ታላቅ ብለን ያልነው የሰቀልነው ከላይ
ይፈርጥ ጀምሯል እንደበሰለ እንቧይ
ይወርዳል፣ ይዘቅጣል ይሰራል አምቡላ
ማር ጠጅ እንዳልነበር ይሆናል አተላ።
እንደጥሬ እንቁላል ከእጅ እንደወደቀ
አያነሱት ነገር ተጨመላለቀ
ቦካ ተለወሰ … አካሉ ረከሰ
ገማ በሰበሰ … ሃሳቡ ኮሰሰ።
አድንቀን … አድንቀን
መርቀን … አፅድቀን
ሳይቸግር አርቅቀን
ድንገት አሳቀቀን!
ኧረ አሸማቀቀን!
ህልማችን መከነ፣ ተስፋችን ተነነ
ትክን አለ አረረ፣ ውስጣችን በገነ
“ሀ”ብለን ተነሳን፣ ያለፈው ባከነ
ወየው ታናሽነት !
ወየው ርካሽነት !
‘ወየው… ወየው… ወየው
እኔስ ስንቱን አየው’
ወየው ብለን ቀረን፣ ፀጉራችን በነነ!
ተ
… ቃ
….. ጠ
……… ል
……….. ን !
ከንግዲህስ ወዲያ አቋም አውጥተናል!
ላልተወሰነ ቀን፣
… ላልተወሰነ ማታ፣
…… ላልተወሰነ ዘመን
ማድነቅ አቁመናል!
…… ማክበር አቁመናል!
……… አጉል ማሞጋገስ መስቀል አብቅተናል!
መ፟ሸ፟ንገል፣ መ፟ደለል
መ፟ገ፟ፈተር፣ መ፟በደል
መታሸት፣ መ፟ቀ፟ሸር
መ፟ፈ፟ተግ፣ መበጠር
መሰጣት፣ መ፟ከካት
መታመስ፣ መቆላት
መ፟ሰልቀጥ፣ መበላት
ከንግዲህ በቅቶናል!
ይኸው በአቋምችን ላንዋዥቅ ጸንተናል!
ላልተወሰነ ቀን፣
… ላልተወሰነ ማታ፣
…… ላልተወሰነ ዘመን
ማድነቅ አቁመናል!
…… ማክበር አቁመናል!
……… አጉል ማሞጋገስ ማሽቋለጥ ትተናል!
ይልቅ ለጎጇችን ለራስ በርትተናል!!!
//©አብዲ ሰዒድ //