RSS

ዘ – መ – ቻ !

09 Jan

አያቴ ኮርያ ዘማች ነበር። እናቴ ቡና አፍልታ መንደርተኛው በተሰበሰበ ቁጥር ምክኒያት እየፈለገ ስለ ኮሪያ ማውራት ይወዳል።

<< እኛኮ ለዓለም ኩራት ለሃገርም ክብር ነን!… እዚህ ተጥለን ብንታይ ዝናችን የተረሳ እንዳይመስላችሁ… በሄድንበት ያገራችንን ስም ከፍ አድርገን ኒሻን በኒሻን ተምነሽንሸን… በሊጎፍኔሽን አርማ ደምቀን… ባገራችን ባንዲራ አሸብርቀን… የተመለስን ጀግኖች ነን!… አታዩትም ግርማ ሞገሴን!>>… እያለ ያቺን ለዘመናት ያየናትን ጥቁር ፎቶ ያሰየናል… አያቴ ሙሉ የጦር ልብሱን ገጭ አድርጎ የለበሰባትን ፎቶ…

እውነቱን ነው!… አያቴ ያምራል… ግርማ ሞገሱ ያስፈራል… ቆራጥ አመለካከቱ ያስደነብራል… እንዲህ አርጅቶ እንኳ አትንኩኝ ባይ ነው… እማዬ ለምን ይሄን ፎት ፊት ለፊት እንደሰቀለችው ግልፅ ነው…. አያቴ ምንም ከምታደርግለት የጥንት ፎቶውን እያየህ ስለ ኮሪያ ብትጠይቀው እንደወደድከውና እንዳከበርከው ይረዳሃል… “አረጀህ፣ ደከምክ፣ አረፍ በል፣ ተኛ ፣ተነስ…” ምናምን ልትለው ብትሞክር ግን ይጣላሃል.. “ወግድልኝ!… የኮሪያ ዘማች እኮ ነኝ”… እያለ ይሸልልብሃል… ከቶም እጅ አይሰጥም!… ቆራጥ… በራሱ ብቻ መቆም የሚሻ ደፋር ሰው ነው… ብልጧ እናቴም ይህን ባህሪውን ጠንቅቃ ስላወቀች ተጠቅማበታለች… ባይሆንማ አያቴ እንደሞተ ፎቶውን አታነሳውም ነበር… እሺ ከዚያ በኋላ ፎቶው የት ገባ?!… ያያቴ ፎቶ የት ደረሰ?!… ያን ምርጥ ታሪካዊ ፎቶ ምን ወሰደው?…

<< እንደው ማማሩስ ጥርጥር የለው… መቼም ያላዩት አገር የለ… ይሄ መቼ መሆኑ ነው ታዲያ?>> ይጠይቃሉ የጦቢዬ እናት… አያቴም ፊቱ በደስታ እየፈካ… ቡናውን በፍቅር እያጣጣመ… ኮሌታውን እያስተካከለ… አፉን በእጁ እየሞዠቀ ይመልሳል…

<<ይሄማ ከዘመቻው ቀደም ብሎ ነው… በግርማዊነታቸው ቆራጥ ንግግር “ቃኘው ሻለቃ” አርማውን ከዣንሆይ እጅ ተቀበሎ በተሸኘ ጊዜ… አይ ዣንሆይ!… ያደረጓት ንጥር ያለች ንግግር!… የዋዛ ንግግር እንዳይመስላችሁ… ዣንሆይ እንዲሁ በከንቱ ቃል አያባክኑም… ሁሏም ቃላቸው ፍሬ አላት… እስታሁን እንኳ መልክታቸው አይዛነፈኝም>>

ሬዲዮኑን አስተካክሎ እያስቀመጠ ይቀጥላል… አያቴና ሬዲዮ ተለያይተው አይቼ አላውቅም… የዜና ፍቅሩ ሁሌም እንደገረመኝ ነው… በሄደበት ሁሉ በካኪ ጨርቅ የተሸፈነችው ሬዲዮ ከእጁ አትጠፋም…

<< እናላችሁ በተጠንቀቅ ለተዘጋጀነው የቃኘው ሻለቃ አባላት በሙሉ የጦር አርማውን እያበረከቱ ዣንሆይ እንዲህ አሉ… ‘ይህንን የጦር መለዮ ዓላማ በምታደርጉበት ጦርነት ሁሉ በጀግንነት ከፍ አድርጋችሁ ትይዙታላችሁ።… ለኢትዮጵያ ነፃነት ከብዙ ሺህ ዓመት ጀምሮ የተጋደሉት ጀግና አባቶቻችሁ መንፈስ ይከተላችኋል፤ በጦር ሜዳ ክንዳችሁን ያፀናል፤ ልባችሁንም ያበረታል!’…>>

<< እውነት ነው ጀግንነት ከደማችን ነው ሐበሻ ተደፍሮም አስደፍሮም አያውቅም>> ጣልቃ ይገባሉ እትዬ ሸጌ…

<<ታዲያሳ!… መይሳው ካሳም ቢሆን ያን የንግሊዝ ጭባ ሁላ እያዳፋ መድፍ ሲያስቀጠቅጠውና ወባ እንደያዘው ቆለኛ ሲያንቀጠቅጠው ነው የኖረ… ምኒሊክም ቢሆን ያን ሶላቶ ጣልያን በዱር በገደሉ ሲያርበደብደው ነው የከረመ… ጥበበኛዋ ጣይቱም ብትሆን ለአርበኛው ጠጇን እያስጣለች ሶላቶውንና ባንዳውን ውሃ ውሃ እያሰኘች በእንፉቅቅ ያስኬደች ጀግና ናት… አባቴ ራሱ በሚኒሊክ ጊዜ አርበኛ ነበር… ስንቱን ያርበኛ ጀብዱ እንዳጫወተኝ ባወጋችሁ ዘበኑም አይበቃን>> …

አያቴ ላፍታ በዝምታ ትንፋሽ እየወሰደ ይተክዛል… በትዝታ አባቱን እያሰባቸው ይሆናል… የቡና እድምተኛም በጉጉት ይጠባበቃል… አያቴ የሚነግረን ታሪክ ተመሳሳይ ቢሆንም አይሰለችም… እሱ ሲያወራው የሆነ እንዳይሰለች የሚያደርግ ነገር አለው… ሁላችንም በጉጉት እንዲቀጥል እንጠብቃለን… አያቴም ቤቱን ገርመም ገርመም አድርጎ ጨዋታውን ይቀጥላል …

<< እኛም ታዲያ ጀግኖች አባቶቻችንንም ሆነ ዣንሆይን አላሳፈርንም!… ሃገራችንንም በሽንፈት አላስጠራንም!… በተሰለፍንበት ውጊያ ሁሉ አልተበገርንም… አንድም የቃኘው ወታደር እጁን አልሰጠም!… ከ16 ሃገራት የተሰበሰበው ተዋጊና አዋጊ ሁላ እኛን እንደ ተአምር ነበር የሚያየን… ‘ኢትዮጵያውያን ከሰው ፍጡር በላይ ናቸው’ እስከመባል ድረስ ተደርሶ ነበር… በዚያ መሳይ ከባድ ውጊያ ባጠቃላይ በክብር የተሰዋው የቃኘው ወታደር 120 አይበልጥም… ቁስለኛውም ቢሆም ከሌላው አንፃር ሲታይ እምብዛም ነው!>>

የአያቴን በወኔ የተሞላ ንግግር በገብረ ክርስቶስ ግጥም እያወራረድኩ… እኔም አብሬው ዘምቼ እመለሳለሁ…

“… ደስታና ሐዘን በቦታው ጨፈሩ
ሣቅ ለቅሶ እየሆነ እምባ ሄደ በግሩ
በያይነቱ ኒሻን ጠመንጃ ሸክሙ
ወቴ ከነደሙ
እዚህ ይዞ መጥቷል ከሩቅ ከኮሪያ
ተቃጥሎ ይጋያል የባቡሩ ጣቢያ
. . . . . . . . . ብቻ እዚህ አይደለም…”

ከዘመቻ ሲመለስ ባቡር ጣቢያ ሄጄ የተቀበልኩት ያህል ይሰማኛል… ሁሌም ትረካው እንደተዋሃደኝ ነው…

<<አንቱ እንደሁ እድለኛ ኖት… በደጉ ዘመን ሁሉን አሳልፈዋል… ጥጋቡንም ዓለሙንም እስኪበቃዎት አይተውታል… ምን ቀሮት እቴ!>> እማማ ዘኔ ናቸው…

<<ይመስገን… ይመስገን… ደግሞ አንቺስ ብትሆኚ ምን ቀረሽና ነው… ኮሪያ ባትዘምቺም መቼም ከኮሪያ ዘማች ጋር ሳትኮምሪ አልቀረሽም… እሱም ቢሆን ዝና ነው እኮ… እኛ እንደሁ ብርቅ ነበርን… አሃሃ… ጥጋቡንማ ተይኝ!… ዣንሆይ እኮ በችጋር ለተጎዱትና ይልሱት ይቀምሱት ለቸገራቸው የፓኪስታን ዜጎች አይዟችሁ እግዜር እንደሰጠን እንሰጣችኋለን ብለው ረብጣ ዶላር ለሩዝ መግዣ ይሰዱላቸው ነበር!>>

<<እንዴ አባ ኢትዮጵያ እርዳታ ትሰጥ ነበር እንዴ?!>> እጠይቃለሁ እኔ

<<ኋላስ!… ስንቱን ረሃብተኛ ከረሃቡ ታድጋው የለ እንዴ!… ስንቱን ችጋራም አርጥባው የለም እንዴ!… ምድራቸው እህል አላበቅል ሰማያቸውም ውሃ አላፈስ ብሎ በረሃብና በቸነፈር ሲቀጣቸው አይዟችሁ ብላ የለም እንዴ!… ስማ ልጄ! ይህች ለምለም ሃገር እኮ ታላቅ ናት!… ዛሬ ተራቁታ ብታያት የዋዛ እንዳትመስልህ… በወስላቶች ዝርፊያ የደኸየች ቢሆንም ሃብታም ነበረች…. ደግሞም ዳግም ማበቧ አይቀርም!>>

የአያቴን በተስፋ የተሞላ ንግግር እያዳመጥኩ… እርዳታ አድራጊዋን ኢትዮጵያ እየታዘብኩ… እማዬ ከሱንከሞ ሱቅ ለቡና ቁርስ እንዲሆናት (በአቋራጭ ምሳም ይሆናል) በብድር ያስመጣችውን ሽንብራ እየቆረጠምኩ… (ግን መቼ ልትከፍለው ነው? ከየት አምጥታ ልትከፍለው ነው? – እሱን አላህ ነው የሚያውቀው)… ለአያቴ ይልሰው ይቀምሰው ያላተረፉለትን ዣንሆይና አያቴ ለሳቸው ያለውን ክብር እያሰላሰልኩ… አንድ የመርቲ ጣሳ የጉድጓድ ውሃዬን ጭልጥ አድርጌ ጠጥቼ (ሆዴ እየተንቦጫቦጨ) ወጣሁ… እኔም ወደ ዘመቻዬ በምንጋ ተመምኩ…

እነሆኝ አደግኩ!
እነሆኝ የኔ ዘመቻ!

… የበደሌ ዘመቻ!
… … የኮካ ኮላ ዘመቻ!
… … … የቀ እና ቐ ዘመቻ!
… … … … የለ እና ሌ ዘመቻ!

ቻ! ቻ! ቻ!
ከንቱ ብቻ!

አጁዛ አለ አዳም ረታ!
እውነትም አጁዛ!

Image

 
1 Comment

Posted by on January 9, 2014 in ስብጥርጥር

 

One response to “ዘ – መ – ቻ !

  1. Nebyu andualem

    December 25, 2018 at 6:44 am

    ዋው ወንድም አለም ሳላደንቅህ አላልፍም ሁሉም እንዳንተ ቢስብ እና ሃሳቡን በተሰጠው ተሰጦ ቢገልፅ የት በደረስን ።
    ፈጣሪ ይባርክህ

     

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: