RSS

እቴ አንቺን ሳስብሽ . . .

08 Mar

 

እቴ አንቺን ሳስብሽ ልቤን የሚደክመኝ
ዐይንሽ ላይ ሳተኩር እኔ ዐይኔን የሚያመኝ . . .

አይደለም ለፊትሽ፣ ለገጽሽ ከራማ
አይደለም ለድምጽሽ፣ ላንደበትሽ ዜማ
አይደለም ለጸጉርሽ፣ ለዚያ የሃር ነዶ
አይደለም ለጥርስሽ፣ ለሃጫው በረዶ . . .

አይደለም አይደለም፣ ውዴ አበባዬ . . .
ነገሩ ወዲያ ነው፣ ሌላ ነው ጉዳዬ . . .

አየሽ . . .
በኔና አንቺ መንደር፣ በሁለታችን አገር
ወንድ ነው የበላይ፣ ወንድ ነው ‘ሚከበር
ወንድ ነው ‘ሚያነሳ፣ ወንድ ነው የሚጥል
ወንድ ነው በግብሩ ሴትን የሚያጣጥል
አዳፍኖ ‘ሚያቃጥል . . .

(በርግጥ ሴትም ሆነው ሴትን የሚያረክሱ
አይጠፉም ይሆናል በስምሽ የሚያርሱ)

ግን ግን ለምን ሆነ ?!
ልቤ ገነገነ . . .

አዋቂ ታዋቂው፣ አድናቂ አዳማቂው
መሪና ተመሪ፣ ተጨመላላቂው
መንገድ የጀመረ፣ ተረኛ ጠባቂው
ሁሉም እንዳቅሙ፣ ስምሽን አንስቶ
እንደፈቀደለት፣ ድክመትሽን አውስቶ
ውበትሽን አጉልቶ፣ ገላሽን አቡክቶ
ነፍስሽን ዘንግቶ፣ ህልምሽ ላይ ተኝቶ
ሲጽፍ ሲቸከችክ፣ ስንቱን እንቶፈልቶ
ኃይልሽ በየት በኩል፣ በነማን ተሰምቶ
ኧረ እንደምን ታይቶ …

(ይኸው እኔ ራሴ፣ እየጻፍኩ አይደለ
ብዙ ያልጨመረ፣ ብዙም ያልጎደለ)

ጥንባዣም ደራሲ፣
ኮተታም ሃያሲ፣
እንቅልፋም ገጣሚ፣
ሆዳም አሳታሚ . . .
ባንድ አገር፣ ባንድነት ዐይኑ እየፈዘዘ
በንዋይ በዝና፣ ነፍሱ እየነፈዘ
በሆዱ፣ በራቡ፣ እየደነዘዘ፤
የቃላት ቡትቶ እየበዋወዘ
ስንት ቀን ገደለሽ፣ ስንት አንቺን ገነዘ …

አየነው፣ ሰማነው …
ገዝተን አነበብነው …

‘ወሲብ፣ ገድል፣ ሚስጥር
የአዲስ አባ ‘ቂንጥር’
የጭኖች ንቅሳት
የዳሌ ትኩሳት’
መዋደቅ መነሳት የሚል ዝባዝንኪ
ስንት ሰዎች ጻፉ በይ ንገሪንኝ እስኪ ?!

ለምቦጭሽን አትጣዪ፣ ጠበቅ አርገሽ ስሚኝ
ካጠፋሁም ላጥፋ፣ ተይኝ አታርሚኝ
ይልቅ ተማሪና ስታመም አክሚኝ።

አሁን ያ ደራሲ . . .
‘ጭኗ ሲተራመስ፣ ዳሌዋ ሲቆጣ
ጡቷ ሲወጣጠር፣ ቅንዝሯ ሲመጣ
ሲሰራት፣ ሲቆላት፣
እንደ ጉድ ሲያምሳት፣
አብርድላትና ከንቱ ነፍሷን ንሳት፤
መቼም ከዚህ በቀር ሁሉም ነው የሚያንሳት።’

ብሎ እየጻፈ በገላ ችርቸራ
በሴትነትሽ ጥግ ዝሙት እየዘራ
ከመጣ ከሄደው አንቺን እያዳራ
‘ታላቅ ሰው’ ተብሎ ባገሩ ሲጠራ
ማን ተከላከለ?
ማን ሰው ሃቅ አወራ?

ደግሞ የገረመኝ …
ከሁሉም ከሁሉም ይብሱን ያመመኝ …

‘በጭኖችሽ ሰማይ
ወጥታ ብርቱ ፀሐይ
አቃጥላ ፈጀችሽ አንቺኑ መልሳ
የቁሌት አዝመራ በነፍስሽ ነስንሳ።’

ብሎ የጻፈውን ያንኑ ደራሲ
ሲያንቆለጳጵሰው ያ ብኩን ሃያሲ

“እውነት ነው፣ ሃቅ ነው
እሱማ ታላቅ ነው።”
ብለሽ ስታወሪ፣ ላገር ስትለፍፊ
ስሰማና ሳይሽ ዘውትር ስታናፊ
አ – ቤ – ት… ስታስከፊ !

በእውነት ገረመኝ …
በእውነት አመመኝ …

ጡት ብቻ ነሽ አንቺ ?!
ጭን ብቻ ነሽ አንቺ ?!
ወሲብ ነው ገድልሽ ?!
በቃ እሱ ነው ድልሽ ?!
ህልም የለሽም እንዴ ?!
ኧረግ ወየው ጉዴ . . .

(አትመልሽው ይቅር፣ አታውሪልኝ ለኔ
ኑሪና አሳይው ለብኩን ወገኔ።)

አየሽ አንቺ ለሱ . . .
(ብታምኚም ባታምኚም)
‘አንብበሽ ማይገባሽ፣ ገብቶሽ ማትረጂ
ካገኘሽው ጋራ፣ የትም ‘ምትበ-ጂ’
ትሰሪው ትሆኚው፣ ታልሚው የሌለሽ
በቂጥሽ ከመኩራት ፥
ቁጭ ብሎ ከማውራት ፥
ወንድ ልጅ ከማርካት ፥
የዘለለ ሚና ባለም የጎደለሽ
ሸሌ ነሽ፣ ሸርሙጣ፤
ቀን እየጠበቀ ግብርሽ የሚወጣ።’

ደሞ ይሄን ያልኩሽ፣ እኔ እንዳልመስልሽ
ለስድብ ለቁጣ ፥
ለተቃውሞ ጣጣ ፥
መንገድ አደባባይ፣ ጎዳና እንዳይጠብሽ
ገላልጠሽ መርምሪው፣ ያለውን በቅርብሽ…

አውቃለሁ።

የሚያብብ ቡቃያን ብዙ ነው ረጋጩ
የደረሰ ፍሬን እልፍ ነው አፍራጩ
ብዙ ነው ገናዡ፣ ብዙ ነው በዝባዡ
ብዙ ነው በዋዡ፣ ብዙ ነው አፍዛዡ
ብዙ ነው ቀጣፊው፣ ብዙ ነው በራዡ …

መሪዎቹ ገናዥ፣ ካድሬዎቹ ገናዥ
አምራቾቹ ገናዥ፣ ነጋዴውም ገናዥ
ዘፋኞቹ ገናዥ፣ ጸሐፊዎች ገናዥ
በቀልዶች ጋጋታ፣ በፌዞች አደንዛዥ
እኔና አንቺ ደግሞ ባካኝ ተንጠራዋዥ …

“እምቢኝ አልገንዝም !
የሚያብብ ቡቃያን አላደነዝዝም !
የነገዋን ብርሃን አላደበዝዝም !”
ያለው ብርቱ ታጋይ
በነዚያኞች ሃካይ
ተጠልፎ ተጥሎ ተጋድሞበት ሃኔ
አሸልቧል ወዲያ ማንም ሳይል ወይኔ።

አንዳንዱም እስር ቤት
አንዳንዱም መጠጥ ቤት
ገሚሱም ሰው አገር
ገሚሱም ጎዳና ወደናንተ ሰፈር
ወድቋል፣ ይታዘባል
የወጪ ወራጁን ሳቅ ይመዘግባል።

