስ ለምን በህግ ‘ፈፅሞ እንዲከለከል’ አያደርግም?! የምል ወገኛም አይደለሁም፤ አይተዋወቅ ብዬም እየተነሳሁ አይደለም። በህግ የተከለለ የማስተዋወቅ ስርዓት ይኑረው (ወይም ህጉ ካለ በብርቱ ይተግበር) ነው መነሻዬ። አዎ በነጋ በጠባ ቢራ ቢራ አይበሉብን!.. ጎዳናዎቻችንን ሁሉ በቢራ አይሙሉብን!… ኧረ በዛ!… ኧረ ለከት ይኑረው!… ነው የኔ ሃሳብ። እኛ’ኮ ባይተዋወቅም በመጠጣት አንታማም!… ኑሯችን ለስካር ሩቅ አይደለም!… እንኳን አይዞህ ጠጣ ተብለን እንዲሁም ጠጪዎች ነን… ለዚህ እንኳን ብቁ ነን!…

የኛ አርቲስቶች፣ የኛ አስተዋዋቂዎች፣ የኛ ጋዜጠኞች፣ እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለሙያዎች አልኮልን የሚያስተዋውቁበትን መንገድ ልብ ብሎ ላስተዋለው ያስተዛዝባል ብቻ ሳይሆን ያሳስባልም። በተለይ ይሄን ማስታወቂያ እየሰሙ የሚያድጉ ልጆችስ ብሎ ማሰብ ለሞከረ የኔ ብጤ ክባዳም አንገት ያስደፋል።

‘የነፍስ እህል ውሃ ነው’… ‘የዘላለም ፍሰሃ ይሰጥሃል’… ‘ጨዋታህ ያለ ቢራ አይደራም’… ‘ወዳጅነትህ ያለ መጠጥ አይቀጥልም!’… እያልክ ላሳደግከው ልጅህ ኋላ ላይ ደግሞ ‘መጠጥ ይጎዳሃል’… ‘ጤናህን ያዛባብሃል’… ‘ከወዳጅ ያጣላሃል’… ምናምን ብትለው “አባዬ ደግሞ ታሾፋለህ እንዴ?!… አንተ አይደለህ እንዴ ለህዝቡ ስታውጅ የነበረው?!” ብሎ እንደሚያፌዝብህ ለማሰብ ጥልቅ ተመራማሪ መሆን የሚሻ አይመስለኝም። ያው እንዳላገጥን እንለቅ ካልሆነ በቀር…

አብዛኞቹ አርቲስቶች በግጥም፣ በዜማና በሙዚቃ ቅንብር ሲያንቆለጳጵሱት፤ በተለያየ የምስል ዲዛይን ሲያስሽሞነሙኑትና ሲያሞጋግሱት ስራዬ ብሎ ላያቸው አስካሪ መጠጥ የሚያስተዋውቁ ሳይሆን ብርቱ የነፍስ አድን መድሃኒት ሊያድሉ የሚሰናዱ ነው የሚመስሉት። አብዛኞቹ ነገረ ስራቸው ቅጥ ያጣ፣ የሚከፈላቸውን ገንዘብ እንጂ የሚሉትን ነገር ለሽራፊ ሰከንድ እንኳ ያሰቡበት የማይመስሉ ናቸው። በርግጥ ሁሉም ብሎ በአንድ ላይ መጨፍለቅ አግባብ አይደለም (እዚህ ውስጥ ያልተካተቱ አርቲስቶች ይቅር ይበሉኝ) በአብዛኛው ለአይናችን አሊያም ለጆሯችን የከበዱት አርቲስቶቻችን (ትልልቆቹም መጤዎቹም) ግን ቢያንስ የአንድ ቢራ አስተዋዋቂ መሆናቸው የአደባባይ ሃቅ ነው።

በነጠላ ዜማም ይሁን በነጠላ ፊልም ትንሽ ዝና ከተፍ ካለች ጥቁር መነፅርና ቢራ መለያቸው እየሆነች ነው። ኧረ ጎበዝ እየተሳሰብን እንጂ!… በጥቁሩ መነፅር ስታዩት ሌላ ነገር ወይም ሌላ ሃገር እየመሰላችሁ ይሆን እንዴ?!… እስቲ ከጥቁሩ መነፅር ውጡና ጎዳናዎቻችሁን… ህዝባችሁን እዩት… በሃላፊነት ጠጡ ከማለታችሁ በፊት በሃላፊነት ታስተዋውቁ ዘንድ ትለመናላችሁ።

“አውዳመት ሲደገስ ጎረቤት ሲጠራ
ወዳጅ ለመጋበዝ ገበታ ሲሰራ
እንዲሞቅ እንዲደምቅ ጨዋታ እንዲደራ
ይንቆርቆር ይቀዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ

ደስ ብሎ እንዲውል ያውዳመቱ ቆሌ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ አብሮ ይኑር ሁሌ
ወዳጅነት ጠብቆ ፍቅር እንዲደራ
ቅዱ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ያዘቦት ያውዳመት የሁል ጊዜ ቢራ።”

ያዝ እንግዲህ!… ቢራ ከሌለህ አውዳመት የለም!… ወዳጅነት የለም!… ጎረቤት የለም!… መሰባሰብ የለም!… መተሳሰብ የለም!… ፍቅር ብሎ ነገር የለም!… ይልሃል!… በል እንግዲህ ጠጣና አውዳመትህን አድምቅ!… ወዳጅነትህንም ቀጥል… ቢራህም ሁሌም አብሮህ ይኑር ይልሃል!…

እኔም ልጨምርልህ… ከቢራህ የተለየህ እለት ድህነትህና ድንቁርናህ ፍንትው ብሎ ይታይሃልና በድህነትህ እንዳታፍር በኋላቀርነትህም እንዳታዝን ለከት የሌለው አጠጣጥ ጠጣ!… ጠጥተህ ድህነትህን እርሳ!… ይሄንንማ መፅሐፉም ብሎኛል ካልክም መብትህ ነው… መፅሐፉንም… ማስታወቂያውንም… እኔንም “እምቢኝ!” ያልክ ቀን ግን ወዳጅነት እንዴት እንደሚጠብቅና ድህነት እንዴት እንደሚፋቅ ሊከሰትልህ ጀምሯል ማለት ነው። ያኔ እናወጋለን!… ላሁኑ ግን ይህችን ሚጢጢዬ ግጥም እያላመጥክ ቀጥል …

‘አባቱ ደንዳና ብርቱ ጌሾ ወቃጭ፤
እናቱ ታታሪ ብቅል አብቃይ ቀያጭ፤
ኮበሌ ልጃቸው ሆነላቸው በጥባጭ፤
በል ዝም ብለህ ጨልጥ ያገር ሰው ተቀማጭ።’

ላሁኑ ሰላም
ትዝብቱ ግን ይቀጥላል

አብዲ ሰዒድ

Image

 
Leave a comment

Posted by on January 6, 2014 in ስብጥርጥር

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: