እኔ እዚህ እየጮህኩኝ፣ እሱ እዚያ እየተኛ
በምን በኩል ይሆን የኛስ መገናኛ ?!
መጠየቄን አልተው፣ ዛሬም እጮሃለሁ
መልካም ቀን ይመጣል፣ አይቀርም አምናለሁ።
‘ባካችሁ ቀስቅሱት ያንን ባለ ተራ
የተሸከመው ቃል አለበት አደራ።
ምነው ለገመሳ ምነው ደነቆረ ?!
በገደል ማሚቱው ድምፄ ውሎ አደረ።
ተሰማ አስተጋባ ይኸው ዳር እስከዳር
አውቆ ተኝቶበት ሲያመቻቸው ለአዳር
ዛሬም አልረፈደም ቀን አለን ወዳጄ
በል ስማኝ ጩኸቴን ብያለሁ ማልጄ።
አማን ሰላም ይሁን፣ ቸር ይዋል መንደሩ
በፍቅር ይሻላል፣ ተሳስቦ ማደሩ።
ሃገርህ ሃገሬ፣ ርስትህም ናት ርስቴ
አብረን እንገንባት ተው ስማኝ በሞቴ።
ተው ስማኝ ሃገሬ
ተው ስማኝ ሃገሬ
ምነው መጨነቄ፣ ምነው መቸገሬ።
የተቀመጥክበት ዙፋንህ ቢደረጅ
አያልፍ እንዳይመስልህ ተው አታስጠናኝ ደጅ
ይልቅ ፅደቅበት መልካም አድርግና
ለዘመንህ ክብር ለስምህ ልዕቅና።
የከርቸሌውን በር ከፈት አርገው ባሻ
ህብረት ነው ‘ሚበጀን እስከመጨረሻ !
ፍቅር ነው ጥረቴ፣ ሳላም ነው ብርታቴ
እታገልሃለሁ፣ አይደክምም ጉልበቴ።
የነጃሺን አድባር፣ የቢላልን ምድር
የሙአይመንን ጡት፣ የረሱልን ፍቅር
በሳላም ልጠብቅ ላልደፍር ላልነካ
እኔስ ቃል አለብኝ በጡት የተነካ።
ዝምታህ ይከብዳል፣ እኔስ ሰግቻለሁ
አስረግጠህ ስማኝ፣ ተው ጓዴ ብያለሁ
ቃሌን ተቀበላት፣ ያው አስረክቤያለሁ።
ተው ስማኝ አገሬ
ተው ስማኝ አገሬ
በዛ መጨነቄ፣ በዛ መቸገሬ።
_________
(አብዲ ሰዒድ)