ይገርማል . . . !
“ትውልድን ለማነፅጽ
ወገንን ለመቅረጽ
በሚል አጉል ቅዠት እኔ አልተነሳሁም
ጥበቤን ለማውረድ በርግጥ አልሳሳሁም
እንደመጣ ጻፍኩት
ከዚያም አሳተምኩት
በቃ ተደነቀ
ባገሩ ታወቀ።”

ይሉት መቀባጠር፣ አጉል ፍልስፍና
በአፍሪካ ምድር፣ ተስፋን ላያቀና
የተደፈርሽ አንቺን ክብር ላያፀና
አይገባኝም እኔ አታስረጂኝ እቴ
ይልቅ ነቅተሽ አንቂኝ፣ አድኚኝ ከሞቴ።

አየሽ ባገራችን . . .
ትንሽ ገንዘብና የበዛ ቲፎዞ
በግራና በቀኝ፣ ለጋሻ ተይዞ
ላውሪ ጋዜጠኛ፣ ለጣፊ መናኛ
ኪሱን ሸጉጦለት፣ ነፍቶት እንደፊኛ
ካልሆነ አይጻፍም፣ አይታተም ከቶ
ቢታተምም እንኳ አለልሽ ተረስቶ
በቁም ተዘንግቶ ።

(ይህ ሁሉ መለፍለፍ አሁን ለምንድነው
ዝብዘባ የሚያበዛ ጅላንፎ ሞኝ ነው።)

ብቻ አንቺን ሳስብሽ፣ ለዚህ ነው ‘ሚደክመኝ
እራሴን፣ ወገቤን፣ አይኖቼን የሚያመኝ …

ቢሆንም አምናለሁ!
ከጡቶችሽ ሰማይ
ከጭኖች ሰማይ
ከዳሌ ከባትሽ፣ ከሽንጦችሽ ሰማይ
የራቀ የላቀው የነፍስያሽ ሰማይ
ኃይሉን የተፋ ቀን፣ ወጥተሽ ካደባባይ
ያኔ ነው ያገሬ፣ ብርሃኗ የሚታይ
ያኔ ነው ሚነቀል፣ የሕቦቼ ብካይ።

________
አብዲ ሰዒድ
2006 E.C

Image

 
7 Comments

Posted by on March 8, 2014 in ግጥም

 

7 responses to “እቴ አንቺን ሳስብሽ . . .

 1. Abay Mengistu

  July 31, 2014 at 2:22 pm

  አብዲ ሰዒድ:እንዴት ነህ ካለህበት ሁሉንም ግጥሞችህን እጅግ በጣም ወድጃቸዋለሁ:: በዚሁ ቀጥልበት! በተለይ እቴ አንቺን ሳስብሽ የሚለው የኔም ሀሳብ ስለሆነ እጅግ በጣም ወድጀዋለሁ:: አንዳንዴ እዚህ ድህረ_ገጽ ስገባ ግጥም ምንያህል ሀይል እንዳለው እረዳለሁ
  ብቻ በርታ መልካም ጊዜ::ለወደፊትም ሌሎች ስራወችህን ለማንበብ በጉጉት እጠብቃለሁ::
  አባይ ነኝ ከእስራዔል

   
 2. ashenafi gabre

  June 1, 2016 at 3:25 pm

  ምን ማለት እችላለው?
  ግጥምህን ሳነብ
  ውስቴ ግርም አለው
  ቀጭ ብዬ ነበር መሀል ላይ ተነሳው
  እንደገናም ቅጭ አልኩ
  በደስታም አለቀስኩ
  መጨረሻ ላይማ ተነስቼ አጨበጨብኩ

   
 3. amare ke addis ababa

  June 30, 2016 at 12:33 pm

  betam arif gtmnew bertaln wogenachn

   
 4. dasash

  February 9, 2017 at 11:33 am

  betam arif gtim nw wowwwwww

   
 5. Dawit Gizaw

  February 27, 2017 at 9:56 am

  amazing touch!!!keep it up!

   
 6. አብራሃም ወርቁ

  May 8, 2017 at 7:40 am

  ታድለህ የሚገርም ተሰጦ ነው

   
 7. abrar mohammed

  November 12, 2020 at 12:01 pm

  አንደኛ

   

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: