RSS

Monthly Archives: December 2012

በብሪትሽ መንደር . . .


british1

በብሪትሽ መንደር በብሪትሽ ቀዬ
አገኘሁት ራሴን በደማቅ ተስዬ …

የእምዬ ምኒሊክ የአድዋ ጀብዱ
የአርበኞች ተጋድሎ የደም ስሪት ቅዱ
የታሪክሽ ስፌት በጦርና ጋሻ
በደማቅ ተጽፈሽ አየሁሽ ሃበሻ …

በብሪትሽ መንደር በብሪትሽ ቀዬ
አገኘሁት ራሴን በወግ ተሰቅዬ …

የሃይማኖት አድባር የእምነት መናገሻ
የእስላም የክርስቲያን መነሻ መድረሻ
የግማደ መስቀል የክቡር ማደሪያ
የማክዳ ጥበብ የጽዮን መዋያ …

የነጃሺ እትብት የሶሃቦች መኖሪያ
የታሪክ አውድማ የእውቀት መናሀሪያ
የስልጣኔ ፈርጥ የዘመን መታያ
ጎበኘሁሽ ዞሬ ጥበብ ኢትዮጵያ …

በብሪትሽ መንደር በብሪትሽ ጓዳ
አገኘሁት ራሴን ከርሞ ከግድግዳ …

በከሰል፣ በሙጫ፥ በዉሃ ተቀይጦ
የኢልሙ መክተብያ ‘መዱ’ ተበጥብጦ
በለውህ የታተመ የቁርአንሽ ለዛ
የሸሆችሽ ድርሳን ዝናሽን ሲያበዛ …

ዉብ የቁም ጥፈትሽ የብራናሽ መልኩ
የግዕዝ ምጣኔሽ የቀለምሽ ልኩ
የቅርጻቅርሽ ጥግ የአልባሳትሽ ዝሃ
የቄሱ መቁጠሪያ የኢማም ሙስበሃ
ሁሉን አገኘሁት ተሻግሮ በረሃ …

በብሪትሽ መንደር በብሪትሽ ቀዬ
አገኘሁት ራሴን በወግ ተሰቅዬ …

/ © አብዲ ሰዒድ፤ 2005 E.C
ብሪትሽ ሙዚየም፣ ለንደን /

 
4 Comments

Posted by on December 26, 2012 in ግጥም

 

የ’ኔ አምባሳደር . . .


Image

በድሬዳዋ ከተማ ተወልዳ ያደገችው፣ በ17 አመቷ ብሄራዊ ትያትርን የተቀላቀለችው፣ ዘፋኝ፣ ዳንሰኛ፣ የፊልም ተዋናይት፣ የውዝዋዜና የዳንስ አሰልጣኝ የሆነችው… በተለያዩ ሃገራት በተለይም በአውሮፓ ጥንቅቅ አድርጋ ኢትዮጵያዬን በጥበብ ስራዎቿ የምታወድስልኝ ምንይሹ ክፍሌ ለ’ኔ የባሕል አምባሳደሬ ናት!…

“መባ” በተሰኘው የመጀመሪያ አልበሟ (Mosaique Vivant − 2002 ) በኔዘርላንድ፣ በጀርመን፣ በቤልጂየም እና መሰል የአካባቢው አገሮች ዝናን ያተረፈችው፣ በተገኝችባቸው መድረኮች ሁሉ የአገራችንን የተለያዩ ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ሌሎች ገጽታዎች ለማስተዋወቅ የማትደክመው ምንይሹ በ’ርግጥም ለ’ኔ የባህል አምባሳደሬ ናት!…

ከኢትዮጵያ፣ ከማሊ፣ ከሱዳን፣ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ከኔዘርላንድ፣ ከአሜሪካ እና ከሌሎች አውሮፓ አገራት በተውጣጡ ሙዚቀኞች ታጅባ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በሌላውም የአለም ክፍል ተደማጭነትን እንዲያገኝ (አለም አቀፋዊ መልክ እንዲኖረው) የበኩሏን ለማበርከት የምትዳክረው ምንይሹ በኔ ልኬት ደርጃ ከምሰጣቸው (ምንም እንኳ የሙዚቃ ባለሙያ በልሆንም − እንደ አድማጭ) የኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የሙዚቃ አምባሳደሮች አንዷ ናት!…

“ድሬዳዋ” በተሰኘው ሁለተኛ አልበሟ (Me and My Record 2008) በ2008 በአውሮፓ የዓለም የሙዚቃ ሰንጠረዥ ከምርጥ አስር አልበሞች አንዱ ለመሆን የበቃችው… በአማርኛ ከሚታተሙ የአገር ውስጥ የህትመት ውጤቶች በተጨማሪ በደች፣ በቱርክ፣ በጀርመን እና በሌሎች ሃገሮች በእንግሊዘኛና በየሃገሮቹ ቋንቋዎች በሚታተሙ ጋዜጦችና መጽሄቶች ስለሙዚቃዋ ዓለም አቀፋዊነት ከፍተኛ ሽፋን ያገኘችው ምንሹ በ’ርግጥም የሁልግዜም የባሕል አምባሳደሬ ናት!…

17 የተለያዩ አለም አቀፍ አርቲስቶች በተሳተፉበት፣ ስለ ዉሃ ብቻ በተቀነቀነውና በአለም ላይ ለሚገኙና በንጹህ ውሃ እጥረት ህይወታቸው በአጭር ለሚቀጭባቸው ህጻናት የንጹህ ዉሃ ያለህ ሁላችንም ያቅማችንን እናበርክትላቸው ዉሃ… ዉሃ… ዉሃ… ስትል ከሌሎች ዓለም አቀፍ አርቲስቶች ጋር ያቀነቀነችው ምንይሹ በግጥሙ መልዕክት ብቻ ሳይሆን በሙዚቃዊ ደረጃዋም ልቤን ታጠፋዋለችና ለኔ ከጥቂት ምርጦቼ አንዷ ናት!…

ሰላም ለህጻናት፣ ሸማኔው ደጉ፣ ዉሃ ዉሃ፣ ወሰንኩ፣ እንዲሁም የዲ የዲ በጉራጊኛ፣ ኤ ሃማማ በሲዳሚኛ፣ በወላይትኛ፣ በኦሮሚኛ እና በሌሎች የአገራችን ቋንቋዎች ስለ ባህሎቻችን ስፋትና ጥልቀት ለማስተዋወቅ የምትለፋው ምንይሹ፣ ቡና ቡና ስትል የቡና መገኛዋን ከፋ ደረጃውን በጠበቀ ሙዚቃ የምታወድስልኝ ምንይሹ፣ ከኢትዮጵያም አልፋ አፍሪካዬ ስትል ለአፍሪካ ያቀነቀነችልኝ ምንይሹ፣ በአፍሪካ ምድር ጦርነት ይቁምልን፣ ሰላም ይስፈንልን ስትል ጮክ ብላ ተምትጣራው ምንይሹ በርግጥም ለ’ኔ የሰላም አምባሳደሬ ናት!…

ከነ Oumou Sangare, Salif Keita, Angelique kidijo, ከነጂጂ እና ከሌሎች ምርጦች ጋር በአንድ መደዳ አስቀምጬ የማደምጣት ምንይሹ ለ’ኔ በርግጥ አምባሳደሬ ናት!… በቅርብ የሚለቀቀው “ጥቁር ቀለም” የተሰኘው አልበሟ እንዴት እንደናፈቀኝ…
ጥቁር ቀለም…

♫ … ዮጵያ… ኢትዮጵያዬ
…. ዮጵያ… ኢትዮጵያዬ…

ጥቁር ቀለም ፈሶ ምድርሽን ሲሞላው
በተራራ ሜዳ በጫካ በዉሃው
ልዩ ታሪክ ያለሽ የራሳችን ድርሻ
ኩራት የዘላለም ቅኔ ነሽ ሐበሻ . . . ♫

Love you Minyeshu …
http://www.minyeshu.nl/

 
Leave a comment

Posted by on December 25, 2012 in ስብጥርጥር

 

ሸማኔው በብሪትሽ . . .

♫. . . ሸማኔው ደጉ … british33
ጠንካራው ብርቱ …
ኩሩ ባህልህ …
መለያ እምነትህ …
‘ማያልቅ ፈጣራህ …
ሰርተህ በዓለም …. ይታወስ ሞያህ …
ድብቅ ውለታህ …

ኦሆ ሸማ… ሸማ . . .
ኦሆ ሸማ… ሸማ . . .

. . . ወገን ሸማኔ የወንዜ የአገሬ
የትውልድ ገጽታ አሻራ ታሪኬ . . . ♫

(ድምፃዊት፦ ምንይሹ ክፍሌ)

ከላይ የጠቀስኩትን የምንይሹ ዘፈን በተደጋጋሚ ብሰማውም ከመደበኛ አድናቆት በዘለለ ለስሜቴ እጅግ ቅርብ ሆኖ ግጥሙን በወግ ያብሰለሰልኩበት ጊዜ ትዝ አይለኝም፣ እንዲሁ ምንይሹን ስለምወዳት አደምጠዋለሁ እንጂ!… (ሰፊው ህዝብ ግን ምንይሹን ይወዳት ይሆን? እምብዛም ስትንቆለጳጰስ አንሰማም:: ግን እኮ የምሩን ምርጥ ናት… ውይይ ጭፈራዋ ይምጣብኝ!… የኔ የባሕል አምባሳደር!… ስላንቺማ በሰፊው ነው መጻፍ ያለበት!… ስወድሽ፣ ሳደንቅሽ፣ ሳከብርሽ!)… ብቻ ዘፈኑ ውስጤ ዘልቆ ይሰረስረኝ የገባው በታላቋ ብሪታኒያ መዲና የሚገኘውን ብሪትሽ ሙዚየም ስጎበኝ ነው…

“ደግሞ ብሪቲሽ ሙዚየምና የሸማኔ ዘፈን ምን አገናኛቸው?!… ሽሮ ሜዳ የሄድክ መሰለህ እንዴ?!… አይ የባላገር ነገር የማይመሳሰለው ነገር ሁሉ ይመሳሰልበታል እኮ!” ብሎ የሚሳለቅ ከተሜ ከተገኘም ብሪቲሽ ሙዚየምም ሆነ እንዳጋጣሚ ያየኋቸው የስልጡኗ አውሮፓ ከተሞች ያመላከቱኝ ነገር ቢኖር ባለገርነትን አበክሮ ማየት፣ ማንነትን አብጠርጥሮ መለየት ብሎም “ይሄ ነገር አይረባም!” ብሎ ማንኛውንም ነገር ያለመናቅ ለብልጽግናቸው ያበረከተውን የላቀ አስተዋጽኦ ነው፡፡ እናም እንዳሻኝ ሸማኔን እና ብርቲሽ ሙዚየምን እያዛመድኩ በየዋህ የብልጽግና ምኞት እቀጥላለሁ… ደግሞ ለምኞት!…

 
ብሪትሽ ሙዚየም . . .

ብሪትሽ ሙዚየምን መጎብኘት በ’ርግጥ ዓለምን ጥንቅቅ አድርጎ እንደ መጎብኘት ነው ብዬ በድፍረት ብናገር የተለያዩ የዓለም ክፍላትን ባለመጎብኘት ምክኒያት የመጣ ግልብ ድምዳሜ ነውና መቻል ነው እንግዲህ!… በበኩሌ ግን ዓለምን ጎብኝቼ ተመልሻለሁ፡፡

የዛሬ 260 አመት የተቋቋመ፣ 250ኛ አመት የልደት በአሉን የዛሬ ዘጠኝ አመት ገደማ ያከበረ፣ በዓለም የመጀመሪያው በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀ ሙዚየም የተባለ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የጉብኝት እቃዎችን የያዘ፣ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በየአመቱ በአምስት ሺህ ሰዎች እንዲሁም አሁን ባለንበት ዘመን ስድስት ሚሊዮን በሚገመቱ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች የሚጎበኝን ሙዚየም መጎብኘት… ለኔ ብጤው ዓለምን ቀርቶ አለሙን ላላየ ዓለምን ጎበኘሁ ብሎ ቱሪናፋውን ቢነፋ አይገርመኒ ብላችሁ ማለፍ ነው እንግዲህ …

ብሪቲሽ ሙዚየም ሲባል የእንግሊዝን ጀብዱና ታሪክ ብቻ የሚዘክር የእንግሊዞች ሁለንተና ጥርቅም የተሞላበት አዳራሽ የሚመስለው ሰው ካለ በርግጥ ያ ሰው ልክ እንደ’ኔ ተሞኝቷል… ሙዚየሙ ያልያዘው የዓለም ጉድ የለም፡፡ የግብጾች፣ የሜሶፖታሚያ፣ የግሪኮች፣ የፐርሺያኖች፣ የጃፓኖች፣ የኮሪያዎች፣ የቻይናዎች፣ የአፍሪካዎች… ኧረ የስንቱ ስልጣኔና ቅርስ ተኮልኩሏል መሰላችሁ… የሰአት ታሪክ፣ የመገበያያ ገንዘብ ታሪክ፣ የጦርነቶች ታሪክ ስንትና ስንት ታሪክ ታጉሮበታል መሰላችሁ… ሙዚየሙን ጥንቅቅ አድርጎ ለመጎብኘት ቢያንስ አንድ ሳምንት እንደሚያስፈልግ የሙዚየሙ ጥናት ያመላክታል፡፡ ታዲያ እኔ ከሦስት ሰአታት ባልበለጠ ጉብኝቴ ስንቱን ላወራ ይቻለኛል?… እንዲሁ በወፍ በረር የቃረምኳትን ልተንፍስ እንጂ …

የአፍሪካ ጨርቃጨርቅ . . .

አፍሪካ የሚል ስያሜ የተሰጠው አዳራሽ የሚገኘው በታችኛው የሙዚየሙ ክፍል ሲሆን ደረጃውን ስወርድ “ለምን ታች አደረጉን? ያው አሁንም ካለም መጨረሻ ናችሁ እያሉን ይሆን?” እያልኩ ነገር እየፈተልኩ ነበር… ከዉስጥ ዘልቄ ስዘዋወር፣ የተለያዩ የአፍሪካ አገራትን አልባሳትና ልብሶቹ የሚሰራባቸውን ሁኔት ከተለያዩ መግለጫዎች ጋር ስጎበኝ “የደጉ ሸማኔ” የስራ ውጤት የሆነችው ጥበብ ዉበቷን ተጎናጽፋ ኢትዮጵያዬን ተሸክማ አገኘኋት… ውይ ደግሞ ማማሯ፣ ውይ ደግሞ ዉበቷ… ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አልባሳት ጋር ተሰልፋ ሳያት ስሜቴ ተደበላለቀብኝ… እንዲሁ በደመንፍስ የምንይሹን ዘፈን ማንጎራጎር ጀመርኩ… ከስልኬም ከፈትኩት፣ ጆሬዬም ላይ ሰካሁት፣ እጅግ የበዛ ትርጉምም ሰጠኝ…
እውነትም የትውልድ ገጽታ… እውነትም የታሪክ አሻራ… እውነትም የማንነታችን መታያ ስል ሸማኔዎችን አከበርኩ… ምንይሹንም አመሰገንኩ…

♫ . . . ወገን ሸማኔ የወንዜ የአገሬ
የትውልድ ገጽታ አሻራ ታሪኬ . . . ♫

በባህል…
__ ኮርተን እንድንታይ አ’ርገህ
በብሔር…
__ ባንድነት ልንዋብ ጥረህ
ገበናን…
__ ሸፍነን ኖረን አጥርተን
እምነትን…
__ በቀለም በጥበብ አፍርተን . . . ♫

♫ . . . መስቀላይ ሀሹ
ኡፋይሲ ሀሹ
ኦቶራ ኦቶ መኖራ አቀና…
መፃቤሳ … አሶሳ መኖራ ቀና
ኡፋይ … አሶሳ መኖራ ቀና . . . ♫
(የቋንቋው ባለቤት የሆናችሁ ብታርሙት ትችላላችሁ… ካበላሸሁት)

አብዲ ሰዒድ
2005 E.C

 

 
Leave a comment

Posted by on December 24, 2012 in ስብጥርጥር

 

ሸበላው በሼፊልድ (2) . . .

በንግሪቭ አደባባይ . . . sheffield

በእንግሊዟ ደብረሲና (ሼፊልድ) ከሸበላው ጋር መጀመሪያ የሄድነው ወደ በንግሪቭ አደባባይ ነበር፣ ይህን አደባባይ በርን ግሬቭም ይሉታል አሉ፡፡ እናም እንደደረስን ግራ ይገባኝ ጀመረ… ግራ መጋባቴን የተገነዘበው ሸበላው “እሺ ሸበላው መርካቶ አብዱ በረንዳ የመጣህ መሰለህ አይደል?” ቢለኝ… “አይ የለም ሲኒማ ራስ ነው የመሰለኝ” ሳቅ እያልኩ…

ያለምንም ማጋነን በርግጥ ሸገር የገባሁ ነው የመሰለኝ፡፡ ከሸገርም ቅልጥ ያሉ ጫትና ጥቃቅን ነገሮች መቸርቸሪያ ሰፈሮቿ የደረስኩ ያህል ነው የተሰማኝ… ታላቋ ብሪታኒያ ስለሚገኙ መቃሚያ ቤቶችና በእንግሊዝ ምድር ጫት መነገድም ሆነ መቃም ያልተከለከለ ስለመሆኑ የሰማሁ ቢሆንም በለምለም ኮባ ቅጠል የተጠቀለለ… የሸገርን ጫት ነጋዴዎች ሊቀታተር የሚችል ትኩስ ጫት በክብር እና በግርግር ሲሸጥ ያጋጥመኛል ብዬ ፈፅሞ አልገመትኩም!… በወግ የተስተካከለ መጅሊስ ያለበት መቃሚያ ቤት አገኛለሁ ብዬማ ፈጽሞ አልጠረጠርኩም!… ማንበብ ሌላ ማየት ሌላ ማለትስ ይሄኔ ነው…

የአካባቢው ድባብ፣ የቸርቻሪ ሱቆቹ ሁኔታ፣ የነጋዴዎቹ ባህሪ፣ ጫት ፍለጋ ገባ ወጣ የሚሉት ዲያስፖራዎች፣ የየመኒዎቹ ዎልፍና ትርምስ፣ የመስጂዱ የርቀት የአዛን ድምጽ፣ የዙሪያ ገባው ቆሻሻ፣ እዚም እዛም የወዳደቁት ፌስታሎችና ቆርቆሮዎች… ኧረ ምኑ ቅጡ ብቻ ምኑም አውሮፓ አውሮፓ አይሸትም! ሸገር ሸገር እንጂ፡፡ ከመጣሁባት ከወግ አጥባቂዋ ስውዲን ጋር እያነጻጸርኩ… ከእትብቴ ምድር ከኢትዮጵያዬ ጋር እያዋደድኩ መጠየቅ ጀመርኩ…

እኔ፦ ቆይ ግን ጫት እንዴት አልከለከሉም?!

ሸበላው፦ አይ ሸበላው! ለምን ብለው ይከለክላሉ?!… ዝም ድንዝዝ የሚያደርግን ነገር ለምን ይከለክላሉ?… ቃሚው ይቅማል ከዚያም ዝምም ብሎ ያኗኗር ዘይቤያቸውን በልምምድ ያውጠነጥናል… ታርጋውንና የተመዘገበበትን ታሪክ ያብሰለስላል…. ምን አደረገኝ ብለው ነው የሚከለክሉት?… አንድ ሰሞን ጫት ይከልከል ተብሎ ቆሞ ነበር አሉ ታዲያ አንዱ ሃራራ አናቱ ላይ የወጣበት ሱማሌ እዚሁ መሃል አደባባይ ላይ ቆሞ “አላህ ሃራም ያደረገውን ወንድና ወንድ መጋባት እየፈቀዱ ለምለም ቅጠል እንዴት ይከልክሉናል? ፋክ ኢንግሊዚ… ፋክ ኢንግሊዚ!” እያለ በጩኸት አቀለጠዋ…

እኔ፦ አሃሃሃሃሃ… ወይ ሱማሌ!… ቆይ ታርጋ ምንድነው? የምን ታርጋ?

ሸበላው፦ አገር ቤት መኪና ነው ታርጋ ያለው አይደል… እዚህ ደግሞ ላንተም መለያ ቁጥር ይሰጥሃል… ያው ታርጋህ እንደማለት ነው… ኮሽታህ ሁሉ ይመዘገብበታል… አለቀ:: ስለዚህ ወደድክም ጠላህም ነጋ ጠባ እርምጃህን ከታርጋህ ጋር ታዛምዳታለህ… የኛ የትራፊክ ፖሊሶች ታርጋ እየፈቱ ሾፌሮችን እንደሚያበሳጩት ሁሉ እዚህም ታርጋህ ላይ ጥቁር ነጥብህን እየለጥፉ ናላህን ያዞሩታል … ሲስተም ነው የሚሰራው የሚሉት ፈሊጥ እዚህ ነው የሚገባህ… አጀብ ነው አቦ!

እኔ፦ ያው በሁሉም የሰለጠኑ ሃገሮች እንደሱ መሰለኝ…. ብቻ ይገርማል…. ይህ ሰፈር ግን ነገሩ ሁሉ አገር ቤት አገር ቤት ይመስላል…

ሸበላው፦ ነው እኮ ነው ታዲያ!… ይህ ሁላ ሸበላ አንገቱ ላይ ስካርፕ ጠምጥሞና አለባበሱን ለውጦ ስታየው እውነት እንዳይመስልህ… ለመመሳሰል እኮ ነው… ልቡም፣ ግብሩም፣ ህልሙም እዛው ነው − እናቱ ቤት፡፡ የኛ ሰው አገር እንጂ አመል አይለውጥም!… ህዝባችን አህጉሩ እንጂ ግብሩ አይቀየርም!… በየሄደበት የራሱን አገር ይገነባል… ታዲያ ሌላውም ሰፈር እንዲህ እንዳይመስልህ… የቀለጡ የፈረንጅ ሰፈሮች አሉልህ…

እኔ፦ እሱስ ልክ ነህ…

ሸበላው፦ እንግዲህ ክተበው!… ለምን እዚህ ያመጣውህ ይመስልሃል?!… ሸበላው ወዳጃችን ትጽፋለህ ስላለኝ እኮ ነው!… አየህ ሰው ነው የሚጻፍ…. ስለ ሰው ነው የሚከተብ… እንጂማ ምድር ያው ምድር ነው… ግንብም ያው ግንብ ነው… ወላሂ የሚከትበን አጥተን እንጂ ስንት ጥራዝ ይወጣን መሰለህ… እስቲ ደሞ ወደ ሻምበል እንሂድ (መኪናውን እያሽከረከረ)…

ቀልደኛው ሻምበል . . .

በ1981 (እ. ኢ. አ) ስለተደረገው የከሸፈ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ… በጓድ መንግስቱ ሐይለማሪያም እና በጀነራሎቹ መካከል ስለነበረው ሽኩቻ… አያ መንጌ ከጀርመን ሲመለስ አየር ላይ እንዳለ እሱን አመድ አድርጎ አብዮቱን ለመቀልበስ ስለተዶለተው ያልሰመረ ዱለታ… ስለጀነራሎቹ ፍጻሜ እና ስለ ጦር ሰራዊቱ የተለያየ ውጥንቅጦች ከየመጽሃፍቱ ከመቃረም በቀር ክዋኔውን በቦታው ሆኖ የታዘበ አሊያም በከፊልም ቢሆን የታሪኩ አካል የሆነ ሰው ገጥሞኝ አያውቅም… ኧረ ያጋጥመኛል ብዬ አስቤም አላውቅ… በእንግሊዟ ደብረሲና ግን ቀልደኛው ሻምበል ጥርስ በማያስከድን ጨዋታው እያዋዛ ልክ ትላንት የተፈጸመ ያህል ሲተርከው ሳይ ወይ ስደት ስንቱን ይዞታል ብዬ ከመቆዘም ሌላ ምን ልል ይቻለኛል…

“አባቴ ያቺን ሰዓት” በሚል ርዕስ በደረጀ ደምሴ ስለ ሜጀር ጀነራል ደምሴ ቡልቶ (የጸሃፊው አባት ናቸው) የተጻፈውን መጽሃፍ የወጣ ሰሞን ማንበቤን አስታውሳለሁ… በጀነራሉ ቆራጥነት፣ ለአላማቸው ባላቸው ጽናት፣ ስለ ጦር ሳይንስ ባላቸው እውቀት መደመሜም ትዝ ይለኛል… አስመራ ከተማ ላይ ስለነበራቸው የመጨረሻ ሰአት ቆይታና ስለህወታቸው ፍጻሜም ያነበብኩት ባይኔ ላይ አለ… እሳቸው በተገደሉበት በዚያች ቅጽበት በቦታው ኖሮ በጆሮው ግራና ቀኝ ጥይት እያፏጨ… ፍጻሜያቸውን የተመለከት፣ የወጡበትን መኪና እስከነታርጋ ቁጥሩ፣ እስከነ ሞዴሉ፣ እስከነአለባበሳቸው፣ እስከነአወዳደቃቸው ፊልም በሚመስል መልኩ የሚተርክ ሰው ማግኘት ግን ከማንበብም በላይ ደስ የሚል ነገር ነው…

ስለ ሜጀር ጀነራል ቁምላቸው ደጀኔም ቢሆን ያው ስለ አብዮቱ ከተጻፉ መጻህፍት እንዳቅሚቲ ቃርሜያለሁ… እንዴት ከሞት እንዳመለጡ፣ እንዴት ጉራጌ አካባቢ እንደተሸሸጉ፣ እንዴት ከሃገር እንደወጡ በመጠኑ ለቃቅሜያለሁ፡፡ የሚኪሊላንድ ታሪክና የሳቸው ካገር አወጣጥ በርግጥ እንደፊልም መስጦኝም ነበር… የደብረሲናው ሻምበል ይህንንና መሰል ታሪኮችንም በሳቅ ፍርስ በሚያደርጉ የጦር ቤት እና የራሽያ ትምህርት ቤት ገጠመኞች እያዋዛ ተረከልኝ… በዚህ አጋጣሚ ምነው ግን ፊልም ሰሪዎቻችን እኒህን ታሪኮች ቢሰሯቸው!… ቀን ከሌት የምናየውንና የምንኖረውን ኑሮ እየደጋገሙ ከሚያሰለቹን እኒህን እና መሰል ታሪኮች ጣል ቢያደርጉልን ይጣፍጥላቸው ነበር… እግረ መንገዳቸውንም ለትውልድ ታሪክ ያስተምራሉ እኮ… (ጥቆማ መሆኑ ነው እንግዲህ… በኛ ቤት ጠቁመን ሞተናል…)

ስለ ኢትዮ ኤርትራ ጦርነትስ ቢሆን በወቅቱ አገር ቤት በግል ስራ ተሰማርቶ ይኖር የነበረው ሻምበል ካለበት ተፈልጎ ተጠርቶ ጦሩን እንዳገለገለ ሲነግረኝ ተገርሜም አላባራሁ… “ከውትድርና ህይወት የራቀ ሰላማዊ ኑሮ ውስጥ ለአመታት ቆይቶ ወደ ጦርነት መመለስ አይከብድም?” ስል እንደዋዛ ለጠየቅኩት ጥያቄ የመለሰልኝ ግን በአእምሮዬ ይመላለሳል…. “እንዴ!… የጦር ባለሙያ እኮ ዋና ተግባሩ አገር መጠበቅ ነው… እኔ አሁንም ቢሆን አገርን የሚነካ ነገር ከመጣ ዛሬም እሄዳለሁ… ያቅሜን ላገሬ ለማበርከት አላንገራግርም…. ጉዳዬ ከአገር እንጂ ከማንም አይደለም… ይሄ ደሞ እኔ ብቻ ሳልሆን ማንኛውም የጦር ባለሙያ የሚጋራው ነው:: የሚያሳዝነው ግን ከዚያ ሁሉ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከንቱ እልቂት በኋላ ባለስልጣን ተብዬው የድሮ የጦር ባለሙያዎች ስላደረጉት እገዛ ሲጠየቅ ሽምጥጥ አድርጎ የ’ኔንና የመሰሎቼን ውለታ ከመካዱም በላይ ʻምን አብዛኛዎቹ እንኳን ለዚህ አላማ ቀርቶ ራሳቸውንም ማገዝ አይችሉም!ʼ እያለ ከንቱ መሳለቅ ሲሳለቅ ስትሰማ ያምሃል”…. ወይ ሻምበል!

ብቻ በዚህም ተባለ በዚያ የዚህ አይነት ሰዎች የታሪክ ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ ለታሪክ ጸሃፊዎችም የሚያበረክቱት ሚና ቀላል አይደለም… በየሃገሩ በርካታ ተመሳሳይ ሰዎች እንደሚኖሩም እሙን ነው፡፡ ምነው በሰላም ተሰባስበው… በዳይና ተበዳይም ይቅር ተባብሎ ለቀጣይ ትውልድ ታሪካቸውን በቀናነት ቢያካፍሉን ስልም የየዋህ ምኞቴን እየተመኘሁ ሸበላውን አየሁት… መደዱን ይቀጥልልኝ ያዘ . . .

እህሳ ሸበላው
አያዋ ጎምላላው
እንግዲህ ክተበው በል ጣፈው አደራ
አንዳች ቢያስተላልፍ ለወዲያኛው ጭፍራ. . .

ኡመቱ በሞላ
እንዲሁ ሲጉላላ
ደጅ ደጅ እንዳየ ውጪ ውጪ እንዳለ
ህልሙን ህልም በላው ቀኑን የትም ጣለ
እስቲ አላህ ያግራው ቀኝ በቀኝ ያ’ርግልን
ምቀኛ ሸረኛን ምንገድ ያስቀርልን. . .

ሸበላው ሸበላው ሸበላው ወዳጄ
መቼም ወገኔ ነህ መከታ ቀኝ እጄ
አንተ ትብስ አንቺ ብሎ እየተነሳ
በደቦ እንዲደቃው የቂምን ነቀርሳ
አሚን በል ዘመዴ ብርቱ ዱዓ አለብን
እምዬና ህልሟ ከንቱ ዳይቀርብን. . .

 

አብዲ ሰዒድ
2005 E.C

 
2 Comments

Posted by on December 19, 2012 in ስብጥርጥር

 

ሸበላው በሼፊልድ (1) . . .

ሸበላው ሸበላው፣ ሸበላው ዘመዴ
የወንዜ ኮበሌ አያ እንዴት ነህ ጓዴ?!sheffield
እስቲ አሏህ ያግራው ቀኝ በቀኝ ያ’ርግልን
ምቀኛ ሸረኛን ምንገድ ያስቀርልን . . .

ያኛው በስንቱ ጉድ ሲያራኩተን ከርሞ
አሰብን ሊሻገር ሌላው መጣ ደግሞ
መገን ያገሬ ሰው ተው በሉት ያን ከንቱ
አጉል አትራቆት ያች ምስኪን እናቱ . . .

የዋዛ እንዳይመስልህ ያ የጨው በረሃ
ስንቱን አቅልጦታል እያሰኘ ውሃ
እንጂማ ማን ጠልቶ 
ሁሉ ልቡ ፈርቶ 
በስጋት ተብላልቶ 
እንጂማ ማን ሸሽቶ ከጋራ ገበታ
ዳህላክ ውጦት እንጂ የተስፋውን ሽታ . . . 

ሸበላው ሸበላው፣ ሸበላው ዘመዴ
እንኳን ደህና መጣህ አያዋ መውደዴ
በል ተነስ ላስጎብኝህ ይቺን “ደብረሲና”
በእንግሊዝ ምድር የህልሜን መዲና . . .

በሃገረ እንግሊዝ በሼፊልድ ምድር ላገኘሁትና በቀልድ እያዋዛ አክራሞቴን ከሌሎች ፍቅር ከሆኑ ወዳጆች ጋር ላጣፈጠልኝ ሸበላው ጓዴ የተገጠመ፡፡ ሸበላው፣ ሃጂ፣ ሻምበል፣ ጆኒ እንዲሁም ፍቅር አቅርበው፣ ፍቅር መግበው የማይሰለቻቸው እህቶቻችን ሰላማቸው ይበዛ ዘንድ በደብረሲና አድባር እየተለማመንኩ እስቲ ትንሽ የቃረምኩትን ላጫጭስላችሁ…. ልክ እንደቡናቸው ጭስስስስስስ… 

ወይ ስደት፣ ወይ ኑሮ፣ ወይ ህይወት፣ ወይ ታሪክ፣ ወይ ጦርነት፣ ወይ ጥበብ፣ ወይ ETV፣ ወይ ESAT፣ ወይ መሌ፣ ወይ ሐይሌ፣ ወይ መንጌ፣ ታጋዩ፣ አታጋዩ፣ ተታጋዩ ስንቱን አነሳን ስንቱን አፈረጥነው… በጉንጭ አልፋ ክርክር ሳይሆን ለዛ ባለው የጨዋታ ወግ… ጉዞዬ የብልጭ ድርግም ያህል ቢሆንም ዳግም ልመለስ ቀጠሮ አለኝና ጥቂት ከማለት አያቦዝነኝም… 

ሼፊልድ ከስምንት ታላላቅ የእንግሊዝ የክልል ከተሞች አንዷ ስትሆን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይኖርባታል፡፡ ከ 13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በገበያ ማእከልነት ስታገለግል የቆየች ቢሆንም የከተማነት ካባዋን ተከናንባ ታፍራና ተከብራ መኖር የጀመረችው የዛሬ 120 አመት ገደማ እንደሆነ ስጎለጉል ያገኘሁት መረጃ ይገልፃል፡፡ በኢንዱስትሪና በብረታብረት ምርቷ የምትታወቀው ሼፊልድ በሁለተኛው የአለም ጦርነት የጦር መሳሪያ አምራችም ነበረች… በምላሹም የቦንብ ውርጅብኝን አስተናግዳለች… ያኔ ለሞተባቸው መጽናናትን ይስጥልን… አሁን ነዋ እኛ ለቅሶ የደረስነው!… aha… 

የከተማዋ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ ገደላማ ነው በዚህም ያገኘኋቸው ወዳጆቼ ሼፊልድ የሚለውን የኢንግሊዝ ስያሜ በአገርኛ ለውጠው ደብረሲና እያሉ ነው የሚጠሯት… የደብረሲናን ዋሻ ከተሻገርኩ በኋላ በሚምዘገዘገው የአንበሳ አውቶቡስ አቧራም፣ እድሜም የጠገቡትን የደብረሲና ከተማ ቆርቆሮዎች እየታዘብኩና እየቆዘምኩ ቁልቁል እንደወረድኩት ሁሉ የእንግሊዟንም ደብረሲና በናሽናል ኤክስፕሬስ ባስ እየተገረምኩ ቁልቁል ወረድኳት… የዚህኛው ጉዞ ላይ ግን የደብረሲና ቆሎ ቸርቻሪ ኮረዳዎች የሉም… እነዚያ ፍልቅልቅ አበባዎች አይታዩም!… “ቀዮ ቆሎ ተጋበዝልኝ”… “ቀዮ ጦስኝ ውሰድማ”… “ቀዮ ብርትኳን”… “ቀዮ መንደሪን”… “ቀዮ ቆሎ… ግዴለም ተጋበዝ… ስትመለስ ትከፍለኛለህ”… ሲሉኝ አይሰማኝም… ከባስ ወርጄ በዱክትርና መርሃ ግብር ትምህርቱን ሊከታተል ሼፊልድ ከከተመው አብሮ አደግ ወዳጄ ጋር ከተገናኘሁና ሸበላውን ከተዋወቅኩ በኋላ ግን ቆሎ ቸርቻሪ ኮረዳዎቹን ብቻ ሳይሆን ህዝቤን ከነዘዬው አገኘሁት… አይ ሸበላው…

ከሸበላው ጋር እንቀጥላለን… ይቀጥላል . . .

 
Leave a comment

Posted by on December 16, 2012 in ስብጥርጥር

 

እ – መ – ጣ – ል – ሻ – ለ – ሁ . . .

ውሃ እንደ አቧራ ባይኔ እየቦነነwinter pic
እልፍ እፍኝ በረዶ ጉንጬ እየዘገነ
እጅ እግሬ ደንዝዞ
በቆፈን ተይዞ
ደጁ እንደ መርግ ከብዶኝ ከቤት ብውል ባድርም

አንቺማ ጠርተሽኝ በፍፁም አልቀርም! . . .
ኧረ እንዴት፣ ኧረ እንዴት፣ እኮ እንዴት ‘ቀራለሁ?!
በረዶ ለብሼ፣ በረዶ ጎርሼ እመጣልሻለሁ!

ሰሚኝማ ውዴ …
ቅድም ና ብለሽኝ በሳይክል ስጣደፍ
አቅሌን ነፍሴን ስቼ በረዶው ላይ ስከንፍ
የነጠረው ውሃ ጎማዬን አዳልጦ
ፍቅርሽን ያዘለው ነፍሴ ተፈጥፍጦ
እኔና ሳይክሌ እዚህና እዚያ ወድቀን
በሽራፊ ሰከንድ ላመት ተራርቀን
ጉልበት ወኔ ከድቶን ተሰብረን ተጨንቀን
በጭንቁ በርትቼ
የተረፈ አካሌን ለቅሜ ጎትቼ
ስወድቅ ስነሳ እመጣልሻለሁ
አንቺ ና ብለሽኝ እንዴት ‘ቀራለሁ?!

ኧረ እንዴት፣ ኧረ እንዴት፣ እንዴት ይቻለኛል?!
በረዶ ጎርሼ፣ በረዶ ለብሼ መምጣት ይቀለኛል . . .


ስሚኝማ ፍቅሬ …

መኪናዋም በርዷት ባሱም ተጎትቶ
ወዳንቺ መምጫዬን ጊዜዬን ሰውቶ
ሰማይና ምድሩ፣
ዛፍና ቅጠሉ፣ በነጭ ተሞሽሮ
ነፍስ እያስቆዘመ ቅልጥፍናን ሽሮ
እያስተካከዘ ቢያነጫንጨኝምወዳንቺ ከመክነፍ ከቶ አያስቀረኝም . . .

ኧረ እንዴት፣ ኧረ እንዴት፣ እኮ እንዴት ‘ቀራለሁ?!
በረዶ ጎርሼ፣ በረዶ ለብሼ እመጣልሻለሁ! . . .

ስሚኝማ ፍቅሬ …
እኔነቴ ማሬ …
በጓንት በካፖርቱ በኮፍያው ታጅሎ
ዘንካታው ቁመናሽ ኩርምት ክትት ብሎ
የፊትሽ ወዘና በበረዶው ረግፎየውበትሽ ፀዳል ከራማው ተገፎ
የጎዳና ገጽሽ ጀንበሩ ቢጠልቅም
ʻከቡትስሽʼ ላይ ጣለኝ ፍቅር ጉዱ አያልቅም…

አወይ መውደድ አወይ
አወይ ፍቅር አወይ
እስቲ አሁን በሞቴ ጫማ ይወደዳል ወይ?!…
ቢወደድ ቢጠላ እኔ ምን ተዳዬ
እንኳን መልክሽ ቀርቶ ʻቡትስሽʼ ነው ገዳዬ…

“ገዳዬ ገዳዬ… አንቺ ልጅ ገዳዬ”
ጎጆሽ የተሰራ በሁለመናዬ
ህይወት ማስቀመጫ የክብር ሙዳዬ . . .
“ገዳዬ ገዳዬ… አንቺ ልጅ ገዳዬ”
መጣሁ ተቀበይኝ ማሬ ወለላዬ . . .

(© አብዲ ሰዒድ፤ 2003 E.C)

 
Leave a comment

Posted by on December 2, 2012 in ግጥም