በዕለተ አርብ ቀን፣ በዕለተ ከተራ፣
ለጥምቀት ዋዜማ፣ ወገን ሲጠራራ፣
ባንድ እየዘመረ፣
ባንድ እየጨፈረ፣
ሎሚ፣ ከረሜላ እየወረወረ …
በጸሎት ሊያነጋ፣ ውርጭ እየደፈረ፣
ሕዝበ ክርስቲያኑ፣ ጃን ሜዳ ሲያቀና፣
በክብሩ ማረፊያ፣ አዳሩን ሲያፀና፣
ለማለዳው ፀበል፣ ለግፊያው ሲዘጋጅ፣
ዋልያው ተጓዘ፣ ላገር ክብር ግዳጅ፡፡
ባህረ ጸበሉን፣ በፍቅር ተራጭቶ፣
ጽላቱን በክብር፣ ከደብሩ ሸኝቶ፣
ቃና ዘገሊላን፣ በጸሎት ተደፍቶ፣
የውስጠቱን መሻት፣ ላምላክ አስረድቶ፣
ጉዳዩ እንዲሞላ፣ በእምነት ተሞልቶ
ባሳለፈ ማግስት፣ በቀን መጀመሪያ፣
በዕለተ ሰኞ፣ ድል ይሁን ለኢትዮጵያ፡፡
እግዜር ያግዛችሁ፣
እግዜር ያበርታችሁ፣
ስንቱ በየደብሩ፣ ስለት ገባላችሁ፡፡
*** . . . ክልኤቱ ዱዓ . . . ***
በዕለተ አርብ ቀን፣ በየውመል ጁመዓ፣
መስጂድ ተሰባስቦ፣ ወገን ሲያደርግ ዱዓ፣
ያ ረቢ!… ያ ረቢ!…
አትበለን እምቢ !
ብርቱ ሃጃ አለብን፣ ሕዝብ ፊት አቅራቢ፣
ʻድምፃችን ይሰማ!… ድምፃችን ይሰማ!ʼ…
ጥረት ልፋታችን፣ ከንቱ እንዳይታማ፡፡
የረሱል መከታ፣ መጠጊያና ጋሻ፣
የቢላል የዘር ግንድ፣ የቸር መናገሻ፣
የኡሙ አይመን ምድር፣ ፍቅር መጨረሻ፣
የሶሃቦች ደጀን፣ የክፋት ማርከሻ፣
የነጃሺ ቀዬ፣ የእምባችን ማበሻ፣
ለሆነችው ምድር፣ እናት ኢትዮጵያ
ያ ረቢ አደራህን፣ አግዛት በፍልሚያ፡፡
አላህ ያግዛችሁ፣
አላህ ያበርታችሁ፣
ሸሆች በየመስጂድ፣ ዱዓ ያዙላችሁ፡፡
*** . . . ሰልስቱ ፍቅር . . . ***
ኑሮ አልሞላ ብሎ፣ ድህነት ቢገፋኝ፣
አሊያም ፖለቲካው፣ ሰው አገር ቢደፋኝ፣
ምን ብኖር እርቄ፣ ወገኔን ናፍቄ፣
ለአገሬስ ልጆች፣ ወጣለሁ ደምቄ፡፡
ዘር ማንዘር አልቆጥርም፣
ሃረግ አልመትርም፣
ቡትለካውም የለኝ፣ በከንቱ አልዘምርም፤
አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ አርማዬን ይዤ፣
ዘመን የወለደው፣ ተስፋዬን አርግዤ፣
አለሁ ከጎናችሁ፣
የአገሬ ልጆች ብርታት አይራቃችሁ
ኧረ እንኳን በደህና በሰላም መጣችሁ፡፡
__________ // _________
አብዲ ሰዒድ
ስኬት ለብሔራዊ ቡድናችን!
ፎቶ ምንጭ: @ Dimitru (Facebooker), www.DireTube.com, EthioTube