.
በማዲባ ምድር፣ በአቦይ ማንዴላ፣
በፈርጡ ስቴዲየም፣ በዚያ በ’ምቦምቤላ፣
ያ ሆ በል! ያገር ልጅ፣ በል የ’ርግብ አሞራ፣
ለኩራት ለክብርህ፣ ለእትብትህ ባንዲራ፡፡
ጉሮ ወሸባዬ፣ ጉሮ ወሸባዬ፣
ቀና በይ ካንገትሽ፣ እናት ኢትዮጵያዬ፣
ዝናሽ ያንሰራራ፣ ክብርሽ ይድነቃቸው፣
የከርሞ ታሪክሽ፣ ሃይል ይሁን ስንቃቸው፡፡
በቼልፊኮ ጫማ፣ እግር እየደማ፣
በእናት አገር ፍቅር፣ ልብ እየተጠማ፣
ስንት ታሪክ ታየ፣ ስንት ጉድ ተሰማ፡፡
ኢታሎ ቫሳሎ፣ ሉችያኖ ቫሳሎ፣
መንግስቱና ግርማ፣ ዝናቸው ከፍ ብሎ፣
ለዘመን ያደረ፣
ለአፍ የከበረ፣ ታሪክ እንደጻፉ፣
የዛሬም ልጆችሽ፣ ክብርሽን ያትርፉ፡፡
አዳነ፣ ሳላሃዲን፣ ሳላሃዲን፣ አዳነ፣
አገር ከህመሙ፣ በናንተ እግር ዳነ፣
እንግዲህ ይቅናችሁ፣ ብርታት አይራቃችሁ፣
ሴሌሜ ሴሌሜ፣ በቸር ያድርሳችሁ፡፡
“ሴሌሜ ሴሌሜ፣ ሆ ያ ሴሌሜ፣”
በዋልያ ፍቅር፣ አለሁኝ ታምሜ፤
“ሴላ፣ ሴላ፣ ሴላ፣
ሴላላላ ላ ሚያ”
ድል ካንቺ ጋር ይሁን እናት ኢትዮጵያ፡፡
__________ // __________
© አብዲ ሰዒድ
ጥር፣ 2005 E.C
shegerewa@gmail.com